1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው ተባለ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 26 2017

በአማራ ክልል ለመማር የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አሁንም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል ። ለመማር የተመዘገቡትም ቢሆን በቂ የመማሪያ መጽሓፍት ማግኘት እንዳልቻሉ መምህራንና ተማሪዎች አመልክተዋል ።

Äthiopien | Bildungsbüro der Region Amhara
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ትምህርት ቤት የደረሱትም መማሪያ መጽሐፍት አላገኙም

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ለመማር የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አሁንም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል ። ለመማር የተመዘገቡትም ቢሆን በቂ የመማሪያ መጽሓፍት ማግኘት እንዳልቻሉ መምህራንና ተማሪዎች አመልክተዋል ። 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዘገቦ ለማስተማር አቅዶ የነበረ ቢሆንም የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጥ መስከርም ወር አጋማሽ ላይ ገልፆ ነበር፣ ይሁንጂ ከመስቅል በኋላ ቁጥሩ ሊጭምር እንደሚችል በወቅቱ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ለትምህርት የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሌለውና ችግሩ ምስራቅ ጎጃም ዞንን ጨምሮ በሌሎችም የምዕራብ አማራ ዞኖች መቀጠሉን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

በምዕራብ አማራ ያሉ በርካታ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት አልመጡም

ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም በከፊል፣ ደቡብ ጎንድር በከፊል፣ አዊ ብሔርሰብ አስተዳደር በከፊል ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ አስረድተዋል። ማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተሻለ አፈፃፅም ቢያስመዘግብም፣ በአንዳንድ ወረዳዎች ኝ አሁንም ችግሮች እንዳሉ አቶ ጌታቸው ገልጠዋል። የምስራቅ አማራ ዞኖች ከምዕራብ አማራ ዞኖች ሲነፃፀር የተሻል የተማሪ ምዝገባ መካሄዱንም ተናግረዋል። የተመዘገቡ ተማሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም  በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች ከፍተኛ የመጽሐፍት እጥረት እንዳለባቸው ያነጋገርናችው ተማሪዎች ይናገራሉ።

ትምህርት ቤት የደረሱትም መማሪያ መጽሐፍት አላገኙም

አርሴማ መስፍን በደሴ ከተማ አስተዳደር ሆጤ ሁለተናኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የሒሳብ፣ የእንግሊዝኛና የፊዚክስ መማሪያ መጽሐፍት እጥረት በስፋት መኖሩን ነግራናልች። አስራ ሁለተኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና ለሚወስድ ተማሪ ይህ ከባድ እንደሆነ ነው ያስረዳችው።

በባሕር ዳር ከተማ የአፄ ሠርፀ ድንግል ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዮናስ ተሻገር በበኩሉ በተለይ የሙያ ትምህርት መጽሐፍት በትምህርት ቤቱ በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት እንዳለበት አስረድቷል።

መምህራን "በመጽሐፍት እጥረት ባግባቡ ማስተማር አልቻልንም” አሉ

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንድ የዋግሹም አድማሱ ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር እንደገለፁልን በትምህርት ቤቱ አንድም የ12ኛ ክፍል ተማሪ የመማሪያ መጽሐፍ የለውም። የመጽሐፍ እጥረቱ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጠዋል።

አማራ ክልል፦ ትምህርት ቤት የደረሱትም መማሪያ መጽሐፍት አላገኙም ተብሏልምስል Alemnew Mekonnen/DW

በትምህርት ቤቱ እጅግ አነስተኛ የመጽሐፍት ቁጥር እንዳል የተናገሩት መምህሩ። ምንም መፀሐፍ የሌላቸው የትምህርት መስኮችም አሉ ነው ያሉት። "ከ12ኛ ክፍል አንድም የእንግሊዝኛ መማሪያ መጽሐፍ ያለው ተማሪ የለም” ብለለዋል። በባሕርዳር ከተማ የሚገኝ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ሌላ መምህርም ተመሳሳይ አሰተያየት ሰጥተዋል፣ አንድ መጽሐፍ በርከት እየተሰጠ ያለው፣ ይህም የተሻለ የሚባል እንደሆን አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ አንድ መጽሐፍ ለ5 እና ለ6 እየተጠቀሙ እንደሆን አስረድተዋል፣ ይህም የተሻለ ሊባል እንደሚችል ጠቁመዋል፣ ምንም የሌላቸው ስለሚኖሩ። በዚህ መንገድ ማስተማር ከባድ እንደሆነባቸው በምሬት ገልጠዋል።

ቁጠራችው በርካታ የሆኑ ተማሪዎች ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ትምህርት ቤቱ መጥተው መመዝገባቸው አንዱ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል። በባሕርዳር ከተማ የአፄ ሠርፀ ድንግል መካከለኛ ትምህርተ ቤት ዳይሬክተር በሙያ መጽሐፍት በኩል እጥረት ቢኖርም በሌሎቸ መትሐፍት በኩል ከሌሎች ትምሀርት ቤቶች ሲነፃፀር የተሻል መሆኑን ነግረውናል።

በአንደኛ ደረጃ ያለውን የመጽሐፍት ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦ 4 ሚሊዮን መጽሐፍት በህትመት ላይ መሆናቸውን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ተናግረዋል።

"4 ሚሊዮን የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት መጽሐፍት በህትመት ላይ ነው” ትምህርት ቢሮ

"... በ2017 የትምህርት ዘመን የአማራ ክልል መንግሥት 1.6 ቢሊዮን ብር ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚያገለግሉ መጽሐፍት ለማሳትም በጀት መድቧል፣ ከዚህ ውስጥ በ729 ሚሊዮን ብር  የ4.1 ሚሊዮን መጽሐፍት ህትመት ውል ተይዞ ህትመቱ በሂደት ላይ ነው ” ነው ያሉት።

ሕርዳር ከተማ የአፄ ሠርፀ ድንግል መካከለኛ ትምህርተ ቤትምስል Alemnew Mekonnen/DW

5 ሚሊዮን የሁለትኛ ደረጃ ምማሪያ መጽሐፍት በስርጭት ላይ ሰለመሆኑ

ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚሆኑ ከ5 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍት ከትምህርት ሚኒስቴር ወደ ክልሉ ትምህርት ቢሮ መድረሳቸውን ኃላፊው አመልክተው፣  መዘግየት በዝግጅትና በስርጭት ወቅት እንደነበር አቶ ጌታቸው አልደበቁም፣  የክልሉ የፀጥታ ችግርም ሌላው መጽሐፍትን ወደ ትምህርት ቤቶች ለማድረስ ፈተና እነድሆነባቸው ገልጠዋል።

ወደ 6.7 ሚሊዮን የሁለተኛ ትምህርት ቤት መጽሐፍት ከፌደራሉ ትምህርት ሚኒስቴር ወደ አማራ ክልል እየተላከ መሆኑን ጠቅሰው፣ 5.2 ሚሊዮን መጽሐፍት ወደ አማራ ክልል ደርሰው በስርጭት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ባለፈው 2016 ዓም በአማራ ክልል 16 ሚሊዮን መጽሐፍት ታትመው ለስርጭት በቅተው እንደነበርም አቶ ጌታቸው አስረድተዋል። በአማራ ክልል  ከ10  ሺህ በላይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW