1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል ይፈፀማል የተባለዉ ግፍ፣ የኢትዮ-ሶማሊያ ድርድር፣ የኬንያ ቀዉስ

ዓርብ፣ ሰኔ 28 2016

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ ሑዩማን ራይትስ ዋች በያዝነዉ ሳምንት ባሰራጨዉ ዘገባዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባልደረቦች በአማራ ክልል፣ «መጠነ ሰፊ» ጥሰት አድርሰዋል ይላል።ድርጅቱ በተለይ በጤና ተቋማት፣ ባለሙያዎችና ሕሙማንና ላይ ደረሰ ያለዉን ግፍ «ከጦር ወንጀል እኩል የሚቆጠር« ብሎታልም

ሑይማን ራይትስ ዋች እንደሚለዉ የመብት ጥሰቱ «ከዞር ወንጀል እኩል» የሚቆጠር ነዉ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባልደረቦች አማራ ክልል ዉስጥ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰዋል በማለት ሑይማን ራይትስ ዋች ዘግቧል።ምስል Solomon Muche/DW

አማራ ክልል ይፈፀማል የተባለዉ ግፍ፣ የኢትዮ-ሶማሊያ ድርድር፣ የኬንያ ቀዉስ

This browser does not support the audio element.

 

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።በዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ሳምንቱን በተዘገቡ ሶስት ጉዳዮች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ከስድብ፣ ዘለፈና ዉንጀላ የፀዱትን ነቅሰን እጠናቅረናል።አመራ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይፈፀማል ሥለተባለዉ ግፍ ሑዩማን ራይትስ ዋች ያወጣዉ ዘገባ፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ድርድርና የኬንያ ተቃዉሞ ሰልፍ ናቸዉ-ርዕሶቹ።በዚሁ ቅደም ተከተል ይቀርባሉ። አብራችሁኝ ቆዩ። 

አማራ ክልል ይፈፀማል የተባለዉ ግፍ

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ ሑዩማን ራይትስ ዋች በያዝነዉ ሳምንት ባሰራጨዉ ዘገባዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባልደረቦች በአማራ ክልል፣ «መጠነ ሰፊ» ጥሰት አድርሰዋል ይላል።ድርጅቱ በተለይ በጤና ተቋማት፣ ባለሙያዎችና ሕሙማንና ላይ ደረሰ ያለዉን ግፍ «ከጦር ወንጀል እኩል የሚቆጠር« ብሎታልም።ለዘገባዉ መሠረት ያደረገዉ ግፍ ተፈፀመብን ያሉና ያዩ ሰዎችን አነጋግሮ እንደሆነ አስታዉቋልም።በዘገባዉ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናትን አስተያየት ለማካታት ዶቸ ቬለ እስከ ትናንት ድረስ ቢጥርም ባለሥልጣናቱ አልተገኙም።
ሕይወት ወልዴ ግን በፌስ ቡክ ጥያቄ ብጤ አስተያየት ሰጥላች።«ስንት ንፁሃን ሲገደሉ ነው እምባገነኑ ለፍርድ የሚቀርበው?» የሚል።

አረጋዊ ገብረዮሐንስ በበኩሉ የአማራ ክልልን ሁኔታ ከትግራይ ክልል ብጤዉ ጋር ያነፃፅራል።«ትግራይ ላይ ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ሲነፃፃር» ይልና አረጋዊ እንደ ጥሩ የአርቲሜቲክ ቀማሪ 0. አድርጎ 8 ዜሮ አስከትሎ 1 ነዉ ይላል።የካርሎስ በቀለ ቢቂላ አስተያየት አጭር ነዉ።«ከመከላከያ ጎን እቆማለሁ።» የሚል።ጋሻዉ ሙሉጌታም እንደ ካርሎስ ባጭሩ ግን ተቃርኖ «ይነጋል አይቀርም።» አለ በፌስ ቡክ።

ልዩ ሆሜስ የሚል ስም ያለዉ ወይም ያላት አስተያየት ሰጪ አስተያየት ሒዩማን ራይትስ ዋችን የሚተች ይመስላል። «አይዞሽ ቻሉት ውጊያ እቃቃ መሰላችሁ?» ጠየቀ ወይም ጠየቀች ልዩ ሆሜስ በፌስ ቡክ።ቀጠለም« ምነው እስራኤል ጋዛ ላይ ስትጨፈጭፍ አልከሰሳቹሕም» አከለ ወይም አከለች-ልዩ ሆሜስ።ቢኒ ማኒ ዘገባዉን «የተሳሳተ ነዉ» ባይ ነዉ።«አማራ ክልል በተለይ ጎንደር መከላከያ ህዝቡን እያገለገለ ነው ፋኖ ሰው እያገተ አስቸግሮናል።» የቢኒ ማኒ አስተያየት ነዉ።

ዓሊ ኢድሪስ  «የአፈሪካ መንግስታትን ለማስፈራራት የተቋቋመ ደርጅት ነው » ብሎ ይጀምርና ይቀጥላል።«ስለ ሂዩማን ራይት የቆመ ቢሆንማ ሰለጋዛ ስቆቃ ዝምታን አይመረጥም ነብር ስለዚህ ማንም አይሰማቸውም» ጨረሰ ዓሊ ኢድሪስ።ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ «ሰሞኑን በሸዋ እና በጎጃም የተገደሉት ገበሬወች አይጠቀስም ከዚህ በላይ የጦር ወንጀል አለ» ጠያቂዉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል ስም አለዉ።
ወርቁ ስዩም ላቀዉ «ምን ያልተፈፀመ ግፍ አለ???!!!» ይላል።አስተያየቱን በሁለት የጥያቄና በሶስት ቃል አጋንኖ ምልክቶች አጠናክሮታል።

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ባደረጉት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ለኢትዮጵያ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚገመተዉ የበርበራ ወደብምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ድርድር

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት እዉቅና ከሌላት ከሶማሊላንድጋር ባለፈዉ ታሕሳስ የመግባቢያ ሥምምነት ከተፈራረመች ወዲሕ በሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክና በኢትዮጵያ መካከል ያለዉ ግንኑነት ሻክሯል።የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ 20 ኪሎሜትር የሚሰፋ ወደብ ለ50 ዓመት ትኮናተራለች።
ኢትዮጵያ ባንፃሩ  ከ30 ዓመት በፊት ከሞቃዲሾ ማዕከላዊ መንግስት አስተዳደርተገንጥላ የራስዋን መንግስት ለመሠረተችዉ ሶማሊላንድ ዕዉቅና ትሰጣለች።የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ላይ የተፈረመዉን የመግባቢያ ስምምነት ከመንቀፍ አልፈዉ «ኢትዮጵያ የሶማሊያን ልዑላዊ ግዛት ወርራለች» በማለት ወንጀለዋል።ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትንም አቋርጠዋል።
በሁለቱ ጎረቤት ሐገራት መካከል የተካረረዉን ጠብ ለማርገብ ቱርክ በጀመረችዉ ጥረት የሁለቱን ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ባለፈዉ ሰኞ አንካራ ላይ በተዘዋዋሪ አደራድራለች።ሁለቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ፊት ለፊት ባይነጋገሩም በስማ በለዉ የተደረገዉ ድርድር ተስፋ ሰጪ ነዉ ተብሏል።በመጪዉ ነሐሴ ማብቂያ ለመቀጥልም ተደራዳሪና አደራዳሪዎች ተስማምተዋል።
ያብፀጋ ኦኬሎ አስተያየት ምክርን ከምኞት ያሰባጠረ ነዉ።እንዲሕ ይላል በፌስ ቡክ።
«በጋራ መልማት ሰላማዊ ቀጠናዊ ትስስር ለምስራቅ አፍሪካ ወሳኝ እንደሆነ ግልፅ ነው። መቼም ሶማሌ የሚበጃትን እንደምትመርጥ አልጠራጠርም። ሰላምና ልማት ለኢትዮ-ሶማሌ! ሰላም ለምስራቅ አፍሪካ!» ያብፀጋ ነዉ-ይሕን ያለዉ።
ጥላሁን አሰፋ እሱም በፌስ ቡክ «ሶማሊያ  የኢትዮጵያን ዉለታ መርሣት የለባትም እንደሃገር ምክርቤት ይኖራት ዘንድ ብዙ መሥዋእትነትን ከፍላላች » ይላል ጥላሁን አሰፋ።ቀጠለም።« በቅንነት በሠላማዊ መንገድ ለመወያያት መሞከር አለበት።» እያለ።
አብድረሕማን ደጉ ምርት የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ድርድሩ በመጀመሩ የተደሰተ ይመስላል።ዱዓ ብጤም አክሎበታል።«እሰይ ደስ የሚል ዜና። አላህ መጨረሻውን ያሳምርልን» ይላል አብድረሕማን።
ጥላሁን አሰፋ  «ሁለቱ አገሮች በሥምምነት ቢሠሩ ነዉ ፣ ለሁለቱም ጥሩ የሚሆነዉ» ሲል፣ ንዑማን ሁንዳ ዱርሳ «መወያየት የተሻለዉ መንገድ ነው» ባይ ነዉ።ከፈኒ አዱኛም የመወያየትን ጥቅም ይገልፃል በፌስ ቡክ።«በመነጋገር መግባባት ይቻላል። ወደ ግጭት ከመግባትም ይጠብቃል።« ይመክራል-ከፈኒ።
        የኬንያ ተቃዉሞ ሰልፍ፣የፕሬዝደንቱ ምላሽ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐባይ አሕመድና የሶማሊላንዱ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የመግባቢያ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅትምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

ሶስተኛዉ ርዕስ የመጨረሻዉም  ነዉ።ከኢትዮጵያም፣ ከኢትዮ-ሶማሊያም ጉዳይ ወጣ ብሉ ግን ብዙም ሳይርቅ በኬንያ ፖለቲካዊ ቀዉስ ላይ ያተኩራል።የኬንያ መንግስት ያረቀወዉ የግብር ጭማሪ ደንብ በቅርቡ በሐገሪቱ ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እንዲያፀድቁት ተወስኖ ነበር።
ይሁንና የኬንያ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ «የገንዘብ ደንብ 2024 የተባለዉ ረቂቅ ደንብ ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉሞታል።ተቃዋሞ ሰልፈኛዉን ለመበተን ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸዉን የኬንያ የጤና ባለሙያዎች ማሕበር ባለፈዉ ሳምት አስታዉቋል።የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ተቃዉሞዉ ማየሉን ሲረዱ ባለፈዉ ሮብ እጅ ሰጡ።ደንቡን ሰረዙት።
«የተማረ መሪ።» አለ ታደለ ፀጋዬ በፌስ ቡክ።ሳቤላ ብዙነሕ አዳሙ  እንደ ታደለ ፀጋዬ ሁሉ ፕሬዝደንት ሩቶን ታደንቃለች። «የህዝብ መሪ እንዲህ ነው።የእኛ አሉ እንጂ ...?» እያለች።የሸዋ ጌጥ በበኩሉ ግን በፌስ ቡክ «እንደኛ ቢደነዝዙ አይሻልም» ይጠይቃል የሸዋ ጌጥ።

ሶሎሞን ታደሰ «ግርግር ለሌባ ይመቻል ማለት ይህ ነዉ።ድሮም የግብር ጎዳይ አይደለም ደሞ አሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲ አይነት ነገር እንዲፈጠር የሚፈልጉ » እያለ ይተቻል።ክንዳለም ታደሰ ግን የሶሎሞንን አስተያየት አይቀበለዉም።«ልብ አላቸዉ እነሱ» አለ ክንዳለም በፊስ ቡክ-ኬንያዉያንን መሆኑ ነዉ።ቀጠለም « እኛ አለን እንጅ???» በሶስት ጥያቄ ምልክት አሳረገ።

የኬንያ ወጣቶች የሐገሪቱ መንግስት ያረቀቀዉን የግብር ጭማሪ ደንብ በመቃወም ናይሮቢ ዉስጥ ካደረጉት ተቃዉሞ አንዱምስል Monicah Mwangi/REUTERS

 

ንጉሴ ስጦት።«ችግራቸው በተቃውሞ ሰልፍ ከተፈታማ ጥሩ ነው።» ብሎ ጀመረ ተቺ አስተያየቱን።«አሉ እንጂ የኛዎቹ በተቃውሞ ሰልፍ ቀርቶ በጦርነትም የህዝብን ችግር እማይረዱ።» «ጀግናው የአዲስ አበባም ሕዝብ በሚል ሐረግ ምፀታዊ አስተያየቱን የጀመረዉ ፊሽ መኮንን ነዉ።«ለታክሲ እና ለዳቦ መሰለፉን አሳይቷል።በሚቀጥለውም ወደመጣበት እንደሚመለስ አስታውቆል። ለቆ ለመሄድ ዝግጁ ነው።« አከለ ፍሰሐ መኮንን 
የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ቅኝት ለሳምቱ የሰማችሁትን ያክል ነበር።መልካም ጊዜ በያላችሁበት።

ነጋሽ መሐመድ ነኝ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW