አሜሪካ ለኢትዮጵያውን በምትሰጠው የመግቢያ ቪዛ ላይ ቁጥጥሯን አጠናከረች
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ስደተኛ ላልሆኑ እና ወደ ዩናይትድ ስቴት መጓዝ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ጊዜያዊ ቪዛ የሶስት ወራት ብቻ እንደሚሆን አስታወቀ። በዚህ የአጭር ጊዜ ቪዛ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ መግባት የሚችሉት አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚሆን ኤምባሲው ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
እርምጃው ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን የገለጸው የአሜሪካ ኤምባሲ ውሳኔው ከዚያ በፊት የተሰጡ ቪዛዎች ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር አረጋግጧል። እስካሁን የነበረው አሠራር የተቀየረው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ስደተኛ ያልሆኑ ሰዎች የቪዛ አሰጣጥ ፖሊሲ ላይ ባደረገው ለውጥ ምክንያት እንደሆነ የኤምባሲው መግለጫ ይጠቁማል።
ስደተኛ ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጥ ቪዛ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ለቱሪዝም፣ ለንግድ፣ ለሕክምና እና የተወሰኑ ቋሚ ያልሆኑ ሥራዎች በጊዜያዊነት ወደ አሜሪካ እንዲገቡ የሚፈቅድ ነው።
እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያውያን የሚያገኙት ቪዛ ወደ አሜሪካ በተደጋጋሚ እንዲገቡ የሚፈቅድ (multiple-entry) እና እስከ አንድ አመት የሚቆይ ነበር። አዲሱ ገደብ በተለይ ተማሪዎች ፣ ነጋዴዎች፣ ባለሙያዎች እና ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት የሚጓዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በጎርጎሮሳዊው 2024 ብቻ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ 23,270 ቪዛ ስደተኛ ላልሆኑ ሰዎች እንደሰጠዩናይትድ ስቴትስውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መረጃ ያሳያል። በመሥሪያ ቤቱ መረጃ መሠረት በአፍሪካ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በዓመቱ በአጠቃላይ 343,075 ቪዛ ስደተኛ ላልሆኑ ሰዎች ሰጥተዋል።
በናይጄሪያ አቡጃ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና መቀመጫውን በሌጎስ ያደረገው የሀገሪቱ ቆንስላ በድምሩ 64 ሺሕ ገደማ ቪዛ በመስጠት ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛሉ። የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ስደተኛ ላልሆኑ ሰዎች ቪዛ የሚሰጥበት ፖሊሲ ላይ ያደረገው ለውጥ በተመሳሳይ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በናይጄሪያ ዜጎችም ላይ ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም መሠረት ናይጄሪያውያን የሚሰጣቸው ቪዛ የሶስት ወራት ብቻ ሲሆን ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያገለግለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
በዶናልድ ትራምፕ የሚመራው የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያን ጨምሮ በ36 ሀገራት ላይ የጉዞ ዕቀባ የመጣል ዕቅድ እንዳለው ባለፈው ሰኔ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ካሊድ አብዱኬ
እሸቴ በቀለ