1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እብዱ ማነዉ?

ሰኞ፣ ሐምሌ 29 2011

ዶናልድ ትራምፕ። በርግጥ ብቻቸዉን አይደሉም።ስደተኛን ብቻ ሳይሆን ነጭ ያልሆኑ የምክር ቤት እንደራሴዎችን ሳይቀር  አንዴ በኃይማኖታቸዉ፣ ሌላ ጊዜ በፆታቸዉ፣ በተደጋጋሚ በቆዳ ቀለማቸዉ ሲያበሻቅጡ ሚሊዮኖች ይደግፉ፣ያጨበጨቡ፤ያደንቁ ያወድሳቸዋልም።

USA El Paso | Trauer nach Anschlag
ምስል Reuters/C. O'Hare

የኤል ፔሶና የዴይተን ግድያ

This browser does not support the audio element.

ጆርዳን አንኮንዶ እና ፓትሪክ ክሩሸየስ አይተዋወቁም።ግን የአንድ ሐገር-የአንድ ግዛት ልጆች ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ-ቴክሳስ።አኗኗር፣ አስተሳሰብ፣የሕይወት ፍልስፍናቸዉም ይቃረን ይሆናል።ሁለቱም ግን ወጣቶች ናቸዉ።እሷ የ25፣ እሱ 21 ዓመታቸዉ።እሷ ባለቤቷን አስከትላ፣ የሁለት ወር ሕፃን ልጇን ታቅፋ፣ እሱ አንድ ሺሕ ኪሎሜትር አቋርጦ፣ ጠመንጃዉን አቀባብሎ እሷ መንደር ከትልቁ የገበያ አዳራሽ ገቡ።ኤል ፔሶ ዎልማርክት።ቅዳሜ።ገደላት። ባለቤቷን፣ ሌሎች 18 ብጤዎቻቸዉንም ረሸነ።This is America ይሉሐል አሜሪካኖች።የደጎች-የለጋሶች፣ የጨካኞች-አረመኔዎች ሐገር።የድሆች-የቱጃሮች፣ የዘረኞች-የሰብአዊ አሳቢዎች ምድር።ከሁሉም በላይ የዘር ጥላቻ የአገዛዝ መርሐቸው ምሶሶ የሆነባት የዶናልድ ትራምፕ ትልቅ ሐገር።አሜሪካ ትቅደም ነዉ መፈክራቸዉ።አሜሪካንን ዳግም ትልቅ እናድርግ ነዉ ዓላማቸዉ።ለላቅ ትልቅነት በምታትረዉ ትልቅ ሐገር ባንድ ቀን ዕድሜ ከኤል-ፔሶ እስከ ዴይተን 29 አስከሬን የተቆጠረበት ግድያ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።
                                  
የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ አስከባሪ ባለስልጣናት የሐገር ዉስጥ አሸባሪ ብለዉታል።የሜክሲኮዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማርሴሎ ኤብራርድ በሜክሲኮ ማሕበርሰብ ላይ የተፈፀመ ሽብር።«እኛ ዩናይትድ ስቴትስ በሚኖሩ በሜክሲኮ ማሕበረሰብ አባላት ላይ የተፈፀመ የሽብር ጥቃት ነዉ እንላለን።»
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሕግ አስከባሪዎቻቸዉን አስተያየት፣ የሜክሲኮ ባለስልጣናትን ግምት አልተቀበሉትም።የመርማሪዎችን የምርመራ ዉጤትም አልጠበቁም።የኤል ፔሶና የዴይተን ገዳዮችን «አዕምሯቸዉ የተነካ» ናቸዉ አሉ።አብዶች።
«ይሕ የአዕምሮ በሽተኝነት ችግር ጭምር ነዉ።የሁለቱንም  (ግድያ) ብትመለከቱ የአዕምሮ ሕመምተኝነት ነዉ።እነዚሕ በእዉነቱ ከፍተኛ የአዕምሮ ሕመም የተጠናወታቸዉ ሰዎች ናቸዉ።»
አሜሪካ! ስንቱን እብድ ታስተናግዳለችስ? የእብደቱ ምንጭስ የት ይሆን? ፓትሪክ ክሩሽየስ ተወልዶ ካደገበት ፕላኖ፣ አለን ቴክሳስ፣ 1000 ኪሎ ሜትር የተጓዘበትን ሰበብ ምክንያት በግልፅ ፅፎ 8chan በተባለዉ የቀኝ ፅንፈኞች አምደ መረብ አሰራጭቶ ነበር።የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች ፖሊስን ጠቅሰዉ እንደዘገቡት ግለሰቡ ግለሰቡ ኑዛዜ በመሰለዉ መጣጥፉ ባለፈዉ መጋቢት ኒዉዚላንድ አልኑር መስጊድ ዉስጥ ለጁመዓ ሶላት የተሰበሰቡ ሙስሊሞችን የረሸነዉ ግለሰብ አድናቂ፣ የሽብር ግድያዉ ደጋፊ ነዉ።
በዘገባዉ መሠረት ትጥቅ አልባ፣ እንደ ኃይማኖታቸዉ ወግ ፈጣሪያቸዉን ለመማፀን የተሰበሰቡ 51 ሲቢሎች በመደዳ መረሸናቸዉን በፁሁፉ ደግፏል።ወጣቱ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን የስደተኞች መርሕ በተለይም ሜክሲኮን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የሚያገናኘዉን ድንበር በግንብ አጥር ለመዝጋት መወሰናቸዉን አጥብቆ ይደግፋል።ትራምፕ ግን «እብድ» አሉት።እብዱ ማነዉ? ስንትስ ነዉ? አናዉቅም።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን እንዲሕ ማለታቸዉን ሠምተናል።
«ሜክሲኮ ዜጎችዋን ስትልክ ጥሩዎቹን አይልኩም።አደንዛዥ ዕፅ ያመጣሉ።ወንጀል ያመጣሉ።ሴት ደፋሪዎችን ያመጣሉ።»

ምስል Getty Images/AFP/M. Ralston

ጆርዳን አንኮንዶ በርግጥ ከሜክሲኮ ዘር የምትጋራ ወጣት ናት።ትራምፕ ያሉትን ግን አንዱንም አልነበረችም።ሰኔ፣ ለሷ የደስታ ወር ነበር።ሶስተኛ ልጇን በሰላም ተገላገለች።ወንድ ልጅ።ደስታ።ኃምሌም ጥሩ ነበር። ሁለተኛ ባለቤቷን (አንድሬ)ን ያገባችበትን አንደኛ ዓመት አከበረች።ፌስታ።
የ25 ዓመቷ ወጣት የመጀመሪያ ልጇን በቅርቡ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ለማስገባት አቅዳለች።ሌላ ደስታ።ለደስታዉ ዝግጅት የመጀመሪያ ልጇን ስፖርት መለማመጃ ቤት ትታ፣ ሶስተኛ ልጇን ታቅፋ ከተወዳጁ ባለቤቷ ጋር ገበያ ወጣች።ኤል ፓሶ።ዎልማርክት፣ የገበያ አዳራሽ።
እሷ ባለቤትዋን አስከትላ ልጇን ታቅፋ ከገበያዉ አዳራሽ ስትገባ፣ የዶናልድ ትራምፕ የጥላቻ መርሕ ያናወዘዉ ወጣት ጠመንጃዉን ታቅፎ ካዳራሹ ገባ።ማን ይናገር የነበረ? «ወዲያዉ ቡም ቡም ቡም የሚል ድምፅ ሰማሁኝ።ከማክዶናልድ፣ ከአዳራሹ፣ በአደጋ ጊዜ በሮች እየሮጥን ወጣን።አብሮኝ የነበረዉ ሰዉዬ ጭንቅላቱን የተመታ ወንድ፣ ደረቷን የቆሰለች ሴትዮ----ደም የሚፈሳቸዉ ብዙ ሰዎች--- በቃ እንደ ተለመደ ነገር ማየቱን ነገረኝ።»ቅዳሜ።አንዷ ጆርዷን፣ አንዱ አድሬ (ባለቤቷ) ይሆኑ ይሆናል።ብቻ ሁለቱም አልተመለሱም።መቼም አይመለሱም።«በጣም ጥሩ ሰዎች ነበሩ።ጠንካራ ሰራተኞች ነበሩ።ለሶስቱ ልጆቻቸዉ ደግ ወላጆች ነበሩ።ለልጆቻቸዉ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።ከሁሉም በላይ በፍቅርና ዉዴታ ተከባክበዋቸዋል።በዚሕ ነዉ የምናስታዉሳቸዉ።»
የጆርዳን አክስት ባለቤት ናቸዉ።የሁለት ወሩ ሕፃን ተርፏል።ፖል።የ21 ዓመቱ ፓትሪክ ክሩሽየስ ከገደላቸዉ 20 ሰዎች ሰባቱ የሜክሲኮ ዜጎች ናቸዉ።ከ26ቱ ቁስለኞች ደግሞ ስድስቱ የሜክሲኮ ዜጎች ናቸዉ።ሜክሲኮ ጠረፍ ላይ የምትገኘዉ የኤል ፔሶ ከተማ አብዛኛ ነዋሪ አድም የሜክሲኮ አለያም  የሌላ የደቡብ አሜሪካ ሐገር ዝርያ ያላቸዉ በመሆናቸዉ ከተቀሩት ሟች-ቁስለኞቹም አብዛኞቹ የደቡብ አሜሪካ ዝርያ ያላቸዉ ናቸዉ ተብሎ ይታመናል።እዚያዉ ኤልፔሶ የሚኖሩት የ55 ዓመቱ ሜክሲኮዊ ኤፍሪያን ዲያስ ገዳዮች እኛ ሜክሲኮዎች ብንሆን ኖሮ አይነት ይላሉ፣ ጦርነት ይፈነዳ ነበር።
«(ሟቾቹ) ከዘረኝነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸዉ የዋሆች ነበሩ።እዚሕ ኤል ፔሶ ዉስጥ ብዙ ሜክሲኮዎችና አሜሪካኖች እንኖራለን።እንዲሕ አይነት ነገር አጋጥሞን አያዉቅም።እኛ ሜክሲኮዎች  እንዲሕ አይነት ጥቃት ብናደርስ ወይም ለጥቃቱ አፀፋ ብንሰጥ ጦርነት ይጫር ነበር።ሕዝቡ አብዷል።ልጁ (ገዳዩ) እኔ እንጃ፣ እንጃ! እንዲሕ አይነት ነገር ሲያደርስ ምን እንዳሰበ----»
ገዳዮች ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት አብደዋል።ሰዉዬዉ እንዳሉት ደግሞ የሟች ወላጅ-ወዳጅ-ዘመዶች አብደዋል።ያላበደዉ ማነዉ? አናዉቅም።የሚታወቀዉ የኤል ፔሶዉ ገዳይ የትራምፕ ዘረኛ መርሕ ተማሪኪ መሆኑን መፃፉ ግን ተዘግቧል።
ሰዉዬዉ ባባታቸዉ የጀርመን ስደተኞች የልጅ ልጅ ናቸዉ።በናታቸዉ የስኮትላንድ ስደተኛ ልጅ ናቸዉ።ባለቤታቸዉ የስሎቬኒያ ስደተኛ ናቸዉ።ከምርጫ ዘመቻቸዉ ጊዜ ጀምሮ የዉጪ መርሐቸዉ ምሰሶ ያደረጉት ከነጭ ዘር ዉጪ ያለዉን ዘር-ከትልቂቱ ሐገር ዝር እንዳይል ማገድ ነዉ።ሲቻል የመግቢያ ፈቃድ ቪዛ በሕግ መከልከል፣ በሕግ ሲያቅት የፍቃድ መመዘኛዉን ተጓዞች እንዳይችሉት ማድረግ።
ዶናልድ ትራምፕ። በርግጥ ብቻቸዉን አይደሉም።ስደተኛን ብቻ ሳይሆን ነጭ ያልሆኑ የምክር ቤት እንደራሴዎችን ሳይቀር  አንዴ በኃይማኖታቸዉ፣ ሌላ ጊዜ በፆታቸዉ፣ በተደጋጋሚ በቆዳ ቀለማቸዉ ሲያበሻቅጡ ሚሊዮኖች ይደግፉ፣ያጨበጨቡ፤ያደንቁ ያወድሳቸዋልም።«በደቡባዊ ድንበራችን ትልቅ ግንብ እንገነባለን።የማስገንቢያዉን ዋጋ ሜክሲኮ ትከፍላለች።መቶ በመቶ ይከፍላሉ።ከመጀመሪያዉ ቀን ጀምሮ በቀላሉ የማይደፈር፤ ጠንካራ፤ ረጅም፤ ዉብ ግንብ መገንባት እንጀምራለን።»
የ21 ዓመቱ ወጣት ኤልፖሶ ላይ 20 ሰዎችን መግደሉ ዜና አሜሪካኖች አስደንግጦ፣ ሜክሲኮዎችን አሳዝኖ፤ የተቀረዉን ዓለም አነጋግሮ ሳያበቃ በ13 ሰዓታት ልዩነት ዴይተን-ኦሐዮ በሌላ ግድያ ተሸበረች።
ኮነር ቤቲንግ 24 ዓመቱ ነዉ።መዝነኛ ቤት ዉስጥ በተሰባሰቡ ወጣቶች ላይ ጥይቱን አርከፈከፈ።ዘጠኝ ገደለ።አንዷ ታናሽ እሕቱ ነበረች። በአብዛኛዉ ጥቁሮች የሚያዘወትሩትን መዝናኛ ስፍራ ያሸበረዉ ወጣት እዚያዉ በፖሊስ ተገድሏል።ሁለቱንም ገዳዮች የ«ዓዕምሮ ሕመምተኞች» ያሉት ዶናልድ ትራምፕ በሐገራችን ጥላቻ ሥፍራ የለዉም አሉ።
«ሕዝቡን እንወዳለን።እኛ ሐገር ጥላቻ ስፍራ የለዉም።ጉዳዩን በቅርብ እንከታተላለን።ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢል ባር ጋር በሰፊዉ ተነጋግሬያለሁ።ከFBI የበላይ ኃላፊ ክርስቶፈር ወሪይ ጋር፣ ከሁለቱ አገረ-ገዢዎች ጋርም ተነጋግሬያለሁ።ብዙ ነገር እየሰራን ነዉ።ሕግ አስከባሪዎችና ሌሎች ሰዎችም እየሰሩ ነዉ።»
«ጥላቻ ሥፍራ የለዉም።» አሉ ዶናልድ ትራምፕ።ኢትዮጵያዊዉ ገበሬ «ብሳና ይነቅዛል ወይ» ብለዉ ጠየቁት አሉ።«አረ» አለ አሉ ሲመልስ።«ዛፉን ሁሉ ማን አስተማረዉ እና።»  

ምስል picture-alliance/NurPhoto/K. Ann Cote
ምስል Reuters/L. Millis
ምስል picture-alliance/Zuma Press/El Universal/V. Rosas

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW