1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

«አሜሪካ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ጠላት የላትም፤ ቋሚ ብሄራዊ ፍላጎት እንጂ!» ሄንሪ ኪሲንጀር

ሐሙስ፣ ኅዳር 20 2016

ሄንሪ ኪሲንጀር በ100 ዓመታቸው ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሃገራት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወቱት፣ ዲፕሎማትና የፖለቲካ ተመራማሪው ሄንሪ ኪሲንጀር በወታጣትነታቸው ከናዚ ጀርመን መዳፍ አምልጠው፣ በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ውስጥ እጅግ ተደማጭነት እና አወዛጋቢ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ለመሆን የበቁ ሰው ናቸው።

Dokumentation | Henry Kissinger - Geheimnisse einer Supermacht
ምስል ecomedia

ሔንሪ ኪሲንጀር በምን ይታወሳሉ?

This browser does not support the audio element.

የቀዝቅዛ ጦርነትን ውጥረት የማርገብና የአሜሪካ አለማቀፍ ዲፕሎማሲ መሐንዲስ የሚባሉት ሄንሪ ኪሲንጀር በ100 ዓመታቸው ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሃገራት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወቱት፣ ዲፕሎማትና የፖለቲካ ተመራማሪው ሄንሪ ኪሲንጀር በወታጣትነታቸው ከናዚ ጀርመን መዳፍ አምልጠው፣ በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ውስጥ እጅግ ተደማጭነት እና አወዛጋቢ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ለመሆን የበቁ ሰው ናቸው። በአንድ ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆነው የሠሩት ሄንሪ ኪሲንጀር በይበልጥ የሚታወቁት በምንድን ነው?

የዲፕሎማሲ አቀናባሪነት አሻራ

እ.ኤ.አ. ግንቦት 27 ቀን 1923 የተወለዱት የኪሲንጀር አሻራ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበረውና የማይጠፋ ነው። እንደ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ፣ በኋላም በፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን እና ጄራልድ ፎርድ ስር የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን የቀዝቃዛውን ጦርነት ዘመን ውስብስብ ክስተቶች በብቃት መርተው አልፈዋል። በ1973 ዓ/ም የፓሪስ የሰላም ስምምነት በማድረግ የቬትናምን ጦርነት ለማስቆም ላበረከቱት አስተዋፅዖ የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝተዋል።

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ታሪካዊ ግንኙነት እንዲከፈት ያደረጉት ሚስጥራዊ ተልእኮዋቸው የኪሲንጀርን ዲፕሎማሲያዊ ብቃት የበለጠ ግልፅ አድርጎ ያሳየ ነበር። በአሜሪካና በሶቪየት ህብረት መካከል መረጋጋትን እና ከውጥረት የነጻ የሆነ ግንኙነትን ለመፍጠር ያለመና የሃይል ተለዋዋጭነት ተግባራዊ ግምገማ ላይ የተመሰረተ የእውነተኛ ፖለቲካ አካሄደዋል።

 የመካከለኛው ምስራቅ

በመካከለኛው ምስራቅ የኪሲንጀር የተመላላሽ ዲፕሎማሲ በእስራኤል እና በአረብ ጎረቤቶቿ መካከል ከ1973ቱ የዮም ኪፑር ጦርነት በኋላ የሰላም ስምምነቶችን በመፈጸም ሁከት በነገሰበት አካባቢ ሰላም የማስፈን ብቃታቸውን አሳይተዋል።

 የቬትናም ሁነቶች

ያም ሆኖ የቬትናም ጦርነት በኪሲንጀር ማንነት ውስጥ የተወሳሰበ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ምዕራፍ ነው። በሰላም ስምምነቱ ውስጥ የተጫወቱት ሚና ጉልህ ቢሆንም፣ የጦርነቱ ሰቆቃና በአሜሪካውያን ህይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት እና ጉዳቱንም ተከትለው የመጡት፣ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ከዱክ ቶ ጋ መጋራትን ጨምሮ ያሉት ውዝግቦች ፣ በታሪካቸው ውስጥ አከራካሪ ጉዳዮች ሆነው አልፈዋል።

ኪሲንጀር በአፍሪቃ ቀንድ ያለውን ግንኙነት ሚዛናዊ ለማድረግ ከግብረገባዊ አመለካከት በነጻና ተጨባጭ ሁነቶችን ባማከለ መንገድ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፍልስፍና (Realpolitik) ፖሊሲን ተከተልዋልምስል Brendan Smialowski/AFP

  የፖለቲካ ተመራማሪ

የኪሲንጀር ተጽእኖ ከአሜሪካ አልፎ አለማቀፋዊ ይዘት ያለው ነው። ስልታዊ አስተሳሰባቸው እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ግንዛቤያቸው በአለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። “Diplomacy” እና “On China”ን ጨምሮ የጻፏቸው መጽሃፍት በአለም አቀፍ ጉዳዮች ጥናት ላይ የማይጠፋ አሻራን አስቀምጠዋል።

  ውስብስብ ዓለም አቀፍ ስብዕና

ይሁን እንጂ የኪሲንጀር ታሪክና አሻራ ከትችትና ከተቃውሞ የጸዳ አይደለም። በቺሊ፣ በካምቦዲያ እና በሌሎችም አካባቢዎች በድብቅ ኦፕሬሽኖች እና ጣልቃ ገብነቶች ላይ የተከሰቱ ውዝግቦች እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ውንጀላዎች ጋር ተዳምሮ በውጭ ፖሊሲ ውሳኔያቸው ሰብዓዊ፣ ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ ምህዳር ላይ ብዙ ተቃውሞና ክርክር ተነስቷል።

 ኪሲንጀርና በኢትዮጵያ

ልክ እንደሌላው ዓለም ሁሉ የኪሲንጀር ረጅም የዲፕሎማሲ እጅ፣ ኢትዮያንም መንካቱ አልቀረም። ኪሲንጀር ወቅት በኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ሚና ወሳኝ ነበር። በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅት፣ የደርግ መንግስት ስልጣን መያዝ እና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ረገጣ ስጋትጋ በተያያዘ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ውስብስብ ምዕራፍ ነበረው ። አሜሪካ በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራት ሲሆን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ኪሲንጀር በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ግንኙነት ሚዛናዊ ለማድረግ ከግብረገባዊ አመለካከት በነጻና ተጨባጭ ሁነቶችን ባማከለ መንገድ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፍልስፍና (Realpolitik) ፖሊሲን ተከተሉ። ሶቭየት ኅብረት በአካባቢው ሃገራት ላይ በነበራት ተጽእኖ ስጋት ለአሜሪካ የአቋም ለውጥ አንዱ መነሻ ነበር። የቀዝቃዛ ጦርነት ተለዋዋጭ በሆኑ ሁኔታዎች መካከል በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ግንኙነት ሚዛን ለመጠበቅ የኪሲንጀር እውነተኛ ፖለቲካ አካሄድ፣ የአሜሪካን አቋም ከነባራዊ ክስተቶች ጋር አያይዞ በመቅረጽ ረገድ ጉልህ ሚና ነበረው።

ኪሲንጀር ኪሲንጀር የዩናይትድ ስቴትስ ጥቅም ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፍልስፍና (Realpolitik) ፖሊሲን ይከተሉ ነበር ምስል Adam Berry/Getty Images

  ነባራዊ ሁነት ላይ ያተኮረ የፖለቲካ እሳቤ(Realpolitik)

ነባራዊ ሁነት ላይ የተመሰረተው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ሳቢያ ኪሲንጀር ተሞካሽተዋል፣ ተተችተዋልም። ይህ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ ከሥነ ምግባራዊ ፍፁምነት ይልቅ ያለውን ተግባራዊ እውነት ክግምት ውስጥ በማስገባት፣ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የዓለም ኃይል ተለዋዋጭነትን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ተቺዎች ይሄው ፍልስፍና የአሜሪካን ጥቅም ብቻ በማስከበር ላይ ያተኮረ፣ የሌሎችን ሃገራት መብትና ጥቅም ከግምት ዋስጥ ያላስገባነው ሲሉ ይከራከራሉ። ደጋፊዎቹ ግን የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ውስብስብ ጉዳዮችን ውጣውረድ በሚገባ በመሻገር ረገድ ውጤታማነቱን ይመሰክራሉ።

 የኪሲንጀር አሻራ

ዓለም የዚህን ቱባ የዲፕሎማሲ ሰው ኅልፈት በሚያስብበት በዚች ቅጽበት፣ የሄንሪ ኪሲንጀር የታሪክ ቅርስና ውርስ፣ በሃይልና በዲፕሎማሲ መሃከል የሚደረግ የተሰናሰለ፣ የተጋመደና አብሮ የተቃኘ ውስብስብ ጉዞ፣ እያንዳንዷን የአለማችንን ታሪክ የያዘች ገጽ ለመጻፍ መብቃቱን ማሳያ ነው። የኪሲንጀር Realpolitik ፖለቲካ ስልት ተፅእኖ አሁንም በአለምአቀፍ ፖለቲካ ግንኙነቶች ውስጥ አንዴ እያዘገመ፣ አንዴ እየፈጠነ፣ አንዴ ደግሞ እየተንገዳገደ መሄዱን ቀጥሏል። ይህም ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር በተግባራዊነት እና በግብረገባዊ አቀራረብ መካከል ያለውን የተወሳሰበ ግንኙነት ያስታውሰናል።

አበበ ፈለቀ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW