1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያስቀጠለችው ዕቀባ

ታሪኩ ኃይሉ
ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018

ዩናይትድ ስቴትስ ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ አስተላልፋ የነበረውን ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ባለበት እንዲቀጥል መወሰኗን አስታወቀች። ዶቼ ቬለ ስለ ጉዳዩ ያነጋገራቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ውሳኔውን የሚጠበቅና የሁለቱን አገሮች ስልታዊ ግንኙነት የማይነካ እንደሆነ ገልፀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሮቢዮ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሮቢዮ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Umit Bektas/REUTERS

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያስቀጠለችው ዕቀባ

This browser does not support the audio element.

 

ሰሞኑን ይፋ የተደረገውና የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔን የያዘው መግለጫ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እና ተያይዘው ያሉ ሁኔታዎች፣ ለዩናይትድስቴትስ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጪ ፖሊሲ አሳሳቢና የተለየ ስጋት የደቀኑ መሆኑን አመልክቷል። 

የአሜሪካ ሥጋት 

ሁኔታው በኢትዮጵያና በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላም፤ ደኅንነት እና መረጋጋት ስጋት ላይ የጣለ መሆኑን ጠቁሟል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስተዳደር ነበር በስሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቀድሞ ውሳኔውን ያስተላለፈው። በዛሬው ዕለት ተግባራዊነቱ ሊያበቃ የነበረውን የአስችኳይ ጊዜ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል መወሰኑን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንተኛ አቶ አያና ፈይሳ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተውናል። 

የፓለቲካ ተንታኝ አስተያየት 

«መጀመሪያ ላይ የተቀመጠውን ወደ ሰላማዊ ማዕቀፍ መሄጃ የሽግግር ፍትህና ሰላማዊ የዲሞክራሲያዊ ማዕቀፎች ውስጥ የማስገባት ሂደትን አልፈጸማችሁም ነው። ስለዚህ የተቀመጠውን ማዕቀብ ለማንሳት በቂ ሆኖ ስላልተገኘ ለአንድ ዓመት ተጨማሪ አራዝመውታል።»

በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትም ፈፅመዋል በተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረው፣ ይኸው ማዕቀብ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት፣ የዐማራ ክልል አስተዳደርና የህወሐት አባላትን የሚመለከት ነው።

«'ተጠባቂ ነበር»

ትአዛዛዙን የሚያስፈፅመው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሲሆን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱም እንዲተባበር ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህ የማዕቀብ ውሳኔ ያልተጠበቀ እንዳልነበር አቶ አያና ይናገራሉ። 

«'ውሳኔው ያልተጠበቃል አይደለም በእኔ ዕይታ፣ ምክንያቱም ይህ ማዕቀብ ተደርጎ አሜሪካ ለአፍሪቃ የነበረው በተለይ ከንግድ ጋር ተያይዞ፣ አጎዋ ለአፍሪቃ አሜሪካ የምትሰጠው ከቀረጥ ነፃ የሆነ የንግድ እድል አለና፣ ያንን ዕድል የሚጠቀሙ አገሮች የተወሰኑ የአሜሪካን ፖሊሲዎች ወይም አሜሪካ በሰብአዊ መብት ላይ፣ በሰላም ዙሪያ ያላትን ፍላጎት ለማስፈፀም የምትጠቀመበት ነውና በዛን ጊዜ፣ በጦርነቱ ጊዜ የነበረው ጫና አካል ነው።»

የውሳኔው መቀጠል በአገራቱ ግንኙነት ላይ የሚኖረው አንደምታ ምንድነው ተብለው የተጠየቁት የፓለቲካ ተንታኙ እንደሚከተለው መልሰዋል። 

«ይሄ እንግዲህ የተለያዩ ናቸው። እንደ አገር ያላቸው ፍላጎት በተለያየ አቅጣጫ ነው የሚቀመጠው። ቀጣናዊ በሆነው ነገር ላይ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ የሆነች አና ጠንካራ ኮር ስቴት ነው ብለው ስለሚያምኑ፣ በተለይ አሸባሪነት በሶማሊያ ውስጥ በሱዳን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በኤርትራ ውስጥ ያለውን አሸባሪነትና የባሕር ላይ ወንበዴዎችን መግታት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ትብብር አሁንም ጠንካራ ነው። በሌሎችም ነገሮች ላይም ተባብረው የሚሰሩበት ሂደት አለ።»

አሜሪካ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም በተደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና ስትጫወት መቆየቷ ይታወቃል። የውሳኔውን መቀጠል አስመልክቶ ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሻቸውን አላገኘንም። 

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW