1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሜሪካ ከአፍሪቃ ጋር ግንኙነትዋን ማጠናከር ትፈልጋለች

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 8 2015

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ እና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ላይ ወደ 50 የሚጠጉ የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል። ፕሬዚዳንቱ በዚህ መድረክ ላይ ሃገራቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ የወደፊት ተስፋ ቁርጠኝነትዋን ገልፀዋል።

USA Washington | US Africa Summit
የአሜሪካና አፍሪቃ ጉባኤምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

የአሜሪካና አፍሪቃ ጉባኤ አጠቃላይ ይዘት

This browser does not support the audio element.

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ እና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ላይ ወደ 50 የሚጠጉ የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል። ፕሬዚዳንቱ በዚህ መድረክ ላይ ሃገራቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ የወደፊት ተስፋ ቁርጠኝነትዋን ገልፀዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ከስምንት ዓመታት በኋላ ሁሉንም የአፍሪቃ መሪዎች በሚባል ደረጃ ለስብሰባ ወደ ሃገርዋ ስትጋብዝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነዉ። በቀድሞዉ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመነ የተካሄደዉ የአሜሪካና አፋሪቃ ጉባኤ በዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያውና ብቸኛው የመሪዎች ጉባዔ ነበር።   

በአሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ላይ ለሦስት ቀናት በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የተወያየባቸዉ ጉዳዮች እንደ አፍሪቃ አገሮች ሁሉ የተለያዩ ነበሩ። በጉባኤዉ ላይ ጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ዲጂቲል ቴክኖሎጂ እና የኅዋ ቴክኖሎጂ የተሰኙ ርዕሶች የተዳሱበት ነበር። የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነቶች በጉባኤዉ አጀንዳ ቀዳሚውን ስፍራ የያዙ ነበሩ። ግን የጉባኤዉ አላማ ይህ ብቻ አልነበረም።

የአሜሪካና አፍሪቃ ጉባኤምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

«በጉባዔዉ ላይ ለአፍሪቃ መሪዎች ለማስተላለፍ የተሞከረዉ፤ ዋሽንግተን ወደ አፍሪቃ ተመልሷል የሚለዉን መልዕክት ነዉ።  ዋሽንግተን ስለሚያሳስቧሁ ነገሮች ሁሉ ያስባል። ዋሽንግተን ችግራችሁን  እያዳመጠ  ነዉ። ይህን ጉዳይ ለመፍታት አዲስ አይነት አጋርነት ለመጀመር  ዝግጁ ነን፤ ለማለት እንደሆን ይሰማኛል።» ሲሉ ጉባዔው ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለ «DW» የተናገሩት የስትራቴጂና የዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል (CSIS) የአፍሪቃ ሰላም፣ ደህንነትና የአስተዳደር ጉዳዮች ተንታኝና አማካሪ ካሜሮን ሃድሰን ናቸዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የብሔራዊ የደህንነት ጥቅሞች ጉዳይ በአዲሱ የባይን አስተዳደር የአፍሪቃ ስልታዊ ቀረቤታ ላይም ተንጸባርቋል። ይሁን እና እንደ ካሜሮን ሃድሰን አገላለጽ የጉባኤዉ ማጠቃለያ  እንደተጠበቀዉ ዉጤት አልተንፀባረቀበትም።

«የሚያሳዝነው የአሜሪካ አፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ ቃል የተገባልንን ያህል ለአፍሪቃ የሚሆን አዲስ ራዕይ አላቀረበበትም» ሃድሰን ይህን የተናገሩት የመሪዎቹ ጉባዔ ሐሙስ እለት ሲጠናቀቅ ከዶቼ ቬሌ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነዉ።  

በትራምፕ አስተዳደር ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎች ሃገራት ይልቅ ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር ያደረገችዉ የኢኮኖሚ ግንኙነት ጥረት በእጅጉ የቀነሰ ነበር። ይህ ክፍተት ደግሞ የቻይናን ተፅዕኖ እና የቻይና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በአፍሪቃ አህጉር ላይ እንዲጠነክር አድርጎታል። ቻይና፣ በዚህ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባትነሳም በጉባኤዉ ትልቁን አፍራሽ ቦታ የያዘች ነበረች።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአፍሪቃ ዲፕሎማሲዉን በማጠናከር ብሎም በቁልፍ ዘርፎች ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ድጋፍ በማድረግ ተፅዕኖዋቸዉን መልሰው ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ይህ ሩጫ ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪቃ የተለያዩ ሀገሮች ውስጥ ያፈሰሰችውን መዋዕለ ንዋይ ለመቅደም ያለመ ሩጫ ነዉ። ቻይና ለአብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት ትልቋ የንግድ አጋር መሆንዋ ይታወቃል።

የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃን በአዲስ አስተሳሰብ መቅረብ አዎንታዊ ርምጃ ነዉ፤ የሚሉት በውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የአፍሪቃ ጥናት ባለሙያ ኤበኔዘር ኦባዳሬ ናቸዉ።የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ ጉባኤ

«ብዙ መልካም ፈቃድ፣ ለአፍሪቃ ብዙ አዎንታዊ አመለካከት መኖሩ እንደ አንድ የአህጉሪቱ ተንታኝ ጥሩ ነዉ ባይነኝ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ የወደፊት ተስፋ ቁርጠኛ ናት ሲሉ መስማት በጣም የሚያጽናናም  ነው። እናም ይህም የሦስት ቀናቱ ጉባዔ አጠቃላይ ቃና ይመስላል»

ይሁን እና "ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪቃ ዉስጥ የምታደርገዉ ነገር በአብዛኛው በየቀኑ የሚታይ የሚጨበጥ ነገር አይደለም። ማለትም ከአዉራ መንገድ ግንባታ፣ ከአውሮፕላን ማረፊያ ወይም ከድልድይ ጋር በሚመስል መልኩ አይታይም። ስለዚህም ይላሉ የፖለቲካ ተንቻኙ ስለዚህም በአፍሪቃ አህጉር ቻይና አሜሪካንን በእጥፍ በልጣ ትገኛለች። 

የአሜሪካና አፍሪቃ ጉባኤምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ዩናይትድ ስቴትስ በዋሽንግተኑ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የመዋዕለ ንዋይ እና የንግድ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ለየት ያለ አቀራረብ ለማድረግም ሞክራለች። ፕሬዚዳንት ባይደን ለአፍሪቃ ተወካዮች የጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ማዕድ ከሆነዉ ከቡድን  20 አገራት ጋር ቋሚ ቦታ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዉ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ከአፍሪቃ አህጉር ከመጡ  ወደ 50 ለሚጠጉ የሀገር መሪዎች ፊት ለፊት ቆመዉ ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ ያላትን ቁርጠኝነት ደግመው በመናገር ቃል ገብተዋል።

«ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በጋራ ዴሞክራሲን እና መላው ህዝባችንን አንድ በሚያደርገው ዋና ዋና እሴቶችን ለማጠናከር እየሰራን ነው። በተለይ ደግሞ የወጣቶች ነፃነትን፣ እድልን፣ ግልፅነትን እና መልካም አስተዳደር ላይ እየሰራን ነዉ።»  

አሜሪካ ለአፍሪቃ ትልቋ የሰብአዊ ርዳታ ለጋሽ ሃገር ናት። ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በአፍሪቃ ምርጫና መልካም አስተዳደርን ለመደገፍ አዲስ የ165 ሚሊዮን ዶላር ማዕቀፍ ይፋ አድርገዋል። የአፍሪቃ ሕብረት በቡድን 20 ቋሚ አባል ለመሆን ለሚያደርገዉ ድጋፍ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል። የአፍሪቃ ሰላም፣ ደህንነትና የአስተዳደር ጉዳዮች ተንታኝና አማካሪ ካሜሮን ሃድሰን እነዚህ ቃላቶች ለዩናይትድ ስቴትስና ለአፍሪቃ ግልፅ ራዕይ አያቀርቡም ብለው ያምናሉ። ሃድሰን እንደሚሉት ይህ የባይደን ቃል አሜሪካ ለአፍሪቃ ያላትን ራዕይ በግልፅ አስቀምጧል የሚል እምነት የላቸዉም።  

«ፕሬዚዳንቱ የተነገሩት አዲስ እና ልዩ ትርጉም ያላቸው አይደሉም። ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት በመሰረቱ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የየዕለት ስራን ነው»የአፍሪቃ መሪዎች የተሳተፉበት የአፍሪቃ አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ

በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ 50 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ለንግድ፣ ለጤናና ለደኅንነት ድጋፍ ለማዋጣት አቅዳለች ። የአፍሪቃ ጥናት ባለሙያዉ ኦባዳሬ ባንጻሩ ይህ ቃል ኪዳን አዎንታዊ ሆኖ አግኝተዉታል። 

የአፍሪቃ መሪዎች በጉባዔው ላይ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለመተሳሰር የሚቀርቡ አዳዲስ አጋጣሚዎችን በብሩህ አመለካከት ነዉ የተቀበሉት። ከዚህ ሌላ ይላሉ በዋሽንግተን የተካሄደዉ የመሪዎች ጉባዔ ዩናይትድ ስቴትስ ለዓመታት ለሰብአዊ ርዳታ ያዋጣችው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት የሚያስችል ነው። ይሁንና ይህ ለአፍሪቃ ሃገራት በቂ እንዳልሆነ እምነት አለኝ። 

«እርዳታን ለመጠየቅ ወደ ዋሽንግተን አልመጡም። የመጡት በጠረጴዛው ዙርያ ተቀምጠዉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና ዉሳኔዎች ላይ ለመድረስ ነዉ።  የመጡት በእኩል እንዲታዩ እና እኩል ክብርን እንዲያገኙ እንጂ ወደታች እየታዩ እንዲነገራቸዉ ትእዛዝ እንዲተላለፍላቸዉም አይደለም።  ጉባኤዉ ላይ የተገኙት የርዳታ በጀታቸዉ ሲጨምር ለማየት አይደለም። ስለዚህ ዋሽንግተኑ ጉባኤ ጥያቄዎቻቸዉን የመለሰዉ በግማሹ ነዉ። »

የአሜሪካና አፍሪቃ ጉባኤምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ከዚህ በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለት ዓመት በኋላ በምታካሂደዉ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ ለድጋሚ ምርጫ እየተዘጋጁ በመሆናቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ አስተማማኝ አጋር ሆና መቀጠልዋን ማመን እንደሚከብዳቸዉ ካሜሮን ሃድሰን ተናግረዋል። ስለዚህም በአሁን ወቅት ያለው የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር እና አዲሱ የአሜሪካ አፍሪቃ ስልታዊ ግንኙነት በሁለት ዓመት ውስጥ ዳግመኛ ላለመለወጡ ዋስትና ለመስጠት የሚችል ምንም ነገር የለም። 

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW