አሜሪካ የኤርትራን ማዕቀብ ለማንሳት ማጤኗ ለኢትዮጵያ በረከት ወይስ መዘዝ?
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 28 2018
አሜሪካ በቀይ ባሕር ዳርቻ ቁልፍ ቦታ ላይ በምትገኘው በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ልታነሳ መሆኗን የሚያመለክት የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰነድ ስለማሳየቱ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የአሜሪካ የቆየው የኤርትራ ማዕቀቦች ማንሳት ለአገሪቱ ይዞላት የሚመጣው በረከት እና በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ምን ያስከትል ይሆን፤ ለሚለው ጥያቄ ተንታኞች በተለያዩ መንገዱች ይተነትኑታል።
የማዕቀቡ መነሳት እና ወቅታዊው የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት
እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ አሜሪካ ኤርትራ ላይ ከዚህ በፊት የጣለቻቸውን ማዕቀቦች አሁን ለማንሳት ስለማጠኗ የአሜሪካ መንግስት የውስጥ ሰነዶች አሳይተዋል፡፡ ዋሽንግተን ከአሥመራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ውጥን የያዘችው ጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ትገባ ይሆን በሚል የዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታውን በስጋት በሚመለከትበት ባሁን ወቅት ነው፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በጠላትነት የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸው ተሻሽሎ ቢቆይም፤ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ከተፈረም በኋላ ግን በአገራቱ መካከል የነበረው ወዳጅነት ተቀዛቅዞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በይፋ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትን መናገር ከጀመሩ በኋላ ወደ ውጥረት ተሸጋግሯል።
የማዕቀቡ መነሳት ለምን አሁን?
እንደ ተንታኞች ገለጻ ግን አሁን አሜሪካ ኤርትራ ጋር ለመቀራረብ የጀመረችው መንገድ ቢያንስ በምስራቅ አፍሪቃ ላይ ያንዣበበውን የጦርነት ዳመና ይገታል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካን በቅርበት ተከታትለው ትንተና የሚሰጡት አብዱራሃማን ሰይድ፤ አዲሱ የአሜሪካ መንግስት ውጥን ለቀጣናው ሰላም በጎ ነገር ይዞ ሊመጣ ቢችልም ለኢትዮጵያ ግን መዘዝ የሚሆንበት እድልም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ የኤርትራ ማዕቀቦችን የማንሳት ውጥኗ ገቢራዊ ከሆነ "በኢትዮጵያ በኩል ሲደረግ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄን ሊገታው ይችላል፤ ይህም ኢትዮጵያ እና እንደ ኢምረትስ ያሉ ሌሎች የአሜሪካ ተባባሪ አገራት ከአሜሪካ ፍላጎት ጋር ሊጋጩ ስለማይችሉ ነው” በማለት፤ ነገር ግን የአሜሪካ ወደ ቀጣናው መምጣት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሊነሳ የሚችለውን ጦርነት በማስቀረት አዎንታዊ ሚናም ሊጫወት ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡
ኤርትራ በአሜሪካ አዎንታዊነት ካገኘች በቀይ ባህር አከባቢ ጥሩ ሚና የማግኘት እድል ይኖራታል የሚሉት ተንታኙ፤ ይህም ምንም እንኳን ለኤርትራውያን የተለየ ነገር ያስገኝላቸዋል ባይባልም፤ ለኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ግን እፎይታን ሊያስገንላቸው እንደሚችል በምልከታቸው አብራርተዋል፡፡
የአሜሪካ የዴሞክራሲ መርኅ እና የብሔራዊ ጥቅም ግጭት
አሜሪካ ከ30 ዓመታት በፊት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ በመጣል ከዓለም የተገለለች አገር ስታደርጋት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ምርጫ እንኳ በማይደረግባት ኤርትራ የአንድ ሰው አገዛዝን በመቃወም እንጂ ኤርትራ እንደ ኃያላኑ አገራት የአሜሪካ ጥቅም ላይ አደጋ በመደቀኗ አልነበረም፡፡
የዓለም አቀፍ ሕግ ተንታኝ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ እንደሚሉት፦ «የሰው ልጅ መብት ጥያቄ የለም ዛሬ በዓለም ላይ ።» የፕሬዚደንትድ ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርም ስለ ኤርትራ ጉዳይ የሚያሳስበውም ከዚህ አኳያ አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ኤርትራ ማዕቀብ ተነሳላትም አልተነሳላትም መሣሪያን ከውጪ አስገብታ ለጎረቤት አገራት ስጋት ትሆናለች የሚል ስጋት እንደማይታያቸው የገለጹት የዓለማቀፍ ሕግ ተንታኙ፤ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከወደብ ባለቤትነት ጋር ተያይዞ ከኤርትራ ጋር መቃቃር ውስጥ የገባችበት ጉዳይም ተመራጭ የሚሆነው በሰላምና በድርድር ሲፈታ ነው ብለዋል፡፡ ኤርትራ ማዕቀቦች ተነስቶላት አገራት ስለ ኤርትራ መልካም ምልከታ እያሳደሩ መምጣታቸውም ከአለመረጋጋት ይልቅ ሰላምና መረጋጋትን ወደ ቀጣናው የሚመጣው እንደሆነ ነው በአስተያየታቸው የገለጹት፡፡
ሰሞነኛው የሮይተርስ ዘገባ እንዳለውም ኢትዮጵያ የባሕር በር በኃይል ለማግኘት ውጥን ካላት ያንን ውሳኔ አሜሪካ እንደምትቃወም ሰነዱ ያሳያል፡፡ ይህንኑም ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንዳሳወቀችም ነው የተጠቆመው። አሁን ደግሞ አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦችን የምታነሳ ከሆነ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ልትወስድ የምትችለውን የትኛውንም ዓይነት የኃይል ርምጃ እንደሚያስተጓጉልም በብዙዎች ታምኗል፡፡
የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ለኤርትራ ይዞላት የመታው በረከት
አሜሪካ ከኢራን ጋር በገባችው ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በመዘጋቱ ከእስያ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ለሚደረገው የባሕር ላይ ንግድ በቀይ ባሕር ላይ የሚኖርን ቁጥጥር አስፈላጊነትን አጉልቶታል።
እንደ ተንታኞች አስተያየትም አሜሪካ ማዕቀቦችን ከኤርትራ ላይ ለማንሳት የወጠነችውም በቀጣነው ለንግድ መስመር አማራጭ ፍለጋና ደህንነቱን ለማስጠበቅ ነው፡፡ አብዱራሃማ ሰይድ እንዳሉት፦ "ባሁን ጊዜ በኢራን ጦርነት ምክንያት በሆርሙዝ የመርከቦች መተላለፊያ መዘጋቱ ሌላው ተመሳሳይ ጥቅም የሚሰጠው በደቡባዊ ቀይ ባህር ወሰን ላይ የሚገኘው የባቤል-መንደብ መተላላፊያ ላይ የኢራን ሸሪክ የሆነው የየመኑ ሑቲ ጥቃት በመፈጸም ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳያስከትል የተያዘው ውጥን ኤርትራን ተፈላጊነት አምጥቷል፡፡”
እንደ የዓለም ሕግ አዋቂው አቶ ባይሳ ዋቅዎያ አስተያየትም፦ "የሆርሙዝ ሰርጥ ሲዘጋ የተሻለ አማራጭ ይገኛል በሚል ቀይ ባህር ላይ ሌላ አማራጭ መፈለግ፤ ለዚህም የኤርትራ ማዕቀብ ለማንሳት መወሰን አያስገርምም” በማለት አሁን አሁን መንግስታት ማዕቀቦችን ለመጣልም ሆነ ለማንሳት መለኪያው መርህ (የተቀመጠ የዓለም ህግ መስፈርት) ሳይሆን ትቅም ብቻ ነው ብለዋል፡፡ "ኤርትራ ከትቅም አኳያ በምንም መልኩ የአሜሪካን ጥቅም ያማትነካ ናት፤ ዴሞክራሲ ከሆነ ደግሞ አሜሪካም ትቷለች” በማለት ማዕቀቡም ብነሳ ሊያስገርም እንደማይገባ ተንትነዋል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት ዎል ስትሪት ጆርናል የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ አገራቸው ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ማቀዷን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር። በዚህም አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን ለማሻሻል የሚያስችሉ ርምጃዎችን ለመውሰድ ግምገማ ላይ መሆኑን ጋዜጣው ፍንጭ ሰጥቷልም።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ በነበራት ተሳትፎ በኤርትራ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ማዕቀባ መጣላቸውም ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ