1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አምስት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት መመሥረታቸውን ገለጹ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ መስከረም 8 2018

መኢአድ፣ እናት፣ ኢሕአፓ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ቅንጅት መመሥረታቸውን አስታወቁ። ፓርቲዎቹ ቅንጅት የመሠረቱት ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታካሒዳለች ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። "ሰብሰብ ብሎ አቅም መፍጠር" የቅንጅቱ አንድ ዓላማ ነው ተብሏል።

በምርጫ ወቅት የድምጽ አሰጣጥ
ኢትዮጵያ በ2018 ምርጫ ታካሒዳለች ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ተቃዋሚዎች ጥምረቶች እየመሠረቱ ይገኛሉምስል፦ Negasa Desalegn/DW

አምስት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት መመሥረታቸውን ገለጹ

This browser does not support the audio element.

"ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በትብብር በጋራ" ሲሠሩ መቆየታቸውን ያስታወቁ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት መመሥረታቸውን ለዶቼ ቬለ ገለፁ። "ትብብራችንን ሕጋዊ ቅርጽ" አስይዘን አጠናቀናል ያሉት ፓርቲዎቹ የቅንጅቱን ስያሜ እና አርማ የፊታችን ቅዳሜ ይፋ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።

70 የደረሰውን የፖለቲካ ፓቲዎች ቁጥር እንዲቀንስ በማድረግ "ሰብሰብ ብሎ አቅም መፍጠር" አላማቸን ነው ያሉት ፓርቲዎች መኢአድ፣ እናት፣ ኢሕአፓ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት መመራቷ በርካታ የመራጭ ድምፅ እንዲባክን ማድረጉን የጠቀሱ አንድ የሕግ ባለሙያ "ቅንጅት" ይህንን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ገልፀው "ውህደት" በላቀ ለሕዝብ ጥቅም ተመራጭ ነው ብለዋል። ያንን ለማድረግ ግን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የግድ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ቅንጅት የመሠረቱት ምን ለማሳካት ነው?

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ "ቅንጅት መሥርተን ለመንቀሳቀስ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን" ብለዋል።

ቅንጅቱን ከመሠረቱት 5ቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ሰብሰብ ብሎ አቅም መፍጠር፣ ለሕዝብ መልሶ አደጋ ፈጥሯል ያሉትና የበዛውን የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥር መቀነስ ብሎም እውነተኛ ትግል እንዲኖር ማስቻል የመቀናጀታቸው አላማ ነው።

"ሰብሰብ እያሉ [የፖለቲካ ድርጅቶች] ማየት አቅምን ይፈጥራል። ሁለተኛው ወደ 70 እና በላይ ፓርቲዎች ደርሷል በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ ትግል እንንቀሳቀሳለን ብለው ሰርትፊኬት ያገኙ። ሰርትፊኬት ባገኘንበት ልክ ሳይሆን እየጮህን ያለነው እንደገና መልሶ ሕዝቡን የሚበድል ነገር ነው [መብዛታቸው]።"

ቅንጅት ለመመስረት መስፈርት ናቸው የተባሉ ነጥቦች

ፓርቲዎቹ የቅንጅቱን ስያሜ እና አርማ የፊታችን ቅዳሜ ይፋ እንደሚያደርጉ፣ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸው ደግሞ ወደፊት እንደሚገለጽ ተጠቅሷል። ሌሎች ፓርቲዎችም ይቀላቀሉናል ብለን እናምናለን ያሉት አቶ ጌትነት የመቀናጀታቸው መስፈርት እና መርህ ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

"የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መቀበል፣ ከታሪኳ ጋር ብዙ ጠብ ውስጥ አለመግባት፣ እውነትና እና መርህ ላይ የተመሠረተ ተቃውሞ" ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ፓርቲዎች ቅንጅት መመስረታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሁናቴ እንዴት ይገልፁ ይመለከቱታል የሚለውምም መሰባሰባቸውን ለመገንዘብ ይረዳል በሚል ጠይቀናቸው አቶ ጌትነት ወርቁ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥምረት የመሠረቱት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ናቸው። ምስል፦ Megabe Beluiey Abrham Haimanot/DW

"ሀገሩ አደጋ ላይ ነው የሚለው ትልቅ የፖለቲካ መዳረሻ ነው። ለቅንጅቱም ይህ አንድ መነሻ ነው።"

የምርጫ ሕጉ ስለ ቅንጅት እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቶች ምን ይላል?

ኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ምዕራፍ ስድስት ላይ ስለ ለፖለቲካ ፓርቲዎች መዋሀድ፣ ግንባር መፍጠር፣ መቀናጀት እና መተካት በግልጽ አስቀምጧል።

አዋጁ "ለመቀናጀት የፈለጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን የጠቅላላ ምርጫ ወይም የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ከሁለት ወራት በፊት በጽሑፍ ለ [ምርጫ] ቦርዱ ማቅረብ አለባቸው" ይላል፡፡ ቅንጅት ሲፈጠር "እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነቱን እንደያዘ ይቀጥላል" በሚልም ተደንግጓል። "ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተወሰነ ጊዜ እና በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀናጅተው እንደ ሁኔታው በአገር አቀፍ ወይም በክልል ደረጃ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ" በሚልም በዚህ አዋጅ ላይ ሰፍሯል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ እና የሕግ ባለሙያ ምን ይላሉ?

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት አቶ አሮን ደጎል ቅንጅት መፍጠር የሚባክንን ድምፅ ለማስቀረት ቢጠቅምም ውህደት የበለጠ ጠቃሚ መሆኑን በማሳያ ጭምር አስገንዝበዋል።

"አንዱ ፓርቲ ያገኘውን 15 [የመራጭ ድምፅ]፣ ሌላኛው ፓርቲ ያገኘውን 15 ይዘው በተናጠል ከሚገቡ [ፓርላማ] ሦስቱም አንድ ፓርቲ ሆነው ያላቸውን ድምፅ ይዘው ሲገቡ ለሕዝቡ ይጠቅማል። ቢያንስ ድምፁ አልባከነም።" እንደ የሕግ ባለሙያው ዘላቂው መፍትሔ ግን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በማድረግ የምርጫ ሥርዓቱን መቀየሩ ነው።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ "የምክር ቤቱ [የሕዝብ ተወካዮች] አባላት ቁጥር የሕዝብ ብዛትን እና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቁጥር መሠረት በማድረግ ከ 550 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች ከ20 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል" ሲል ደንጓል ያሉት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ምኁሩ አቶ አሮን ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት "አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ የምክር ቤት ወንበር የሚይዝበት ብቻ ሳይሆን መንግሥትም የሚመሠርትበት" መሆኑ በኢትዮጵያ ምርጫ ውስጥ የበርካታ ሰዎች ድምፅ ባክኖ እንዲቀር ማድረጉን አመልክተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW