1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አምስት ፋብሪካዎች በ2016 ያመረቱት ስኳር ከኢትዮጵያ ፍላጎት 10% ገደማ ብቻ ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016

ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫ፣ ከሰም እና ጣና በለስ ፋብሪካዎች በ2016 ያመረቱት 124,097 ቶን ስኳር እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዐስታውቋል። ይኸ የሚሸፍነው የኢትዮጵያን የስኳር ዓመታዊ ፍላጎት 10% ብቻ ነው። መንግሥት እስከ ጥር ስምንት ስኳር ፋብሪካዎችን በመሸጥ የፈሰሰባቸውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር መመለስ አቅዷል።

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ
በምስሉ የሚታየው ጣና በለስ፣ ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫ እና ከሰም ፋብሪካዎች በ2016 ያመረቱት 124,097 ቶን ስኳር እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። ምስል Xinhua/picture alliance

አምስት ፋብሪካዎች በ2016 ያመረቱት ስኳር ከኢትዮጵያ ፍላጎት 10% ገደማ ብቻ ነው

This browser does not support the audio element.

በአዲስ አበባ ከጀሞ ወደ መካኒሳ በሚወስደው መንገድ ላይ ቡና እና ሻይ በመሸጥ የምትተዳደረው ወጣት ደንበኞቿን እያስተናገደች ነው። ዕድሜዋ በ20ዎቹ መጀመሪያ የሚገኘው ወጣት አንድ ስኒ ቡና በ20 ብር ተሸጣለች። ከወጣቷ ዘንድ ቀሽር ፉት ያሉ 25 ብር ይከፍላሉ። ወጣቷ እንደምትለው አንድ “ኪሎ ስኳር 120 ብር ነበር። አሁን 130 ብር ገብቷል።”

ወጣቷ የስኳር ዋጋ ከፍ ቢልም በምትሸጠው ቡናም ሆነ ሻይ ላይ የዋጋ ጭማሪ አላደረገችም። “ደንበኞቼን አጣለሁ” የሚል ሥጋት አላት። አንዲት የአዲስ አበባ ነዋሪ ከ110 እስከ 120 ብር ይሸጥ የነበረው ኪሎ ስኳር “ከአንድ ወር ወዲህ አንዳንድ ቦታ 125 አልፎ አልፎም 130 ብር ነው የሚሸጠው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ ከችርቻሮ ነጋዴዎች አንድ ኪሎ ስኳር ከ125 ብር እስከ 130 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ለመገንዘብ ችሏል። በገበያው በምግብ ሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ አዲስ አበቤዎችን ለሥጋት የዳረገ ነው። “የአዲስ አበባ ሕዝብ ዳቦ እና ሻይ ሳይቀምስ አይወጣም” የሚሉ የከተማዋ ሌላ ነዋሪ የዋጋ ጭማሪው “በጣም መጥፎ ነው” የሚል ሥጋት አላቸው።

ስኳር እና የምግብ ማብሰያ ዘይትን በመሳሰሉ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ የበለጠ ዕድገት ያሳየው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ ለሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ብድር እና ርዳታ ለማግኘት በወሰዳቸው ርምጃዎች ሳቢያ ነው።

በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ ሲደረግ የብር የመግዛት አቅም ተዳክሞ ከውጪ የሚገቡ ሸቀጦች ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ምርቶች ጭምር የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። ቀድሞም የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ስኳር እና የምግብ ማብሰያ ዘይት በመሳሰሉ ሸቀጦች ረገድ የሀገሪቱን ፍላጎት መሙላት አልተሳካላቸውም።

በስኳር የመሸጫ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ ቡና እና ሻይ አፍልተው በሚሸጡ ኢትዮጵያውያን ላይ ብርቱ ጫና ያሳደረ ነው። ምስል DW/James Jeffrey

ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫ፣ ከሰም እና ጣና በለስ ፋብሪካዎች በ2016 ማምረት የቻሉት 124,097 ቶን ስኳር እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባለፈው ሣምንት ዐስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኸርነስት ኤንድ ያንግ በተባለ አማካሪ ኩባንያ ያሠራው የገበያ ጥናት የሀገሪቱ የስኳር ፍላጎት በጎርጎሮሳዊው 2020/2021 መጨረሻ 1.2 ሚሊዮን ቶን 12,000,000 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚገመት ያሳያል።

ከሰነዱ ጋር ሲነጻጸር አምስቱ ፋብሪካዎች በ2016 ያመረቱት የኢትዮጵያን የስኳር ዓመታዊ ፍላጎት 10 በመቶ ብቻ የሚሸፍን ነው። በጥናቱ መሠረት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት በመጪዎቹ አምስት ገደማ ዓመታት በ3% ዕድገት ዐሳይቶ ወደ 1.7 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ከዐሥር በላይ ፋብሪካዎች ቢኖሯትም የገበያውን ፍላጎት ለመሙላት ሕንድ፣ ብራዚል እና ታይላንድን ከመሳሰሉ ሀገሮች ስኳር ስትሸምት ቆይታለች። የቀድሞው የስኳር ኮርፖሬሽን በሕግ ከፈረሰ በኋላ አምስቱ ፋብሪካዎች “ራሳቸውን ችለው” ተቋቁመዋል። ፋብሪካዎቹ የራሳቸው የሥራ አመራር ቦርድ አላቸው።

የኢትዮጵያን የስኳር ኢንዱስትሪ በቅርበት የሚያውቁት የምኅንድስና ባለሙያው አቶ ለማ ጉርሙ መተሐራ፣ ወንጂ ሸዋ እና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች በመንግሥት “የማይሸጡ” ተብለው ከተመደቡ መካከል እንደሆኑ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የምኅንድስና ባለሙያው መንግሥት ፋብሪካዎቹ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ በመፍቀድ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

መራራ ግጭት ያጠላበት የጣፋጩ ስኳር ኢንዱስትሪ

የኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎችን እና ሠራተኞቻቸውን የሚፈታተን ብርቱ ችግር ነው። ባለፈው መጋቢት በታጣቂዎች ታግተው የማስለቀቂያ ቤዛ የተጠየቀባቸው ስድስት የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ተገድለዋል።

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሚገኘው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በግንቦት 2015 ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ በደረሰበት ጥቃት ለወራት ሥራ ለማቆም ተገድዶ ነበር። የፋብሪካው ኃላፊዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በጥቃቱ አራት መቶ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ኪሳራ ደርሶበት ነበር።

የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በ2015 በተፈጸመ ጥቃት 400 ሚሊዮን ብር የሚገመት ውድመት እንደደረሰበት ኃላፊዎቹ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Negassa Dessalegn/DW

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ባልደረባ በአካባቢው በተከሰተ የፀጥታ ሥጋት ሳቢያ “አብዛኛው ሠራተኛ ለቋል፤ ባለሙያ ለቋል” ሲሉ ይናገራሉ። “አሁን ያለው የአካባቢው ሠራተኛ ነው” የሚሉት የፋብሪካው ባልደረባ የፀጥታ ሁኔታው የመሻሻል አዝማሚያ ቢያሳይም “የወደፊቱ እንዴት ይሔዳል [የሚለው] የእኔም ጥያቄ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።  

ስኳር እና ዕዳ

ኢሕአዴግ ይመራው የነበረው መንግሥት የስኳር ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የተከተለው ስልት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዕዳ አሸክሟት አልፏል። በዕቅዱ መሠረት በመከላከያ ሠራዊት ሥር ይገኝ በነበረው ብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሥራ ተቋራጭነት ግዙፍ ብቻ ሳይሆን በርካታ ፋብሪካዎች የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎበት የነበረው የኢትዮጵያ የስኳር ኮርፖሬሽን በሕግ ከፈረሰ አንድ ዓመት ገደማ ሆነው። የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ዕዳ ከነበረባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ ነበር።

የመንግሥት የስኳር ፋብሪካዎችን በብዛት የመገንባት ዕቅድ ሲከሽፍ ሁለቱ ኮርፖሬሽኖች ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያተረፉት ከፍተኛ ኪሳራ ነው። ለስኳር ማምረቻው ዘርፍ ከ2003 - 2010 ባሉት ዓመታት ብቻ 98 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።

የቀድሞው የስኳር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች “የፊስካል እና የዕዳ ሥጋት የጋረጡ” ናቸው። በተለይ ኪሳራ ውስጥ የተዘፈቁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በጎርጎሮሳዊው 2022/23 መጨረሻ መንግሥት በብር ከተበደረው ዕዳ 90 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው በቅርቡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል።

ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) 9.3 በመቶ የሚሆን ብድራቸው ወደ ዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ቢዘዋወርም ስኳር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሥራ ክንውናቸው መሻሻል አላሳዩም።

በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ የተገነባው ጣና በለስ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት የኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች በገንዘብ ካስከተሉት ኪሳራ ባሻገር የአካባቢውን ነባር ማኅበረሰቦች በማፈናቀል ብርቱ ሰብአዊ ቀውስ ፈጥረዋል የሚል ወቀሳ ይቀርብባቸዋል።

በኦሞ ሸለቆ የሚገነቡ የስኳር ፋብሪካዎች የአካባቢውን ነባር ማኅበረሰቦች አፈናቅለዋል የሚል ትችት ይሰነዘርባቸዋል። ምስል Ethiopian Sugar Corporation

የስኳር ኮርፖሬሽን ከፈረሰ በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ በ2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ሦስት እንዲሁም የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካዎችን ያስተዳድራል። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት፣ ተንዳሆ እና ወልቃይት የስኳር ፕሮጀክቶች “በአመዛኙ የንግድ ተቋም ሆኖ” የተመሠረተው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሥር የሚገኙ ናቸው።

ፋብሪካዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ዶይቼ ቬለ አቶ ወዮ ሮባ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከሚመሩት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልሰመረም።

ጥርን የሚጠብቀው የስኳር ፋብሪካዎች ፕራይቬታይዜሽን

መንግሥት በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የሚገኙትን የኩራዝ ፋብሪካዎች፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ፣ እና ተንዳሖ ፋብሪካዎች ለመሸጥ ጥረት ማድረግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ስምንቱን የስኳር ፋብሪካዎች፣ የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች እና የኢታኖል ማምረቻዎች በተናጠል ወይም በጠቅላላ ለመግዛት ያቀዱ ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ መንግሥት ጥሪ ያቀረበው በ2011 ነበር።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሖልዲንግስ እና የገንዘብ ሚኒስቴር በሕዳር 2015 በጨረታው መሳተፍ የሚሹ ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። ሁለቱ ተቋማት ባለፈው መስከረም 2016 ከተጫራቾች የቴክኒክ እና የፋይናንስ ሰነዶች መቀበላቸውን አረጋግጠው ግምገማ መጀመሩን አስታውቀዋል። ይሁንና ሒደቱ በተጠበቀው ፍጥነት አልተጓዘም።

ሒደቱን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ለማ “የተሳታፊዎቹ ቁጥር በጣም የተወሰነ ነው። ሦስት ኩባንያዎች መሳተፋቸውን ነው የሰማንው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ለማ ጨረታው እንደ አዲስ ይጀመራል ብለው ይጠብቃሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮ-ቴሌኮም የድርሻ በመሸጥ፣ ሁለተኛ የቴሌኮም ፈቃድ በመስጠት እና ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል በማዘዋወር በጎርጎሮሳዊው 2025/26 በአጠቃላይ 650 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል ተብሎ ይጠበቃልምስል Eshete Bekele/DW

ዶይቼ ቬለ በጨረታው ሒደት ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሖልዲንግስ ተጨማሪ ማብሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባቀረበው ሰነድ ዘጠኝ የስኳር ፋብሪካዎችን በሽያጭ ወደ ግል ለማዘዋወር ሒደቱን እንደገና እንዳስጀመረ አስታውቋል። መንግሥት የስኳር ፋብሪካዎቹን ሲሸጥ በዘርፉ የግል መዋዕለ-ንዋይ መሳብ እና መንግሥት ፈሰስ ያደረገውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የመመለስ ዕቅድ አለው።

ለሽያጭ የቀረቡ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት “ብዙ ብር ነው የፈሰሰው። ሐብቱ ግን መሬት ላይ በጊዜ ብዛት ያረጃል፣ ይበላሻል። ብዙ ብዙ ነገር ስለሚኖር እሱን ነገር ማሻሻል የሚቻልበትን ሁኔታ ከመንግሥት ይጠበቃል” ሲሉ አቶ ለማ ጉርሙ አስረድተዋል።

ስምንቱን ፋብሪካዎች የመግዛት ፍላጎት ያሳዩ የውጪ ኩባንያዎች በጨረታው የመጀመሪያ ሒደት በቅድሚያ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በሥራቸው የሚያገኙትን ትርፍ ወደ ሀገራቸው የሚወስዱበት መንገድ ይገኝበታል። ሀገሪቱ ባለባት የውጪ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ገቢያቸውንም ሆነ ትርፋቸውን ከኢትዮጵያ ወደ ሀገራቸው መውሰድ ተቸግረው ቆይተዋል።

“እኛም ተሳትፈን ስለነበር ጨረታ ሒደት ላይ ማብራሪያ ሲሰጥ ዋናው ጥያቄያቸው ይኸ ነበር” የሚሉት አቶ ለማ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የገንዘብ ሚኒስቴር “በሒደት ይመለሳል” የሚል ምላሽ ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል። የውጪ ኩባንያዎች “ገንዘብ ማምጣቱን፤ መስራቱን ይፈልጋሉ። ነገር ግን የሚያገኙትን ገቢ መልሰው መውሰድ ይፈልጋሉ። እሱ ነገር ተፈቷል ብዬ አስባለሁ” የሚሉት አቶ ለማ “ለማገኛቸው ብዙዎቹ የውጪ ኢንቨስተሮች በጣም የሚያነቃቃ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

መንግሥት የኢትዮ-ቴሌኮምን ድርሻ በመሸጥ፣ ሁለተኛ የቴሌኮም ፈቃድ በመስጠት እና ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል በማዘዋወር በጎርጎሮሳዊው 2025/26 በአጠቃላይ 650 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰነድ ያሳያል።

ሥዩም ጌቱ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽዖ አበርክቷል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW