1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሞት ቅጣት ተባብሶ መቀጠሉን ይፋ አደረገ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 12 2015

በመላው ዓለም የሞት ቅጣት መጨመሩን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አመለከተ። ድርጅቱ ከአንድ ቀን በፊት ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2022 የተፈጸመው የሞት ቅጣት ከቀዳሚው ዓመት በ53 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል። ለዚህም በተለይ የሞት ቅጣቱ ኢራን እና ሳውድ አረቢያ ውስጥ በብዛት ተግባራዊ በመደረጉ መሆኑ ነው ዘገባው ያመለከተው።

Logo amnesty international

«የሞት ቅጣት ጨምሯል»

This browser does not support the audio element.

የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ እንደሚለው በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ከተፈጸመው የሞት ቅጣት አብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ነው። በተጠቀሰው አካባቢ የተፈጸመውም በዓመቱ ከተመዘገበው የሞት ቅጣት 70 በመቶውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ አካባቢ ቁጥሩ እንደበዛ ያደረገው ደግሞ በተለይ ኢራን የፈጸመችው የሞት ቅጣት ቁጥሩ ከኻቻምናው ከእጥፍ በላይ በመሆኑ እንደሆነም ይጠቅሳል። በተመሳሳይ ሳውድ አረቢያ ውስጥም በሞት የተቀጡት ሰዎች ብዛት ኻቻምና 65 ቢሆንም አምና ግን 196 እንደሆነ አምነስቲ ዘገባ ያሳያል። ከእነዚህ ሃገራት በተጨማሪ እንደ ኩየት፤ ማያንማር፤ የፍልስጤም ግዛት፣ ሲንጋፖር እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥም በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍ ማለቱ በዘገባው ተጠቅሷል። ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 20 ሃገራት የሞት ቅጣት መፈጸማቸውን ያመለከተው ዘገባው አክሎም ሳውዲ ውስጥ በአንድ ቀን 81 ሰዎች በዚህ መንገድ መቀጣታቸውን ገልጿል። በድርጅቱ የሞት ቅጣን የሚከታተለው ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ኪያራ ሳንጆርጂዮ፤ በተለይ ሳውድ አረቢያ ውስጥ የሞት ቅጣት ከተፈጸመባቸው አብዛኞቹ ሺያቶች መሆናቸው ፍርዱ ባልተገባ መንገድ ለተጽዕኖ በሚጠቀሙበት ባለሥልጣናት እጅ መግባቱን ያመላክታል ባይ ናቸው።

«ቅጣቱን በሚጠቀሙ አንዳንድ ሃገራት የሞት ቅጣትን ከቅጣትነቱ ይልቅ በመንግሥታት እጅ ያለ መጠቀሚያ ለማድረግ ቀጣይ ጥረት መኖሩን እያየን ነው። አንዳንዶች የሞት ቅጣት ወንጀሎችን ይቀንሳል ባዮች ናቸው፤ ያንን ግን እያየን አይደለም። ይበልጡን አናሳ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፤ እንዲሁም ተቃዋሚዎች ለመግጣት መንግሥት በመሣሪያነት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አካል ነው።»

አምነስቲ እንዳመለከተው ባለፈው ዓመት በ20 ሃገራት ውስጥ ባጠቃላይ 883 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል። ይኽም በጎርጎሪዮሳዊው 2021 ዓ,ም ከተፈጸመው በ53 ከመቶ ከፍ ብሏል። እንዲህም ሆኖ ይኽ የታየው መጨመር ሺህዎች ላይ ሊፈጸም ይችላል ባላት ሀገር ቻይና ውስጥ የተደረገውን አላካተተም። ኪያራ ሳንጆርጂዮ፤ ተቋማቸው ከቻይና በቂ መረጃ ማግኘት እንደማይችል ያመለክታሉ።

ምስል Brendan Smialowski/Getty Images

«ከቻይና የምናገኘው ጥቂት መረጃ አለ፤ ሆኖም አጠቃላዩን ለማወቅ እና ገጽታውን ለመቀመር አዳጋች ነው። ወደ ሀገሪቱ መግባት አንችልም፤ ገለልተኛ ቃኚዎችም ወደዚያ መግባት አይችሉም። መረጃው የመንግሥት ምሥጢር ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ ያለንን ቅንጭብጭብ መረጃ በመያዝ በቻይና ስለተፈጸመው የሞት ቅጣት ቁጥር ለማውጣት ከባድ ነው። ባለን የቅኝት መረጃ መሠረት የሞት ቅጣት በስፋት እንደሚካሄድ ግን እናውቃለን ። እናም ቻይና በሞት ቅጣት ግንባር ቀደሟ ናት በእርግጠኝነት ማለት እንችላለን።»

ከቻይና ሌላ የሞት ቅጣት ሰሜን ኮርያ እና ቪየትናም ውስጥም በስውር እንደሚፈጸም ነው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ ዘገባ ያመለከተው። ምንም እንኳን የተፈጸመው የሞት ቅጣት ቁጥሩ በተጠቀሰው ዓመት መጨመሩ ቢገለጽም በአንጻሩ ስድስት ሃገራት ቅጣቱን ማስቀረታቸው በአዎንታዊነት ተጠቅሷል። አሁንም ኪያራ ሳንጆርጂዮ፤

«2022 በጣም አዎንታዊ እርምጃዎች እና አዎንታዊ ታሪኮችም ነበሩት። ከሕጋቸው ወይም ከወንጀለኛ መቅጫቸው የሞት ቅጣትን ፈጽመው ያስወገዱ ስድስት ሃገራት አሉን፤ ይኽም ሙሉ ለሙሉ ማስወገዱ ይቀጥላል የሚል ተስፋ ሰጥቶናል። እንዲህ ያለው መልካም ዜና የመጣው ደግሞ ከሁሉም ክፍለ ዓለማት ነው። ፓፓዋ ኒው ጊኒ፤ ካዛኪስታን አሉ፤ እንዲሁም አፍሪቃ ውስጥ እርምጃውን የወሰዱ ሦስት ሃገራት አሉን። በዚህም የሞት ቅጣት በታሪክ በቃልነት ብቻ የሚጠቀስ ይሆናል የሚል ብርቱ ተስፋ አሳድረናል።»

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያሳየው ብዛት ያለው የሞት ቅጣት የተፈጸመው በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓ,ም ነው።

ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW