1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አርባ ምንጭ አቅራቢያ የሻራ ቀበሌ ነዋሪዎች ሮሮ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23 2015

በጋሞ ዞን የሻራ ቀበሌ ነዋሪዎች በአካባቢው አስተዳደር አሥርና እንግልት እየተፈጸመብን ነው አሉ ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት በቀበሌው ከባለፈው ሐሙስ ወዲህ ሰዎች በፀጥታ አባላት በጅምላ እየታሠሩ ይገኛሉ ፤ በርካቶችም በሥጋት ቀበሌውን ለቀው ለመሸሽ ተገደዋል ።

የአርባ ምንጭ ከተማ
የአርባ ምንጭ ከተማ። ፎቶ ከማኅደርምስል Arbaminch culture and Tourism office

ነዋሪዎቹን ሥጋት ገብቶናል ይላሉ

This browser does not support the audio element.

በጋሞ ዞን የሻራ ቀበሌ ነዋሪዎች በአካባቢው አስተዳደር አሥርና እንግልት እየተፈጸመብን ነው አሉ ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት በቀበሌው ከባለፈው ሐሙስ ወዲህ ሰዎች በፀጥታ አባላት በጅምላ እየታሠሩ ይገኛሉ ፤ በርካቶችም በሥጋት ቀበሌውን ለቀው ለመሸሽ ተገደዋል ። ዶቼ ቬለ DW የነዋሪዎቹን ሥጋት አስመልክቶ በስልክ ያነጋገራቸው የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው በፀጥታ አባላቱ እየታሠሩ የሚገኙት በቀበሌው በትጥቅ የታገዘ አንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቡድን አባላት እንጂ ሰላማዊ ሰዎችን አይደለም ብለዋል ።

በጋሞዋ የሻራ ቀበሌ ምን ተፈጠረ ? 

ከሁለት ሳምንታት በፊት በተዋቀረው አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ውስጥ የሚገኘው የሻራ ቀበሌ ካለፈው ሐሙስ ወዲህ ሰላም እርቆታል ፤ ሥጋትም አጥልቶበታል ይላሉ ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው የቀበሌው ነዋሪዎች ፡፡ የጋሞ ዞን መናገሻ ከሆነቸው አርባምንጭ ከተማ በዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሻራ ቀበሌ ቀደምሲል በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሥር ሲተዳደር መቆየቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቀበሌው የአርባምንጭ ከተማ አካል ሆኖ እንዲካለል የተጀመረው አንቅስቃሴ በአካባቢው ለነገሠው ውጥረት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ ፡፡

የጅምላ እሥር

በሻራ ቀበሌ የሰዎችን ሕይወት ያቀጠፈው የባለፈው ሐሙስ የተኩስ ልውውጥን ተከትሎ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በፀጥታ አባላት እየታሠሩ እንደሚገኙ ሥማችን አይጠቀስ ያሉ የቀበሌው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ DW ተናግረዋል፡፡ በቀበሌው የገቡት የዞኑ የፀጥታ አባላት በተሸከርካሪ የሚጓዙ መንገደኞችን ጭምር በማስቆም የነዋሪነት መታወቂያ ይጠይቃሉ የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች ነገርግን ነዋሪነቱ የሻራ ቀበሌ የሆነ ሰው ሲያገኙ ያለምንም ማስረጃ ወስደው ያሥራሉ ፡፡ እስከአሁን በዚህ ሁኔታ ከ300 በላይ ሠዎች ታስረዋል ፡፡ አብዛኞቹ ታሳሪዎች በቀበሌው ከተፈጠረው ጉዳይ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ናቸው ፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀበሌው ባለው ሥጋት የተነሳ አንዳንዶቹ ወደ አጎራባች አካባቢዎች ሲሸሹ የቀረነው ደግሞ በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገደናል “ ብለዋል ፡፡

ፎቶ ከማኅደር፦ የቀድሞው የደቡብ ሕዝቦች ክልል ከዓመታት በፊት በክልሉ የጋሞ ዞንን ጨምሮ የተለያዩ አዳዲስ ዞኖች እንዲኖሩ ምክር ቤቱ ምርጫ ባደረገበት ወቅት የተነሳ ፎቶ ።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በትጥቅ የተደገፈ ሙስና

ዶቼ ቬለ DW የነዋሪዎቹን ሥጋት አስመልክቶ በስልክ ያነጋገራቸው የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ኩንሳ በቀበሌው ከባለፈው ሐሙስ ወዲህ የነበረው አለመረጋጋት አሁን ላይ እየተሸሻለ መምጣቱን ተናግረዋል ፡፡ በቀበሌው የተፈጠረው አለመረጋጋት የህዝብና የመንግሥት መሬትን ከዳላሎች ጋር በመመሳጠር በመሸጥ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ያሏቸውና  አሁን ላይ  በፀረ ሙስና ተከሰው በህግ ሂደት ላይ ከሚገኙ የአካባቢው አመራሮች ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡

አርባምንጭ አቅራቢያ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች 18 ሰዎች ሳይገድሉ እንዳልቀረ ተገለጸ

የቀበሌው ነዋሪዎች ሕጋዊ የይዞታ ባለንብረትነታቸው ተጠብቆ በአዲሱ የአርባምንጭ ከተማ ማስተር ፕላን ውስጥ እንዲካተቱ ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቀሱት አቶ ወንድወሰን “ ይሁንእንጂ የጉዳዩ ዋናው መነሻ በሕግ ጥላ ሥር ከሚገኙ ተጠርጠሪዎች ጋር ግንኙነት ያለቸውና የዘረፋ ጥቅማቸው የተነካባቸው ቡድኖች ሂደቱን ለማደናቀፍ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረዋል ፡፡ ሀቁ በማህበራዊ ሚዲያዎች አንደሚባለው ሳይሆን ይህ ቡድን ዘረፋውን ለመቀጠል በትጥቅ የታገዘ ጥቃት መክፈቱ ነው ፡፡ በዚህም ምክንያት መሆኑ የሌለበት ክቡር የሰው ልጅ ህይወት እንዲያልፍ ሆኗል ፡፡ በነበረው የተኩስ ልውውጥ በታጣቂው ቡድን በኩል ሰባት ሰዎች ሲሞቱ በፀጥታ ተቋማት በኩል ደግሞ አራት አባለት ቆስለዋል “ ብለዋል ፡፡

የፀጥታ አባላቱ ባገኙት ነዋሪ ላይ በሙሉ እሥር እየፈጸሙ ይገኛሉ በሚል ለቀረበው ቅሬታም የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊው አቶ ወንድወሰን “ በፀጥታ አባላቱ እየታሠሩ የሚገኙት በቀበሌው በትጥቅ የታገዘ አንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቡድን አባላት እንጂ ሰላማዊ ሰዎችን አይደለም “ በማለት መልሰዋል ፡፡ በአሁኑወቅትም በሁኔታው የተደናገጡ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በአገር ሽማግሌዎችና  በሃይማኖት አባቶች በኩል የሰላምና የፀጥታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ወንደሰን ተናግረዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW