አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና አፍሪካ፦ አንድ ለአንድ ከአስመላሽ ተካ ጋር
ዓርብ፣ ግንቦት 22 2017
ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና ብርቱ ውድድር የገጠሙበት አርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ አንዳንዶች ለአፍሪካ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ይዞ እንደመጣ ያምናሉ። ከ1.5 ቢሊዮ በላይ ነዋሪዎች ያሏት አኅጉር በናጠጡት ሀገሮች ለሚሰሩ የአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ ውጤቶች ገበያ ከመሆን የዘለለ ሚና ሊኖራት ስለመቻሉ ጥርጣሬ ያላቸውም አይጠፉም።
አስመላሽ ተካ ግን ትምህርት እና ጤናን የመሳሰሉ ዘርፎችን ጨምሮ አርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ በተለያዩ መስኮች ለአፍሪካ ጥቅም እንደሚኖረው ያምናል። ለዚህም ራሱ አስመላሽ ያቋቋመው ልሳን የተባለ ኩባንያ ኹነኛ ምሳሌ ነው።
ልሳን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች የማሽን የትርጉም አገልግሎት ያቀርባል። በአሁኑ ወቅት ለእንግሊዘኛ፣ አማርኛ እና ትግርኛ የትርጉም አገልግሎት የሚሰጠው ልሳን ወደ ፊት አፋን ኦሮሞ እና ሶማሊኛን ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎች የማካተት ዕቅድ እንዳለው አስመላሽ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። ልሳን ከትርጉም በተጨማሪ ድምጽ ወደ ጽሁፍ የሚቀይር በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በማበልጸግ ላይ ይገኛል።
ልሳን የተሰማራበት ሥራ ጉግል እና ፌስቡክን የመሳሰሉ ኩባንያዎች በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ አማካኝነት አገልግሎት የሚሰጡበት ነው። ይሁንና ቴክኖሎጂውን ለማበልጸግ ልሳን የሚከተለው መንገድ እና የእነ ጉግል አካሔድ የተለያየ ነው።
በዚህ ቃለ-መጠይቅ ስለ አርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ ተስፋ እና ሥጋት፣ በቴክኖሎጂው ግንባታ ውስጥ አፍሪካ ስለሚኖራት ሚና አስመላሽ ተካ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ቃለ- መጠይቁን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
አርታዒ ታምራት ዲንሳ