1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረኛ ጥቃት በእንግሊዝ ተጫዋቾች ላይ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 6 2013

በእግር ኳስ ችሎታቸው ለላቀ ክብር ይበቃሉ ተብለው የሚጠበቁትን የእነዚህን «ወጣት ፈጣንና ዓይን የተጣለባቸውን ተጫዋቾች ቅስም ለመስበር ያለሙ» የተባሉት ዘረኛ ጥቃቶች ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ውግዘት ገጥሟቸዋል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጥቃቱን በጥብቅ አውግዘዋል።ጥቃት ፈጻሚዎቹን አሳፋሪ ብለዋቸዋል።

Euro 2020 | Wandbild von Marcus Rashford
ምስል Peter Byrne/PA/AP/picture alliance

ዘረኛ ጥቃት በእንግሊዝ ተጫዋቾች ላይ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው እሁዱ የአውሮጳ እግር ኳስ ሻምፕዮና የፍፃሜ ውድድር ላይ ፍጹም ቅጣት ምት የሳቱ ሦስት የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የተሰነዘረባቸው ዘረኛ ጥቃት መወገዙ ቀጥሏል። የጥቃቱ መሠረታዊ ምክንያትና መከላከያ መፍትሄው የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።
ለአውሮጳ እግር ኳስ ሻምፕዮና የፍጻሜ ውድድር እሁድ ምሽት ለንደን ዌምቢሊ ስታድዮም የገጠሙት የእንግሊዝና የኢጣልያ ቡድኖች ጨዋታ ከመደበኛው ሰዓት በተጨማሪ ለ30 ደቂቃ ቢራዘምም አንድ እኩል በመጨረሻቸው አሸናፊው በፍጹም ቅጣት ምት ነበር የተለየው።ልብ አንጠልጥሎ በዘለቀው በዚህ ጨዋታ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የተሰለፉ ሦስት ታዋቂ ወጣት ጥቁር እንግሊዛውያን እንደ አለመታደል ሆኖ ፍጹም ቅጣት ምት መሳታቸው ሆነ ተብሎ የተዛባ ትርጉም ተሰጥቶት የዘረኛ ጥቃት ውርጂብኝ ሰለባ ሆነዋል። የ23 ዓመቱ ማርኩስ ራሽፎርድ፣የ 21 ዓመቱ ጄደን ሻንኮ እና የ19 ዓመቱ ቡካዮ ሳካ  ማንኛውም የእግር ኳስ ተጫዋች እንደሚያጋጥመው ለጨዋታው ወሳኝ የነበሩትን ፍጹም ቅጣት ምቶች መሳታቸው፣ የእስከዚያን እለቱን ልፋታቸውን መና አስቀርቶ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ለዘረኛ ዘለፋዎችና መሰል ጥቃቶች አጋልጧቸዋል።ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ‘ተጫዋቾቹ ሆነ ብለው ቅጣት ምቶቹን እንደሳቱ ከሚገልጹት የሀሰት መላ ምቶች አንስቶ  የሰዎችን የቆዳ ቀለም መነሻ ላደረጉ ዘረኛ ጥቃቶች የሚያነሳሱ መልዕክቶችና እጅግ የወረዱ ክብረ ነክ ዘለፋዎች ድረስ ፣ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀኑ በኢንስታግራምና በትዊተር ተዥጎድጉውባቸዋል።እነዚህ መልዕክቶች በአብዛኛው ከውጭ የመጡ መሆናቸው ተረጋግጧል ተብሏል።በእግር ኳስ ችሎታቸው ለላቀ ክብር ይበቃሉ ተብለው የሚጠበቁትን የእነዚህን «ወጣት ፈጣንና ዓይን የተጣለባቸውን ተጫዋቾች ቅስም ለመስበር ያለሙ» የተባሉት ዘረኛ ጥቃቶች ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ውግዘት ገጥሟቸዋል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጥቃቱን በጥብቅ አውግዘዋል።ጥቃት ፈጻሚዎቹን አሳፋሪ ብለዋቸዋል።
«በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ዘረኛ ጥቃት የሚሰነዝሩትን «አሳፋሪዎች» ብያቸዋለሁ። በሰራችሁት ነገር አፍራችሁ በዓለም ፊት ራሳችሁን ትደብቃላችሁ ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ።ምክንያቱም ይህ ቡድን በአጠቃላይ የተጫወተው እንደ ጀግኖች ነው።»
 ከውድድሮች አስቀድሞ ተጫዋቾች ዘረኝነትን በመቃወም በአንድ እግራቸው በመንበርከክ ለዓለም መልዕክታቸውን ካስተላለፉበት የአውሮጳ የእግር ኳስ ሻምፕዮና ፍጻሜ በኋላ ዘረኛው ጥቃት መከተሉ አስገርሟል። ቀደም ሲል «የመናገር ነጻነትን የሚገድብ ሲሉ» ቦሪስ ጆንሰንና ሌሎች የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች ድርጊቱን ማንጓጠጣቸው ዘረኞችን የሚያበረታታ መከላከያ ተብሎ ሲተች ነበር።ከቦሪስ ጆንሰን መከላከያ በኋላ የአሁኑ ዘረኛ ጥቃት መድረሱ አያስደንቅም ያሉ አሉ። ሆኖም ጆንሰን ከዚህ ቀደም ያሉትን አስተባብለው ዘረኛውን ድርጊት በመኮነን አቋማቸውን ማስተካከላቸውን  የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ ተናግሯል።
በሦስቱ ተጫዋቾቹ ላይ የተፈጸመውው በደል ብዙዎችን ክፉኛ አሳዝኗል።ቡድኑን ለፍጻሜ ውድድር በማብቃት ትልቅ ሚና የተጫወቱት እነዚህ ተጫዋቾች ከምስጋና ይልቅ ለዘረኛ ጥቃት እንዲጋለጡ መደረጉ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌትን ክፉኛ አበሳጭቷል።በጨዋታው ለሆነው ሁሉ ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ የተናገሩት ሳውዝጌት በተጫዋቾቻቸው ላይ የተፈጸመውን በደል  ይቅር የማይባል ሲሉ ኮንነውታል።
«በእውነት የተወሰኑት መበደላቸው ይቅር የማይባል ነው።አብዛኛው ከውጭ እንደመጣ አውቃለሁ።ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ይህን ለማብራራት ችለዋል።ሁሉም ነገር እኛ የቆምንለት ዓላማ አይደለም።እንደሚመስለኝ እኛ ሰዎችን አንድ በማድረግ ራሳቸውንም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንዲያዛምዱ በማድረግ ፋና ወጊ ሆነናል።»
ምንም እንኳን ዘረኝነትን ለመከላከል በብሪታንያም ይሁን በሌሎች ሃገራት በስፖርቱ መስክ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢካሄዱም ውሳኔዎችም ቢተላለፉም ችግሩ አልቀነሰም።የህዝቡን ዘረኛ አስተሳሰብ  ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶች ታዲያ ለምን ሳይሰምሩ ቀሩ?በተለይ በብሪታንያ የሚሆነውን ያነሳው ድልነሳ እንደሚለው ችግሩ ወዲህ ነው። 
የሃገራቸውን ስም በዓለም አቀፍ መድረኮች ያስጠሩት ሦስቱ ተጫዋጮቻቸው አለአግባባ የተሰነዘረባቸውን የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረገ በደልና ግፍ ያወገዙት አሰልጣኝ ሳውዝጌት ቡድኑም ሆነ ህዝቡ ከጎናቸው እንደቆሙ ነው ያረጋገጡት።እርሳቸው እንዳሉት ብዙሀኑ ህዝብ የድርጊቱ ተቃዋሚ ነው።  
«እነዚህ ልጆች እጹብ ድንቅ ስራ ሰርተዋል። እንደ ቡድን በአንድ ላይ ነው የምናገግመው።እኛ ከነሱ ጎን ነን።99 በመቶው ህዝብም ከነሱ ጋር ነው።ምክንያትም ግሩም ጨዋታቸውን ያደንቃሉ።በተለይ የመጨረሻውን ፍጹም ቅጣት ምት የሳተው ሳካ ለማመን ከሚያስቸግር ብስለት ጋር የዚህ ጨዋታ ፍጹም ኮከብ ነበር። አጨዋወቱ በብዙዎች ፊት ላይ ፈገግታ አምጥቷል።ከቡድኑ አባላት እጅግ ዝና ለማትረፍ የበቃ የቡድኑ አባል ነው።የሁሉም ድጋፍ እንዳለው አምናለሁ።» 
የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ የአሰልጣኝ ሳውዝጌትን አመለካከት ይጋራል። ድልነሳ በልብ በዐዕምሮ የሚሰርጽ ያለውን የዘረኝነት አስተሳሰብ የሚያራምዱት ጥቂቶች ናቸው።
 ዓለም ከፍተኛ የስልጣኔ ደረጃ ላይ በደረሰችበት በዚህ ዘመን ሰልጥነዋል በሚባሉ ሃገራት ጭምር የቆዳ ቀለምን ወይም ዘርን መሰረት በማድረግ የሰው ልጅን ማራከስና ማጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ አሳሳቢነቱ ጨምሯል። ታዲያን ችግሩን እንዴት መከላከል ይቻል ይሆን? ድልነሳው 
የለንደን የፖሊስ ድርጅት ድርጊቱን ፈጻሚዎችን አሳዶ ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታውቋል። 
በሦስት የብሪታንያ የእግር ኳስ ተጫዋጮች ላይ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የደረሰውን ዘረኛ ጥቃትና መፍትሄው ላይ ያተኮረው የዛሬው ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል።ኂሩት መለሰ ነኝ ደህና ቆዩን
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ
 

ምስል Carl Recine/AP Photo/picture alliance
ምስል Paul Ellis/Getty Images/AFP
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW