1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የልጃገረዶች ጠለፋ በኮሬ ዞን

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን «እየተባባሰ መጥቷል» ባሉት ጠለፋ የተነሳ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ። በዞኑ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ስለማይሰጥ አሁን ላይ ሴት ልጆች ወጥተው ለመግባት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ነው ነዋሪዎቹ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ።

Sudan Äthiopien Frauen Symbolbild
ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance

በአካባቢው አዳጊ ሴቶች ዘንድ ወጥቶ የመግባት ሥጋት አይሏል

This browser does not support the audio element.

በደቡብ  ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን «እየተባባሰ መጥቷል» ባሉት ጠለፋ የተነሳ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ። በዞኑ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ስለማይሰጥ አሁን ላይ ሴት ልጆች ወጥተው ለመግባት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ነው ነዋሪዎቹ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ።  በዞኑ በያዝነው ግማሽ ዓመት ብቻ የጠለፋ ድርጊትተፈጽሞባቸዋል የተባሉ የ24 ልጃገረዶች ሥም ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ ወላጆችና የሕዝብ ተመራጮች በዞኑ የሕግ አካላት ላይ  ጫና እያደረጉ ይገኛሉ ።    

የጎርካ ወረዳ ተማሪዋ

ዶቼ ቬሌ ማህበራዊ ተፅኖን ለማስቀረት ሲል ሥማቸውን ያልጠቀሳቸውና በዞኑ የጎርካ ወረዳ ነዋሪ መሆናቸውን የሚናገሩት አንድ አባት ልጆቻቸው የጠለፋ ሰለባ ከሆኑባቸው መካከል አንዱ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው ላይ የጠለፋ ተግባር መፈጸሙን የተናገሩት የጎርካ ቀበሌው አባት " ልጄ ትልቅ ቦታ ትደርሳለች በሚል ተስፋ ነበር ሳስተምራት የነበረው ፡፡ ከሁለት ሳምት በፊት ጆጆላ በተባለው ከተማ ከሚገኘው ትምህርት ቤት ከእህቷ ጋር ወደ ቤት በመመለስ ላይ እንዳለች በስድስት ወንዶች ተጠልፋ ነው የተወሰደችው ፡፡ በወቅቱ እሷም ሆነች እህቷ ጩኸት ቢያሰሙም የሚያስጥላቸው አላገኙም ፡፡ ጉዳዩን በህግ ለመያዝ ያደረኩት ጥረትም አልተሳካም  " ብለዋል ፡፡

ወጥቶ የመግባት ሥጋት

ነዋሪው የሴት ልጆቹ ወጥቶ መግባት አሥግቶታልምስል Colourbox

በኮሬ ዞን በያዝነው የግማሽ ዓመት ብቻ በትምህርት ቤትና በገበያ ጉዞ ላይ የነበሩ 24 ልጃገረዶች  የጠለፋ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ዶቼ ቬለ ከታማኝ ምንጮቹ አረጋግጧል ፡፡ ችግሩ  ያሳስበናል የሚሉ አካላትም በጉዳዩ ላይ ምርመራ ይደረግልን በሚል የተጠላፊዎችን ሥም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኢሰመኮ ማስገባታቸው ታውቋል ፡፡ ወይዘሮ ታደለች ታሪኩ የኮሬ ዞንን በመወከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር አባል ናቸው ፡፡ በዞኑ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት ስለማይሰጥ አሁን ላይ ሴት ልጆች ወጥተው ለመግባት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን የተናገሩት የምክር ቤት አባሏ " ቀደምባሉት ጊዜያት  ጠለፋ በዞኑ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አልነበረም ፤ እንደባህል አይቆጠርም ፡፡ አሁን ችግሩ እንዲባባስ ያደረገው የተጠያቂነት አለመስፈን ነው ፡፡ ይህ ጠላፊዎች የልብ ልብ እንዲያገኙ አድርጓል " ብለዋል ፡፡ 

የሕግ አካላት ምን ይላሉ ?

ዶቼ ቬለ በዞኑ ጎርካ ወረዳ ህጻናትና ሴቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ባህሯ ብዙነህን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ኃላፊዋ በሰጡት የሥልክ ቀጠሮ መሰረት ቢደወልላቸውም ጥሪ ባለመመለሳቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ኤርሚያስ ኤሳ ግን " እስከአሁን ልጅ ተጠልፎብኛል ብሎ ወደ እኛ የመጣ አካል የለም "” ብለዋል  ፡፡

የጠለፋ ችግሩ የለም አልልም ሊኖር ይችላል ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ " ነገሩ ከሚባለው በላይ የተጋነነ ይመስለኛል ፡፡ ምናልባት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የፈለጉ አካላትም ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ አሁንም ጉዳት ደርሶብናል ብሎ የመጣ ሰው ካለ እኛ እንደተቋም ተቀብለን ምላሽ የምንሰጥ ይሆናል " ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW