1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎው ጥቅጥቅ ደን የተጋረጠበት አደጋ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 9 2015

ለጀርመኑ ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ቅርበት ያለው የፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ከሰሀራ በረሀ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት ስራ አጥነት እጅግ ተባብሷል። በተቋሙ የአፍሪቃ ጉዳዮች አጥኚ ሮበርት ካፔል እንደሚሉት በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ሰዎች በገጠርም ሆነ በከተሞች የሌሉ ስራዎች ፍለጋ ላይ ናቸው።

Südafrika Kapstadt | Arbeitslosigkeit
ምስል Nic Bothma/EPA-EFE

አሳሳቢው የአፍሪቃ ወጣት ስራ አጦች ቁጥር ማደግ፤ የኮንጎው ጥቅጥቅ ደን የተጋረጠበት አደጋ

This browser does not support the audio element.

በአፍሪቃ የስራአጦች ቁጥር እየጨመረ መሄድ አሳሳቢ ሆኗል።በተለይ ደቡብ አፍሪቃን በመሳሰሉ ሀገራት ችግሩ ማኅበራዊ ቀውሶችን እንዳያባብስ አስግቷል። በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጥቅጥቅ ደን አቅራቢያ ነዳጅ ዘይት መገኘቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከማፈናቀል በተጨማሪ ለደኑ ጥበቃ አደጋ ይፈጥራል መባሉ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን አስጨንቋል። የዛሬው ትኩረት በአፍሪቃ በነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
ወጣቱ ስቲቭን ሞዮ ሁሌም በየቀኑ ማልዶ ከጠዋቱ አስራ አንድ ሰዓት ከእንቅልፉ ተነስቶ በደቡብ አፍሪቃዋ የንግድ ከተማ ጆሀንስበርግ ጎዳናዎች ስራ ፍለጋ ይሰማራል። የኤሌክትሪክ ባለሞያ ነው። በየጎዳናው እየተዘዋወረ ሞያውን በማስተዋወቅ ስራ ይፈልጋል።ከቀናውና የሚያሰrwe ካገኘ  በቀን እስከ 30 ዩሮ ሊያገኝ ይችላል ።አሁን ግን ገቢው ከቀን ወቀን እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው። ሞዮ የሚኖርባት ደቡብ አፍሪቃ በኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሽን ምክንያት የኤኮኖሚ ዝግመት ላይ ናት። በዚህ የተነሳም በሀገሪቱ ስራ ማግኘት እጅግ እየከበደ ሄዷል። ሞዮ እንደሚለው ችግሩ እየተባባሰ ነው። ስራ ማግኘት አልቻለም።አሁን አሁን ለምግብም ሆነ ለቤት ኪራይ ገንዘብ ከየት እንደሚያገኝ አያውቅም። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ስቲቭ የሞዮን አይነት ሕይወት የሚገፉ በርካታ ስራ አጦች አሉ።
ኬፕታውን የምትኖረው በሀያዎቹ እድሜ ውስጥ ያለችው ናምህላ ምሲምቢ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበረች ። በዩኒቨርስቲ የስነ ልቦና ትምህርት ነበር የምትከታተለው። ሆኖም ምስሃቢ የትምህርቱ ክፍያ ስለከበዳት ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገዳ የስራ አጦቹን ዓለም ተቀላቅላለች። የሌሎች ተማሪዎችም እጣ ከርስዋ ጋር የሚመሳሰል ነው።ሆኖም ምሲምቢ እንደምትለው ስራ ለማግኘት ሰው ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።
«ሰዎች ድርጅቶቻቸው ውስጥ የሚቀጥሩት  ቤተሰቦቻቸውን እህቶቻቸው ነው ዘመዶቻቸውን ነው።የሚያውቅህ ካላገኘህ ስራ ማግኘት በጣም ከባድ ነው።»
የደቡብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ይዞታ እጅግ አስደንጋጭ ነው።በደቡብ አፍሪቃ እድሜያቸው ከ34 ዓመት በታች ከሆነ ሁለት ወጣቶች አንዱ ስራ አጥ ነው። በሀገሪቱ የስራ አጥነት ደረጃ በመጠኑ ተሻሽሏል ቢባልም ባለፈው ጎርጎሮሳዊው 2022 ዓም መጨረሻ ላይ ይፋ እንደተደረገው፣የስራ አጡ ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ 32.7 በመቶ ነበር። ደቡብ አፍሪቃ በስራ አጦች ብዛት ከአፍሪቃም ሆነ ከዓለማችን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የዶቼቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ ዘግባለች።  በደቡብ አፍሪቃ ስራ አጥነት ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ቀውሶችን አስከትሏል። ለአብነት ያህል በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2021 በጆሀንስበርግና በደርባን ከተሞች ዝርፊያና ብዙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል። በዚህ ሰበብም የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ለስራ አጦች አነስተኛ ማኅበራዊ ድጎማ ለመስጠት ተገዶ እንደነበር የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎው ፓትሪክ ቦንድ ያስታውሳሉ።
« ወጣት ስራ አጥነት አደገኛ ነው። በ2021 በሐምሌ ወር በጆሀንስበርግና በደርባና ከተሞች አመጽ አስከትሎ ነበር። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለስራ አጦች በወር  እስከ 18 ዩሮ የሚደርስ የማኅበራዊ ድጋፍ ክፍያ እንዲሰጡ አድርጎ ነበር። ይህም መንግሥት ተስፋ በመቁረጥ ችግሩን ገንዘብ በመስጠት ለማለፍ ያደረገው ሙከራ ነበር።»
ሆኖም ቦንድ ይህ ችግሩን ለማቃለል አይረዳም፤በቂም አይደለም ነው የሚሉት። መንግሥት ገንዘብ የሚሰጥ ከሆነ ከዚህ የተሻለ ሊሆን ይገባል እንደ ቦንድ።ለድጎማ የሚሰጠው ገንዘብ የምግብ ፍጆታንና የመጠለያ ወጪን ከሞላ ጎደል እንዲሸፍን ቢያንስ በወር ወደ 40 ዩሮ ሊያድግ ይገባል ነው የሚሉት።እዚህ ላይ ትልቁ እንቅፋት የሚመጣው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ከመሳሰሉ ድርጅቶች ነው። በደቡብ አፍሪቃ ከፍተኛ እዳ ምክንያት የገንዘብ ሚኒስትሩ በጀት ለመቀነስና ማኅበራዊ ድጎማዎችንም እንዲገድቡ ግፊት ይደረግባቸዋል። 

ምስል Thomas Imo/photothek.net/picture alliance

ለጀርመኑ ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ቅርበት ያለው የፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ከሰሀራ በረሀ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት ስራ አጥነት እጅግ ተባብሷል። በተቋሙ የአፍሪቃ ጉዳዮች አጥኚ ሮበርት ካፔል እንደሚሉት በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ሰዎች በገጠርም ሆነ በከተሞች የሌሉ ስራዎች ፍለጋ ላይ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ገበያ ላይ ያለውን ስራና የስራ ፈላጊውን ብዛት ለማነጻጸር ዩጋንዳ ጥሩ ምሳሌ ናት።በጥናቱ መሠረት በየዓመቱ 400 ሺህ ወጣት ዩጋንዳውያን ወደ ስራው ገበያ ቢመጡም የስራ ቦታ ያለው 52 ሺህ ለሚሆኑት ብቻ ነው።በዩጋንዳ በአሁኑ ጊዜ በተለያየ ሞያ የሰለጠኑ 1.2 ሚሊዮን ወጣቶች ስራ የላቸውም።ከመካከላቸው አንዷ ማውሪን ባቢድዬ ናት። በአንድ የበረራ ትምህርት ቤት የጉዞ አስተዳደር ተምራለች።ከተመረቀች ሁለት ዓመት አልፏታል ።ስራ ግን አላገኘችም።በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በተለማማጅ ሰራተኝነት ካገለገለች በኋላ በአንድ አየር መንገድ ስራ ለማግኘት ብትሞክርም አልተሳካላትም።
«ለሁለት ዓመታት የሚቀጥረኝ የጉዞ ወኪል ቢሮ ወይም አየር መንገድ ስፈልግ ቆይቻለሁ።ግን ምንም አልተሳካልንም። ፉክክሩ ከፍተኛ ነው። ሰው ለሌለው ሰው ስራ ማግኘት ከባድ ነው።»
ባቢድዬ አሁን የራስዋን የጉዞ ወኪል ለመክፈት እየሞከረች ነው። ቻርልስ ኦሲሲ „ኢንተርፕራይዝ ዩጋንዳ” የተባለ ተቋም ሃላፊ ናቸው። አሁን ሁሉ ነገር ስለተለወጠ ስራ ፈላጊም መቀየር መቻል አለበት ይላሉ።
«አሁን ያለው ስራ በጣም አነስተኛ ነው። ወደፊት ደግሞ እየከሰመ ይሄዳል።ይህ በዩጋንዳ ብቻ የሚሆን አይደለም፤በመላው ዓለም እንጂ ። ትምህርት ቤት ሂድ ፣ጠንክረህ ተማር ፣ከዚያ ስራ አግኝ የሚለው  የቀድሞ አመለካከት  ዘመን አልፎበታል።ዛሬ ይህ አባባል መስተካከል አለበት፤ትምህርት ቤት ሂድ  እንደ ተቀጣሪም ሆነ የራስን ድርጅት እንደሚከፍት በስራ ገበያ ተፈላጊ ለመሆን  ራስን በውጤታማ መንገድ አዘጋጅ በሚለው መቀየር አለበት። ብዙ ሰዎች የራሳቸውን ድርጅት የመክፈት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ይበልጥ ድጋፍ ያደርጋሉ።» 
የወጣት ስራ አጦች ቁጥር መጨመር በተለይ በደቡብ አፍሪቃ በጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም. በአረቡ ዓለም የተቀሰቀሰው ዓይነት  አብዮት እንዳያስነሳ ማስጋቱ አልቀረም።ቦንድ እንዳሉት ምዕራቡ ዓለም ደቡብ አፍሪቃ እዳዋን እንድትከፍል ማስገደዱን ከቀጠለ  ሀገሪቱ ለስራ ፈጠራ መርሃ ግብሮችም ሆነ ለማኅበራዊ ድጎማዎች ልታወጣ የምትችለው ገንዘብ አነስተኛ ይሆናል።
የኬፕታውኗ ናማላ ሚሲምቢ ወጣቶች ስራ እንዲያገኙ የሚያግዝ ድርጅት ውስጥ መሠረታዊ እውቀት ከቀሰመች በኋላ ከስራ ማጣት ጭንቀት የሚገላግል ተስፋ ፈንጥቆላታል።ብዙም ሳትቆይ  በረዳት መምህርነት ጊዜያዊ ስራ አግኝታለች።

ምስል Julia Jaki/DW

 

 የኮንጎው ጥቅጥቅ ደን የተጋረጠበት አደጋ

ምስል Judith Raupp/DW


በኮንጎው የታወቀ ጥቅጥቅ ደን አካባቢ ነዳጅ ዘይት ሊወጣ ነው መባሉ መባሉ ነዋሪዎችን ግራ አጋብቷል። አሳ አስጋሪው ዦን ፖል ኢኮሎንጊ፣ ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ፣የርሳቸው መኖሪያ ወደሆነችው ወደ ኮንጎዋ መንደር ምፔካ ከሚመጡ ፖለቲከኞች ወይም ደግሞ ከውጭ ሀገራት ወደዚሁ መንደር ከሚጎርፉ ተመራማሪዎች ማንኛቸውን ማመን እንዳለባቸው ማወቅ ቸግሯቸዋል። አንዳቸው ኩባንያዎች ነዳጅ ዘይት ፍለጋ እንዲያካሂዱ ከመንደሯ መነሳት አለባችሁ ሲሏቸው ሌላኛዎቹ ደግሞ ደኑን እየጠበቁ እዚያው እንዲቆዩ እንደሚፈልጉ ይነግሯቸዋል። ኢኮሎንጎ የሚኖርባት መንደር ምፔካ የምትገኘው ፣በማዕከላዊ አፍሪቃ ፣ሰሜን ምዕራብ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ነው። በስፍራው በብዝሀ ሕይወት የበለጸገ ጥቅጥቅ ደን ይገኛል። የኪሳንጋኒ የሊድስና የለንደን ዩኚቨርስቲ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የጀርመንን ግማሽ ያህል ስፋት አለው የሚባለው የዓለማችን ትልቁ ጥቅጥቅ ደን ከ29 ቢሊዮን ቶን በላይ ካርበን አምቆ መያዝ ይችላላ። ይህን ያህል መጠን ያለው ካርበን ማከማቸት የሚችለው ይህ ጥቅጥቅ ደን የዓለማችን ሙቀት እንዳይጨምር አስተዋጽኦ ያደርጋል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች ደኑ ተጠብቆ እንዲቆይ ቢሹም የኮንጎ መንግሥት ግን ሌላ እቅድ አለው።
ፖለቲከኞች እንደሚሉት በአካባቢው በሚገኙ ሦስት ስፍራዎች ነዳጅ ዘይት ተገኝቷል። ከነዚህ ቦታዎች የሚገኘው ነዳጅም በአጠቃላይ 22 ቢሊዮን በርሜል እንደሚሆን ተገምቷል። ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አንስቶ የተለያዩ ኩባንያዎች የነዳጅ ዘይት ማውጫ ፈቃድ ለማግኘት እየተጫረቱ ነው።ይህ ከተሳካ ለኮንጎ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ንግድ ይሆናል ተብሏል። ነዳጅ ዘይት አውጭ ኩባንያዎቹ ሲመጡም የኪንሻሳ ባለስልጣናት ለኢኮሎንጎ እንደነገሩት አንድ ሺህ የምፔካ ነዋሪዎች ከአካባቢው መነሳት አለባቸው። በዚያ ለሚገኙት አሳ አስጋሪዎች ጥሩ ጥሩ ቤቶች እንደሚሰሩላቸው በመላ ሀገሪቱም ትምህርት ቤቶች መንገዶች እና ሆስፒታሎች እንደሚገነቡ ቃል ተገብቷል። ኢኮሎንጎ 60 ዓመታቸውነው።ወቅቱ የዝንብ ጊዜ በመሆኑ በአቅራቢያቸው የሚገኘው የሩኪ ወንዝ በመሙላቱ ሁሉም ቤቱ ነው ያለው። በኢኮሎንጎ ቤት ዙሪያ ካለው ከዚህ ወንዝ አሁን የሚሰገረው አሳ ቁጥር እየቀነሰ ነው። ከብሪታንያ የመጡ ሳይንቲስቶች በወንዙ ውስጥ የሚገኙት አሳዎች ቁጥር በየጊዜው እየቀነሰ ለመሄዱ ዋነኛው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ለኢኮሎንጎ ይነግሯቸዋል።ስለዚህ እዚያው ቆይተው ጥቅጥቅ ደኑን መጠበቅ አለባችሁ ይሏቸዋል።የ38 ዓመቱ የኢኮሎንጎ ልጅ ድየሜርሲ ቢሳሎ ግን ተመራማሪዎቹ ደኑን አትቁረጡ ስለሚሉ  እነርሱ በሚናገሩት ደስተኛ አይደለም።
««ዛፎች መቁረጥ  አሳ ማስገር ፣ ደኑ ውስጥ እሳት ማያያዝ አትችሉም ይሉናል  ።ታዲያ ካልተፈለን እንዴት ነው እንቅስቃሴያችንን የምናቆመው። እኛ ዛፎችን እንዳንቆርጥ ሜዳም እንናዘጋጅ ከከለከሉን እንዴት አድርገን ነው መኖር የምንችለው ስንል ጠይቀናል። ግን መልስ አላገኘንም።
ካርቦንን በማከማቸት ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ይህ ደን እንዲያዝ «የምድራችንን ሳንባዎች ጠብቁ» የሚሉት ባለጸጋዎቹ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ። ከመካከላቸው ጀርመን ብቻ እስካሁን የ225 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ሰጥታለች።ምፔካ የሚገኘውጥቅጥቅ ደን በተለይ ለስድስት ዓመታት ተጨማሪ የ15 ሚሊዮን ዩሮ  ድጋፍ እያደረገች ነው።
በ2009 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር አማራጭ የኖቤል ሽልማት ያገኙት ረኔ ንጎንጎ ለተፈጥሮ ጥበቃ ሲሟገቱ የኖሩ 60 ዓመት እድሜ ያላቸው የስነ ሕይወት ምሁር ናቸው። ኪንሻሳ ውስጥ  ለመንግስት ቅርበት ባለው አንድ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት ንጎንጎ በ2015 ዓመተ ምህረቱ የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ድሀ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋሙ100 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ  ቃል መግባታቸውን ያስታውሳሉ።
«ገንዘብ ያስፈልገናል። ላለፉት 20 ዓመታት ቃል ብቻ ነው የተገባልን። ፓሪስ ውስጥ በጎርጎሮሳዊው 2015 ያደጉ ሀገራት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ለደሀ ሀገራት በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተው ነበር  
ጥቅጥቅ ደን ያለቸው ኮንጎ ብራዚል እና ኢንዶኔዝያ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት ሀገራት በጀት እንዲመደብላቸው መደራደር ይፈልጋሉ። ግሪን ፒስ ለተባለው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ድርጅት የሚሰሩት የ57 ዓመቱ ራውል ሞንሴምቡላ በዚህ አይስማሙም። ሞንሴምቡላ  እንደሚሉት ነዳጅ ዘይት ቢወጣም በኮንጎ መሰረታዊ የሚባሉችግሮች እስካልተወገዱ ድረስ እድገት ይመጣል ተብሎ አይታሰብም ።
«መልካም አስተዳደርና ግልጽነት እስከ ሌለ ድረስ ሙስናም ካልተወገደ በስተቀር ከመላው ኮንጎ ነዳጅ ዘይት ቢወጣም ምንም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።ኮባልት ፣ኮልታን ወይም ሌላ ጥሬ እቃ እኛን ሀብታም ወይም የለማን ሀገር አድርጎን አያውቅም።»
ግrne ፒስ እንደሚለው ጥብቅ ደኖቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎች አደጋ ላይ  ናቸው። ድርጅቱ መንግሥት ለነዳጅ አውጭዎች ያቀረበው ጨረታ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ግሪን ፒስ እንደሚለው ነዳጅ ዘይት የሚወጣ ከሆነ ከከኮንጎው ጥቅጥቅ  ደን ስድስት በመቶው አደጋ ላይ ይወድቃል። 

ምስል dpa

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW