1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 4 2016

በተለይም ሴት ሕፃናት የመማር መብታቸውን ከማጣታቸው አልፎ ለ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸው፣ ወደ ከተማ እየፈለሱና ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

 Ethiopian Human Rights Commission about SNNPR human rights case
ምስል Ethiopian Human Rights Commission

አሳሳቢው የኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ በቀጠሉ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች እና እነዚህን ተከትለው በመጡ መፈናቀሎች ምክንያት በስምንት ክልሎች ውስጥ 5565 ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ የሚገኙ ወይምየተዘጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።  ከተዘጉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው ተብሏል። 

"አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው" በተባሉት በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የመምህራን ደመወዝ በወቅቱ አለመከፈሉ የበርካታ ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማርን ማስተጓጎሉ ተገልጿል።

ይህ በመሆኑ በተለይም ሴት ሕፃናት የመማር መብታቸውን ከማጣታቸው አልፎ ለ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸው፣ ወደ ከተማ እየፈለሱና ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በክልሎች ትምህርት የማግኘት መብት አፈጻጸምን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ጋር ባደረገው ውይይት ሀገሪቱ ውስጥ በተከሰቱና በቀጠሉ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ተያያዥ መፈናቀሎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ በሽዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችም ከአገልግሎት ውጪ ሆነው መዘጋታቸውን ገልጿል ። 

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱና በቀጠሉ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ተያያዥ መፈናቀሎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ በርካታ ትምህርት ቤቶችም ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል። ለምሳሌ በአማራ ክልል 4178፣ በትግራይ ከልል 648፣ በኦሮሚያ ክልል 420፣ በሶማሊ ክልል 195፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 50፣ በጋምቤላ ክልል 40፣ በአፋር ክልል 26 እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 8 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ኢሰመኮ ገልvጿል።

ሴት ሕፃናት የመማር መብታቸውን ከማጣታቸው አልፎ ለ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውምስል Solomon Muchie/DW

የተፈናቀሉ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት "በርካታተፈናቃይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል" ያለው ኮሚሽኑ በዚህ ምክንያት በተለይ ሴት ሕፃናት የትምህርት መብታቸው ከመጣሱ ባለፈ  ያለ ዕድሜ ጋብቻ ውስጥ እንዲገቡ ስለመገደዳቸው፣ ወደ ከተማ በመፍለስ ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ ስለመሆኑ፣ ሱስን ጨምሮ ለሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች መጋለጣቸው በውይይቱ መመላከቱን በኮሚሽኑ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ዳይሬክተር ዶክተር ብራይትማን ገብረሚካኤል ገልፀዋል።

በሌላ በኩል "አንጻራዊ ሰላም ያለባቸው በተባሉት ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የመምህራን ደመወዝ በወቅቱ እና በአግባቡ ባለመከፈሉ የመማር ማስተማር ሂደቱ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ተስተጓጉሏል ተብሏል።

 ‘’በትጥቅ ግጭትም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑተማሪዎችወደ ትምህርት እንዲመለሱ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ በግጭት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም በቂ በጀት የተያዘላቸውና በዕቅድ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ፤ ትምህርት ቤቶች በቋሚነት እስኪገነቡ ድረስ ጊዜያዊ የመማሪያ አማራጮችን ማዘጋጀት’’ ኮሚሽኑ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጣቸው ናቸው።

ኢሰመኮ ትምህርት የማግኘት መብትን በማረጋገጥ ረገድ መንግሥት ዋናው ባለግዴታ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን "በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው" ላለው የትምህርት መብት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቧል። 
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW