1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የጋዜጠኞች እስር በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ግንቦት 17 2014

የዘፈቀደ እስር፣ የጋዜጠኛን የሙያ ፈቃድ ነጥቆ ከአገር ማባረር፣ የፕረስ ነጻነት መጣስ እና ጋዜጠኞችን ማጥቃት ከያዝነው ወር ጀምሮ መጨመሩን የገለጹት የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሳዲቡ ማሮንግ የታሰሩት ጋዜጠኞች በሙሉ ባንዴ እንዲፈቱና የስቱድዮ ዕቃዎቻቸውም እንዲመለሱላቸው ጠይቀዋል።

Logo CPJ
ምስል APTN

አሳሳቢው የጋዜዘኞች እስር በኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ የታሰሩት ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአስቸኳይ እንዲለቁ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገቱ ሁለት ዓለም አቀፉ ድርጅት ጠየቁ። CPJ እና ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት በየግል ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ ቀናት ቢያንስ ከአስር በላይ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መታሰራቸውን አመልክተዋል። CPJ ድርጊቱን በአገሪቱ የዜጎች መረጃ የማግኘትና የሚድያ ነጻነት አንድ እርምጃ ወደፊት ሦስት እርምጃ ወደኋላ እየተራመደ መሆኑን እንደሚያመለክት ሲጠቅስ፣ ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ በበኩሉ በአማራ ክልል የታሰሩት ጋዜዘኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና በጸጥታ ሃይሎች የተወሰደባቸው የሙያ መሣሪያዎቻቸው  እንዲመለስላቸው ጠይቋል።

የአትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንደየመንግሥታቱ ሁኔታ የሚዋዥቅና በተለይም የፖለቲካ ትኩሳቱ በናረ ቁጥር የፊት ረድፍ ተጠቂ መሆኑ ትችቶች ይቀርቡበታል። ባለፉት ሦስት ዓመታት የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አዋጁ በመሻሻሉ እና የታሰሩ ጋዜጠኞች በመፈታታቸው በዚሁ መስክ ለውጥ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበረ ብዙዎች ይስማሙበታል። ሆኖም በጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ የሚፈጸሙ ያለፍርድቤት ትእዛዝ ማሰር፣ ከቤተሰብ እና ከሕግ አማካሪ መሰወር፣ ለቀናት ወይም ለወራት አስሮ ያለምንም ክስና ይቅርታ መፍታት እየተዘወተረ በመሆኑ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ማሕበራትና ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ተግባሩን ለመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። 

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት CPJ ትናንት ባወጣው መግለጫ ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል ቢያንስ 11 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች መንግሥት « ሕግ ማስከበር» ባለው ዘመቻ «ሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል»` በሚል መታሰራቸውን አመልክቷል። ሌሎች ከ4,500 በላይ ሰዎችም እንዲሁ። በዚህም በአገሪቱ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አንድ እርምጃ ወደፊት ሦስት እርምጃ ወደኋላ እየተራመደ ነው ብሏል። 

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት በበኩሉ በአማራ ክልል ቢያንስ 9 የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች እና ሥራቸውን በዩቱብ የሚያሰራጩ ባለሙያዎች መታሰራቸውን ገልጾ ባስቸኳይ እንዲለቀቁና ጥሪውን አቅርቧል። የታሠሩትም ስለሀገራዊ ጉዳይ በዩትዩብ የሚዘግቡት የንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የአሻራ ጋዜጠኖች እና ሠራተኞች እንደሆኑም አመልክቷል። በሀገሪቱ የሚካሄደው የጋዜጠኞች እስር ያሳሰበው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማሕበርም መንግሥት ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጥሪ ማቅረቡንም ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አክሎ ጠቅሷል። 

ምስል Getty Images/AFP/B. Guay

የዘፈቀደ እስር፣ የጋዜጠኛን የሙያ ፈቃድ ነጥቆ ከአገር ማባረር፣ የፕረስ ነጻነት መጣስ እና ጋዜጠኞችን ማጥቃት ከያዝነው ወር ጀምሮ መጨመሩን የገለጹት የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር  ሳዲቡ ማሮንግ የታሰሩት ጋዜጠኞች በሙሉ ባንዴ እንዲፈቱና የስቱድዮ ዕቃዎቻቸውም እንዲመለሱላቸው ጠይቀዋል። መግለጫውን  ተንተርሰን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማሕበር ፕረዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠን አነጋግረነዋል።

ጦርነት እና ግጭት ባለበት አገር የጋዜጠኝነት ሥራ ለብዙ ትርጉም የተጋለጠ እንደሚሆን የገለጸው የማሕበሩ ፕሬዝደንት ጥበቡ በለጠ ስህተት ቢኖርም እንኳ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ጋዜጠኛው መጠየቅ ካለበትም ሕግና ስርአትን ተከትሎ መሆን እንደሚኖርበት አሳስቧል። የጋዜጠኞች እስር ለውጡን ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ታይቶ የነበረውን ነጻነት እንዳያጠበው እና የአገሪቱንም ገጽታ እንዳያበላሸው ስጋት እንዳለው የገለጸው ጋዜጠኛ ጥበቡ በሙያው የሚስተዋሉ ችግሮች በቅድሚያ በሙያ ማሕበራት እና በመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት መድረኮች መታየት ይኖርበታል ባይ ነው።

CPJ የታሰሩት በዩትዩብ መረጃዎችን የሚያሰራጩት የአሻራ ሚዲያ፤ የንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞችን ጨምሮ፤ መስከረም አበራ የኢትዮ ንቃት ሚዲያ መሥራች እና አዘጋጅ፣ እንዲሁም ሰለሞን ሹምዬ የገበያኑ ሚዲያ መሥራች ባለቤት እና አዘጋጅ መሆናቸውን በማመልከት፤ ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል። ያለፍርድ ቤት የመንግሥት ባለሥልጣናትም ጋዜጠኞች ያለፍርሃት እና ያለዘፈቀደ እስራት ሥራቸውን ለማከናወን መቻላቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪውን አቅርቧል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ሽዋዬ ለገሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW