አሳሳቢዎቹ እገታ እና አስገድዶ የመሰወር ድርጊቶች
ሰኞ፣ ነሐሴ 19 2017
አሳሳቢዎቹ እገታ እና አስገድዶ የመሰወር ድርጊቶች
በተደጋጋሚ እየተፈፀመ የሚገኘው እገታ እና አስገድዶ መሰወር "የሥርዓት እልበኝነት" ማሳያ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠየቀ። በጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ባላቸውና በሌሎች ላይ የሚፈፀመው ይህ ድርጊት "መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ጥበቃ አለኝ" የሚለውን የማኅበረሰብ እምነት እየሸረሸረ የሚመጣ ነው" ሲሉ አንድ ፖለቲከኛ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሰሞኑን ከእገታ የተለቀቂ ሁለት ጋዜጠኞች በማን እና ለምን ታግተው እንደነበር "ግልጽ ማብራሪያ" ጠይቋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት "በመንግሥት ከሚፈጸሙ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እሥሮች ጎን ለጎን በታጣቂ ቡድኖች፣ ለዝርፊያ በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸሙ" ያላቸው እገታዎች "በነጻነት እና ሌሎች መሠረታዊ መብቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።" ብሎ ነበር። ሰሞነኛው ክስተት በተመለከተ ግን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል። እስካሁን የት እንዳሉ ያልታወቀው የጋዜጠኞች ጉዳይ
ሰሞኑን ሁለት ጋዜጠኞች ከ12 እና 10 ቀናት እገታ በኋላተለቀቁ ቢባልም ስለድርጊቱ ፈጻሚም ሆነ ምክንያት እስካሁን ምላሽ የሰጠ አካል የለም። ኢዜማ ድርጊቱ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ለምን በዝምታ ታለፈ? ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት ሰላምን እና ደህንነትን ከሚያውኩ ወንጀሎች ዜጎችን ለመጠበቅ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? ለሚለው ግልጽ ማብራሪያ ጠይቋል።
"እንዲህ ያሉ አፈናዎች በአንድ ወይም በሁለት ጋዜጠኞች ላይ ብቻ የተቃጡ ሳይሆን ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ዜጎች ሥራቸውንና ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልፁ መቀጣጫ እንዲሆን ታልሞ የተደረገ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም" ሲል ድርጊቱን ያወገዘው እናት ፓርቲ ደግሞ ሁኔታው የሥርዓት አልበኝነት ማሳያ እንዳይሆን ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሠይፈ ሥላሴ አያሌው ጥንቃቄ እንዲደረግ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
"መንግሥት በሚያስተዳድረው ከተማ ውስጥ እንደዚህ አይነት ነገሮች በሚፈፀሙበት ጊዜ በምንም አይነት መልኩ ተቀባይነት ያላቸው ጉዳዮች አይደሉም።" "የጋዜጠኞች ስወራ ተጠያቂነትን ማስከተል አለበት" ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር የሰሞኑ "ድርጊት ፈጻሚዎች በግልፅ ታውቀው በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ" ትናንት ጠይቋል። ዶክተር ሰይፈ ሥላሴ እንደሚሉት መሰል ተደጋጋሚ ሕገ ወጥ ድርጊቶች የማኅበረሰብን በሕግ ላይ ያለ እምነት የሚንዱ ናቸው።
"መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ጥበቃ አለኝ! የሚለውን ነገር ከሕዝብ እና ከማሕበረሰቡ አዕምሮ ውስጥ እየሸረሸረ የሚመጣ ነገር ነው።" በጉዳዩ ላይ የመንግሥት የፀጥታ አካላት፣ የኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ዝምታን መርጠዋል። ዶቼ ቬለ ደጋግሞ የችግሩን መነሻ እና ዘላቂ መፍትሔውን በተመለከተ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የጋዜጠኞች፣ የሞያው እና የተቋማቱ ደኅንነት በኢትዮጵያ
ቪዥን ኢትዮጵያ ለዶሞክራሲ የተባለ የሲቪል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ደርሰህ እያደገ የመጣው ይህ የወንጀል ድርጊት ኃላፊነትን ካለመወጣት ጋር የመጣ አሳሳቢ ችግር ነው ይሉታል። "ዛሬ እንኳን በክልል ደረጃ አዲስ አበባ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ነው ያለው። በዚህ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ያሳያል።"
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ ጉዳይ ምላሽ እየሰጠ አደለም። ተቋሙ ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ያለውን ዓመታዊ የመብቶች ሁኔታ ሪፖርት ከሳምንታት በፊት ይፋ ሲያደርግ ግን "በመንግሥት ከሚፈጸሙ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እሥሮች ጎን ለጎን በታጣቂ ቡድኖች፣ ለዝርፊያ በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸሙ" ያላቸው እገታዎች "በነጻነት እና ሌሎች መሠረታዊ መብቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።" ብሎ ነበር። ጋዜጠኞችን "ከሕግ እግባብ ውጪ መሰወር በአስቸኳይ ይቁም" የሙያ ማሕበር
የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት እንደሚሉት የማገት እና የመሰወር ድርጊቶች ችግር አባባሽ እንጂ መፍትሔ ያላቸው አይሆኑም። "ይበልጥ ቀውሱን የበለጠ የሚያባብስ እና የችግሩን አፈታት ይበልጥ የሚያወሳስበው ነገር ካልሆነ በስተቀር፣ ምናልባት ሰዎችን ዝም ከማሰኘት አኳያ፣ ከማስፈራራት ዝም ከማስደንገጥ አኳያ ጊዜያዊ የሆነ ትርፍ ልታገኝ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ የገባችበትን ችግር ቅንጣት ያኸል አይቀርፈውም።" ኢትዮጵያ ውስጥ በአሽከርካሪዎች፣ በተለይ ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል በሚመላለሱ ተጓዦች፣ በተለያዩ ባለሃብቶች ላይ ታጣቂዎች እገታ ይፈጽማሉ። በሌላ በኩል በጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ተሳትፎ ባላቸው ግለሰቦች ላይ "ማንነታቸው በውል ያልታወቁ" በሚል እገታ፣ እሥር፣ መሰወር ተፈጽሞባቸው፣ ቆይቶም ተለቀቁ ከመባል በቀር የድርጊቱ ፈፃሚ ማን ነው? ለምን ተደረገ? ተጠያቂነቱስ የሚሉ ጉዳዮች ተዳፍነው ሲቀሩ እየተስተዋለ ነው። ይህ አሳሳቢ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጠድ የሚደረገው ውትወታ እና ጩኸትም አልተቋረጠም።
ሰለሞን ሙጩ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ