1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አስገድዶ መሰወር፣ እገታ እና እየደረሰ ያለው ቀውስ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

መደበኛ ባልሆነ ማቆያ ቦታ ተይዘው ለሚቆዩ፣ ያሉበት ሳይገለጽ እንዲቆዩ ለሚደረጉ እና አስገድዶ መሰወር ለሚፈፀምባቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው ፍትሕ እንዲሰጥ፣ ተጠያቂነትም እንዲሰፍን ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ፎቶ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

አስገድዶ መሰወር፣ እገታ እና እየደረሰ ያለው ቀውስ

This browser does not support the audio element.

 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ መሆናቸው የተገለጸ ከ52 በላይ ሰዎችን አቤቱታዎች መመርመሩን አስታውቋል።

ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት «በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን» ያስታወቀው ኮሚሽኑ የፀጥታ አካላት ከተያዙ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር ድርድር በማድረግ ሁኔታውን የገንዘብ ማግኛ ምንጭ የማድረግ ሕገ ወጥ ድርጊት መታየቱንም አስታውቋል።

«የመንግሥት አካል እንደዚህ ያደርጋል ብለን አላሰብንም» - የተጎጂ ቤተሰብ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የአስገድዶ መሰወር ሁኔታ፣ ሰዎችን ያሉበትን ሳይገልጹ በተራዘመ እስር ውስጥ ማቆየት አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ገልጿል።

ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ መሆናቸው የተገለጸ ከ52 በላይ ሰዎችን አቤቱታዎች መመርመሩን እና እስከ ዛሬ ድረስ 44 ሰዎች ከአንድ ወር እስከ ዘጠኝ ወራት በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን ለማወቅ መቻሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።

አዲስ አበባ ውስጥ የቤተሰባቸው አባል ለረጅም ወራት በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ታሥሮ የቆየባቸው አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ቤተሰብ በወቅቱ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ወድቀው እንደነበር ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። «የመንግሥት አካል እንደዚህ ያደርጋል ብለን አላሰብንም»።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መደበኛ ባልሆነ ማቆያ ቦታ ተይዘው ለሚቆዩ፣ ያሉበት ሳይገለጽ እንዲቆዩ ለሚደረጉ እና አስገድዶ መሰወር ለሚፈፀምባቸው ፍትህ ጠይቋል።ፎቶ ከማኅደርምስል YAY Images/imago images

ዎች የሚያዙበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት «ተገቢውን የሕግ ሥነ- ሥርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን እና በእሥር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውኃ የማይቀርብላቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ለየብቻቸው ተለይተው ተይዘው የቆዩ መሆናቸውን» ማስረዳታቸውንም ብሔራዊ የመብት ድርጅቱ አረጋግጧል። በኢሰመኮ የሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማይ የታሰሩዎችን የአያያዝ ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸውልናል።

«ከሥራ ቦታ ሊሆን ይችላል፣ ከመኖሪያ ሊሆን ይችላል። እንደዚሁም አንዳንዶች ደግሞ በሥራ ላይ መንገድ ላይ እያሉ ሊሆን ይችላል»።

በማቆያ ቦታዎች የደረሱ የመብት ጥሰቶች 

ኢሰመኮ አክሎም ሁሉም ተጎጂዎች መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች «መሠረታዊ የመጸዳጃ፣ የመኝታ እና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦቶች አለመኖራቸውን፣ የቤተሰብ ሁኔታን ማወቅ ሳይችሉ እና ለቤተሰብ ያሉበት ቦታ ሳይገለጽ፣ እንዲሁም ምግብ እና የመጠጥ አቅርቦቱ እጅግ የተጓደለበት ቦታ የቆዩ መሆናቸውን» መግለፃቸውም ተጠቅሷል።

ለሰባት ወራት አካባቢ ተይዞ መቆየቱን ለኮሚሽኑ የገለጸ አንድ ታሳሪ በስፍራው 60 ያህል ሰዎች ተይዘው እንደነበር መመልከቱን እና መረጃ አውጣ በሚል ድብደባ እንደተፈፀመበት ተናግሯል። ያነጋገርናቸው ቤተሰባቸው ታስሮባቸው የነበረ ግለሰብም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

«ከፍተኛ ድብደባ፣ ረሀብ፣ ስድብ፣ አንድ ወር ከሰው ለይተው ጨለማ ውስጥ ነበር ያሰሩት»።
መሰል ድርጊቶች እንዲቆሙ ስለመጠየቁ

ኮሚሽኑ ይህንን መሰሉ ድርጊት እንዲቆምና ለተጎጅዎች ፍትሕ እንዲሰጥ፣ ተጠያቂነትም እንዲረጋገጥ ጠይቋል። በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት የሚኒስትሩ ዶክተር ለገሠ ቱሉ ስልክ ባለመስራቱ ማካተት አልቻልንም። የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ መሰል ድርጊቶች «ሰዎች በቀጥታ ከሚደርስባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪ፣ በቤተሰቦች ላይ የሚደርሰው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣እንዲሁም እውነቱን የማወቅ መብት ጥሰት እና ተያያዥ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የድርጊቱን አስከፊነት ያባብሰዋል» ሲሉ ዘላቂ እርምት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW