አስጨናቂው አዲስ የጣሊያን የስደተኞች አዋጅ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 5 2015
በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች ወደተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ለመሻገር አለያም በዚያው ለመቅረት ጣሊያንን ዋነኛ መዳረሻቸው አድርገው ይወስዳሉ ። ብዙዎች እጅግ ለከፋ የባሕር ላይ እልቂት ሲዳረጉም በተደጋጋሚ ይስተዋላል ። እንዲያም ሆኖ ግን ፍልሰቱ ሄድ መለስ እያለ ወቅቶችን ይጠብቅ እንጂ አልተቋረጠም ። ከሰሞኑ የጣሊያን ምክር ቤት ወደ ሀገሩ የሚገቡ ብሎም በሀገሩ ውስጥ የሚገኙ ሕገወጥ የሚላቸውን ስደተኞች ለመቀነስ የሚረዳውን አዲስ አዋጅ ደንግጓል ። ሕገወጥ ስደትን ለመቀልበስ በሚል በሀገሪቱ የወጣው አወዛጋቢው አዋጅ በጣሊያንኛ (Cutro decree) ይሰኛል ።
ደቡባዊ ጣሊያን ካላባሪያ የተሰኘው አውራጃ ውስጥ የምትገኘውን ከተማ ስም በመውሰድም ነው አዋጁ ስያሜውን ያገኘው ። በዚህች ኩትሮ በተሰኘች ከተማ ባለፈው የካቲት ወር የስደተኞች ጀልባ ሰጥማ ከ90 በላይ ሰዎች የባሕር ሲሳይ ሆነዋል ። አዲሱ የጣሊያን የስደተኞች አዋጅ ጣሊያን ውስጥ የስደተኛነት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞችን ባለሥልጣናት የልዩ ጥበቃ ፍቃድ እንዳይሰጧቸው በእጅጉ እጅ የሚዘመዝዝ ነው ተብሏል ።
ጣሊያን ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ42,000 በላይ ሕገወጥ ስደተኞችን መዝግባለች ። ከባለፈው ዓመት የአምስት ወራት መረጃ ጋር ሲነጻጸር ይህ በአራት እጥፍ ከፍ ያለ ቁጥር ነው ። የቀኝ አክራሪዎች የሚበዙበት የጣሊያን አዲሱ መንግሥት የልዩ ጥበቃ ፈቃዱ አገልግሎት ፍልሰተኞች አደገኛውን የባሕር ላይ ጉዞ ደፍረው ወደ ሀገሪቱ እንዲጎርፉ የሚያበረታታ ነው ይላል ።
በጣሊያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ባለሥልጣን የሆኑት ቀኝ አክራሪው ሊግ ፓርቲ አባል ኒኮላ ሞልቴኒ፦ «የልዩ ጥበቃ ፈቃድ ለፍልሰተኞች ሳቢ የሆኑ ሁኔታዎችን ስለሚፈጥር እናስወግደዋለን» ሲሉ መናገራቸው በርካታ በጣሊያን የሚኖሩ ስደተኞችን እጅግ አስደንግጧል ።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ «የጣሊያን ወንድማማቾች» የተሰኘው ቀኝ አክራሪ ፓርቲ አባል እና የሀገሪቱ የእርሻ ሚንስትር ፍራንቼስኮ ሎሎብሪጊዳ ሰሞኑን ያሉት ደግሞ በነበረው ውጥረት ላይ ሌላ ውስብስብ ጉዳይ አጭሯል ። ሚንስትሩ የጣልያን ሕዝብ በፍልሰተኞች «እየተቀየረ ነው» ሲሉ አወዛጋቢ ንግግር ማሰማታቸው በብዙዎች ዘንድ ዘረኛ አስብሏቸዋል ።
ከአዋጁ በፊት የልዩ ጥበቃ ፈቃድ የተፈቀደላቸው ሰዎች ጣሊያን ውስጥ ለሁለት ዓመታት መኖር ይችሉ ነበር ። የመኖሪያ ፈቃዳቸውን አድሰውም ወደ ሥራ ፈቃድ መቀየርም ይችሉ ነበር ። ይህ ፈቃድ ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ ለሕይወታቸው እጅግ የሚያሰጋቸው፤ ጦርነት እና የተፈጥሮ አደጋን የሸሹ ስደተኞችን ከለላ የሚሰጥ ነው ። ጣሊያን ውስጥ የቤተሰብ አባል ያላቸው ወይንም በኤኮኖሚ ራሳቸውን ለሚደግፉም ታስቦ የተዘጋጀ ነበር ።
በአሁኑ ወቅት ግን ያ በሙሉ ተቀይሯል ። በእርግጥ የልዩ ጥበቃ ፈቃዱ አገልግሎት የቁም ስቅል ሊገጥማቸው፤ ኢሰብአዊ ድርጊት ሊፈጸምባቸው አለያም ስልታዊ በሆነ መልኩ የሰብአዊ መብታቸው ሊጣስባቸው ለሚችሉ ስደተኞች ተግባራዊ ነው። ሆኖም አዲሱ አዋጅ ጣሊያን ውስጥ የቤተሰብ አባል ያላቸው ወይንም በኤኮኖሚ ራሳቸውን የሚደግፉ ስደተኞች እንደ በፊቱ የልዩ ጥበቃ ፈቃድ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው ። በጣሊያን ፓዶቫ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር ፓዎሎ ዴ ሽቴፋኒ ።
«አንድ ሰው በሀገሩ እጅግ ከፍተኛ የአደጋ ሥጋት ባይኖርበት ግን ደግሞ በአሁኑ ወቅት ጣሊያን ውስጥ ቤተሰብ መስርቶ ልጆች ቢኖሩት የመኖሪያ ሁኔታውን የሚመለከተው ኮሚሽን ስደተኛው የልዩ ጥበቃ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው አድርጎ አይወስደውም።»
አዲሱ አዋጅ የተፈጥሮ አደጋን ሸሽተው አለያም የሕክምና ክትትል ለማድረግ ጣሊያን የገቡ ፍልሰተኞች ላይም ተጽእኖ የሚያሳርፍ ነው ። ከምንም በላይ እንደበፊቱ በልዩ ጥበቃ ፍቃድ መሠረት የሥራ ፈቃድ ማውጣት አይችሉም ።
በመቀበያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ የቋንቋ ትምሕርት እና ሕጋዊ አገልግሎቶች አይኖሩም ። ያለአዋቂዎች ብቻቸውን ስደት የገቡ ልጆች ላይም ነገሮች መቀየራቸው አይቀርም ። እንዲህ አይነት ልጆች የልዩ ጥበቃ ፈቃድ አገልግሎት ቢያገኙም ቅሉ ልክ 18 ዓመት ሲሞላቸው ግን ጥበቃው ይነሳባቸዋል ። ከዚያ ለአንድ ዓመታ ፈቃዱን ማራዘም ይችሉ ይሆናል ። ግን ወደ ሥራ ፈቃድ እንደ በፊቱ መቀየር አይችሉም ። አዋጁ ልጅ አዋቂ ሳይል የፍልሰተኞችን ተስፋ የሚያጨልም ነው ሲሉም ባለሞያዎች ይነቅፉታል ።
አዲሱ አዋጅ ፍልሰተኞች እንዳይፈናፈኑ በማድረግ እጅግ ጥብቅ ቢሆንም ያለ ፈቃድ ለጋብቻ በመገደዳቸው የተሰደዱ ሰለቦች ግን የልዩ ጥበቃ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያመለክቱ ይፈቅዳል ። ምንም እንኳን አዲሱ አዋጅ የልዩ ጥበቃ ፈቃድ ያላቸው እና ለአገልግሎቱ ያመለከቱት ላይ ተግባራዊ አይደረግም ቢባልም ሁኔታው ለፍልሰተኞች አባጣ ጎርባጣ እንዲሆን ተብሎ የተዘጋጀ ነው በሚለው ብዙዎች ይስማማሉ ።
ሳርያ ኩባሊ በአሁኑ ወቅት የልዩ ጥበቃ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ጋቦናዊ ነው። ቀኝ አክራሪዎች ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ጣሊያን የድሮዋ ጣሊያን አይደለችም ይላል ። ያም በመሆኑ ከጣሊያን መውጣት ይሻል ። ምንም እንኳን ጣሊያን ውስጥ በኑሮው ደስተኛ ቢሆንም ሁኔታው ግን እጅግ እንዳሳሰበው ከዶይቸ ቬለዋ ማርታ ሲልቫ ቪጋኖ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ተናግሯል ። ሳርያ ኩሊባሊ በልዩ ጥበቃ ፈቃድ አገልግሎት መሠረት የሥራ ፈቃድ ቢኖረውም ይህን ዕድል ሌሎች አለማግኘታቸው ያሳስበዋል ።
«ልዩ ጥበቃ የምር ሕይወትህን ይቀይርልሀል ። እንድትሠራ፤ እንድትማር ይፈቅድልሀል ። በዚያ ከለላ ብዙ ነገሮችን መሥራት እና መስጠትም ትችላለህ ። ሰዎች ርዳታ ካስፈለጋቸው መርዳት ያስፈልጋል እንጂ የበለጠ እንዲከብዳቸው ማድረግ አይደለም የሚያሻው ። ለሰብአዊነት ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል ። »
ጣሊያን ለስደተኞች የልዩ ጥበቃ ፈቃድ አገልግሎትን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2018 እስከ 2020 ድረስ በቀድሞው የሀገር ውስጥ ሚንሥትር ማቴዎ ሳልቫኒ እንዲቋረጥ ከማድረጓ በስተቀር ምንጊዜም ትሰጥ ነበር ። ምንም እንኳን የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ የሚሉት ሌላ ቢሆንም ከጣሊያን ውጪ አውሮጳ ውስጥ 18 ሃገራት ከልዩ ጥበቃ ፈቃድ ጋር የሚመሳሰል አገልግሎት ይሰጣሉ ።
ጣሊያን የልዩ ጥበቃ ፈቃድ አገልግሎትን በእጅጉ መገደቧ ፍልሰተኞች ያለ ሠነድ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ተደብቀው መኖር እንዲጀምሩ ያደርጋል፤ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ፍልሰተኞች መሠረታዊ መብቶችንም ይገፍፋል ሲሉ ተቺዎች ያስጠነቅቃሉ ። በተለይ ደግሞ አዲሱ አዋጅ ሌላ አዲስ አዋጅን የሚያስከትል መሆኑም ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ። ወደፊት ከሜድትራኒያን ባሕር ስደተኞችን ከሞት የሚታደጉ መርከቦች ላይ የሚሠሩ በጎ ፈቃደኞች እንቅስቃሴንም ይገድባል ። ጣሊያን የስደተኞችን ፍሰት ለመቀልበስ በሚል ባለፈው ወር ለግማሽ ዓመት የሚቆይ የአስቸኳይ አዋጅ ደንግጋለች ።
የሕግ ፕሮፌሰሩ ፓዎሎ ዴ ሽቴፋኒ የጣሊያን አዲሱ አዋጅ በርካታ ስደተኞች ከማኅበረሰቡ ጋር እንዳይቀላቀሉ የሚያደርግ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል ። ያም ብቻ አይደለም ። ስደተኞች ጣሊያን ውስጥ በቂ ጥበቃ እንዳይደረግላቸው በማድረግ ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት የተሻለ ጥበቃ ፍለጋ እንዲፈልሱ ያለመ ነውም ሲሉ ተችተውታል ።
እንደ ቀድሞ የጣሊያን መንግሥት መሪዎች ሁሉ አዲሷ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ አውሮጳውያን ሃገራት ጣሊያን ውስጥ ያለውን የፍልሰተኞች ፍሰት በተቀናጀ መልኩ እንዲጋሩ ይፈልጋሉ ። አዲሱ አዋጅ አደጋ ይዞ መምጣቱን ፕሮፌሰር ፓዎሎ ዴ ሽቴፋኒ ይናገራሉ ።
«ይህ አዲስ ሕግ አውሮጳ የፍልሰተኞችን ጉዳይ ከልብ እንድትመለከተው ጫና ለማሳደር ጥቅም ላይ የዋለ አድርጎ መመልከት ይችላል። ግን ደግሞ በሌሎች ሕይወት መቆመርም ነው ።»
አዲሱ አዋጅ «ኩትሮ ዲክሪ» የሚመለከታቸው በርካታ ኤርትራውያን፤ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ስደተኞች ጣሊያን ውስጥ ይኖራሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ማርታ ሲልቫ ቪጋኖ
ሸዋዬ ለገሰ