1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አቅም የሚፈትነው የጤና አገልግሎት

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ ኅዳር 30 2018

የፊታችን ሐሙስ በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር ዲሴምበር 12 ቀን ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን ቀን ይታሰባል። የተመድ የዘንድሮው ዓመታዊ ቀን ሲታሰብ በተለይ ከአቅም ጋር የተመጣጠነ ህክምናን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ትኩረት እንዲሰጠው ከወዲሁ አሳስቧል።

የልብ ምት ማዳመጫ
የተመድ የህክምና አገልግሎትን ለሁሉም የማዳረስን ወሳኝነት የሚያሳስብበት ዓለም አቀፍ ቀን በጎርጎሪዮሳዊው የቀመን ቀመር ዲሴምበር 12 ቀን ይታሰባል። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ David Herrarez/Zoonar/picture alliance

አቅም የሚፈትነው የጤና አገልግሎት

This browser does not support the audio element.

 

የተመድ በመላው ዓለም ደረጃ በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ.ም. ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ብሎ ከዘረዘራቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማዳረስን ይመለከታል። የተባለው ዓመት ሊደፍን የቀሩት አምስት ዓመታት ብቻ ናቸው። ሆኖም ግን ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ዛሬም መሠረታዊ የሚባሉትን የጤና አገልግሎቶች ገና ማግኘት አለመቻሉን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ለህክምና የሚጠየቀው ክፍያ ደግሞ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።

የፊታችን ሐሙስ በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር ዲሴምበር 12 ቀን ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን ቀን ይታሰባል። የተመድ የዘንድሮው ዓመታዊ ቀን ሲታሰብ በተለይ ከአቅም ጋር የተመጣጠነ ህክምናን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ትኩረት እንዲሰጠው ከወዲሁ አሳስቧል።

የጤና አገልግሎትን ለሁሉም የማዳረስ እንቅስቃሴ

ዘላቂ የልማት ግቦች ተሳክተዋል ለማለት የጤና አገልግሎት ለሁሉም በተመጣጣኝ ዋጋ መዳረስ ሲችል እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ህክምና ማግኘት ካልቻሉ ለከፋ የጤና ችግር እንዲሁም ለከፍተኛ ወጪ ለሚያስፈልገው የጤና እክል እንደሚዳረጉም ያሳስባል። አንድ መንግሥት ለሚያስተዳድረው ሕዝብ አቅሙን ያገናዘበ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል አልሞ ሠራ ማለት በሁሉም ዘርፍ ዘላቂነት ላለው ልማት እና እድገት መሠረት ጣለ ማለት መሆኑንም ያስረዳል።

የተመድ በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓም ላይ ለማሳካት ካቀደው ዘላቂ የልማት ግብ የጤናው ዘርፍ ዋነኛው ነው። ሆኖም የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ዛሬም ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወገን ገና መሠረታዊ እና እጅግ አስፈላጊ የሚባሉትን የጤና አገልግሎቶች አላገኘም።

ስለጤና አገልግሎት ሲነገር አሳሳቢው ጉዳይ ለብዙሃኑ አለመዳረሱ ብቻም አይደለም። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በመላው ዓለም ከአራት ሰዎች አንዱ ለህክምና የሚጠየቀውን ገንዘብ ከፍሎ ለመታከም ፍዳውን ይበላል።

አስተያየታቸውን የሰጡት ወገኖች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሲቲስካን ባሉ የህክምና መመርመሪያ መሣሪያዎች ለመታየት ረዥም ቀጠሮ በጠበቅ ግድ ነው። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Lazarenka Sviatlana/Zoonar/picture alliance

የህክምና አገልግሎት ወጪ

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የህክምናውን አገልግሎት ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይነገራል። ወደ ህክምናው ሙያ የሚገቡ ወጣቶች ቁጥርም በአንጻራዊነት እየጨመረ መሆኑም እንዲሁ። በመንግሥት በኩል የጤና ተቋማት በየቦታው እንዲበራከቱ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ኅብረተሰቡም የሚገልጸው ጉዳይ ነው። የመሠረተ ልማቱ መስፋፋት ይበል የሚያሰኝ ሆኖ አገልግሎቱ ላይ የሚነሱ ጉድለቶች መኖራቸውን ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ።

ያለውን የህክምና አገልግሎት በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚገባ የገለጹልን አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት አገልግሎቱን ከመንግሥትም ሆነ ከግል የህክምና ተቋማት ማግኘት ቢቻልም በሚጠየቀው ክፍያ ምክንያት አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሄደው ወደ መንግሥት ተቋማት ነው። እዚያ ደግሞ በአንድ በኩል ወረፋው ታማሚዎችን ሲያጉላላ፤ የሚታዘዙ መድኃኒቶች አለመገኘታቸው ደግሞ ሌላው ፈታኝ ችግር ነው ይላሉ። 

የሐረር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪም የሚገልጹት ችግር ተመሳሳይ ነው። በግል የህክምና ተቋማት ምንም እንኳን የተሻለ አገልግሎት ቢገኝም በክፍያው ከፍተኛነት ምክንያት ወደ መንግሥት ሀኪም ቤት የሚሄደው የኅብረተሰብ ክፍል እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ለሁሉም መዳረስ እንዳለበት የሚታመነው የህክምና አገልግሎት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችእንዲያገኙ የሚደረግ ጥረት መኖሩን ነው አስተያየት የጠየቅናቸው ወገኖች የጠቆሙን። በአማራ ክልል ወሎ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ እሳቸው ባሉበት አካባቢ አቅም ለሌላቸው ወገኖች የጤና አገልግሎቱን ለማዳረስ የጤና መድህን በአሁኑ ጊዜ እየተገዛ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸውልናል።

ይህ የጤና መድኅን ዋስትና አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ ለሚያስፈልገው የኅብረተሰብ ክፍል የተመቻቸ እድል እንደሆነ ነው የሚነገረው። ይህ ተጨምሮ በሲዳማ ክልል ኅብረተሰቡ ለጤና አገልግሎት ያሉትን አማራጮች በመለከተ የሀዋሳው ነዋሪ ያስተዋሉትን አጋርተውናል።

ሰሞኑን እሷና ልጇ በምግብ መመረዝ ምክንያት ወደ ሀኪም ቤት የሄዱበት አጋጣሚ መኖሩን የገለጸችልን አስተያየቷን የጠየቅናት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ፤ በግል የህክምና ተቋማት ለመታከም ለብዙዎች የማይታሰብ ነው ትላለች። ግን ደግሞ እሷ እንደምትለው በዚህ ወቅት ለብዙኀኑ የኅብረተሰብ ክፍል በመንግሥታዊ የጤና ጣቢያዎች የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እየተሻለለ በመሄድ ላይ ነው። የመድኃኒት አቅርቦት ጉዳይን በሚመለከት ያለው ችግር ግን ተመሳሳይ እንደሆነ ታስረዳለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት የህክምና ተቋማት ለታማሚዎች በሀኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን ማግኘት ዋነኛው ተግዳሮት እንደሆነ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ያካፈሉ ወገኖች ከገለጿቸው የህምናው አገልግሎት ችግሮች አንዱ ነው። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Jan Woitas/dpa-Zentralbild/picture alliance

ታካሚዎችና ሀኪሞች የሚጋሩት ትዝብት

ህክምና ፈላጊዎቹ ወገኖች የሰጡትን አስተያየት በህክምናው አገልግሎት ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ይጋሩታል። ካነጋገርናቸው የህክምና ባለሙያዎች መካከል በድምፅ መቅረብ ያልፈለጉት ዶክተር እንደገለጹልን በአሁኑ ጊዜ የህክምናውን አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት በዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች የታጀበ ነው። ህክምና ፈላጊ ወገኖች እንደተናገሩት የገንዘብ አቅም ያለው በግል የህክምና ተቋማት የተሻለ አገልግሎት እንደሚያገኝ ነው እሳቸውም ያረጋገጡልን። በመንግሥት የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያስተዋሉትን ችግር ደግሞ በሁለት ይከፍሉታል። በአንድ በኩል የባለሙያዎች የሙያ ብቃት እና ከሚከፈላቸው አኳያ ያለው ተነሳሽነት መቀዛቀዝ ሲሆን በሌላው በኩል ደግሞ የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች አቅርቦት እጥረት ለሚታየው ችግር መሠረታዊ ምንጮች እንደሆኑ አመልክተዋል።

ሌላው ተሞክሯቸውን ያካፈሉን የህክምና ባለሙያም ታካሚዎች ያነሷቸውን ችግሮች ይጋራሉ።  በተለይ በአንዳንድ የመንግሥት ሀኪም ቤቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችንም እሳቸው በቅርብ ያስተዋሉትን መነሻ በማድረግ ሲገልጹም፤ የህክምና መሣሪያዎች አቅርቦትና የአገልግሎት ሁኔታን፤ የመመርመሪያ መሣሪያዎች በየጊዜ መበላሸትና የመሳሰሉትን ይዘረዝራሉ።

ጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ለማሳያነት ይጠቀስ እንጂ እንዲህ ያለው ችግር በዋና ከተማ አዲስ አበባ ሳይቀር እንደሚታይ ነው ታካሚዎች የሚናገሩት። የግል ተሞክሮውን ያካፈለን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እንደሚለው አንዳንድ እጅግ አስፈላጊ የህክምና ምርመራዎችን በመንግሥት ሆስፒታሎች ለማሠራት ረዥም ወረፋና ጊዜ መጠበቅ ግድ ነው።

አስተያየታቸውን የሰጡን የዘርፉ ባለሙያ ያነሱት ችግር ግን በህክምና መሣሪዎች ሥራ መስተጓጎል ብቻ የሚያበቃ ብቻ አይደለም የህክምና ባለሙያዎችን የሚመለከተው ተግዳሮትም ሌላው በአገልግሎቱ ላይ ጫና አሳድሯል ነው የሚሉት።

እሳቸው እንደሚሉት የመድኀኒት እጥረት የሚፈጠረው በሁለት ምክንያት ነው። ከመነሻው የአቅርቦት ችግር እና በሙስና አሠራር መድኃኒቶች ሀኪም ቤት ውስጥ እንደገቡ ወዲያው ወደ ግለሰብ እንዲዛወሩ የሚደረግበት ሕገወጥ አካሄድ መኖሩን ያስረዳሉ።

የተመድ የህክምና ዋጋ መወደድ የብዙዎችን ሕይወት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ያሳስባል። ዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎትን ለሁሉ የማዳረስ ቀንን የማሰቡ ዋና አላማም ብዙዎቹ ባለድርሻ አካላት ተባብረው ጠንካራ የጤና ስርዓት እንዲፈጠር ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ ግንዛቤን መፍጠር መሆኑን ገልጿል። ለዚህ ደግሞ የየሃገራቱ መሪዎች በጤናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ እና ብልህነትን የተላበሰ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት እንዲያደርጉ ጠይቋል። በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ,ም የታሰቡትን ዘላቂ የልማት ግቦችም ሊሳኩ የሚችሉት በዚህ መሆኑም አመልክቷል።

አስተያየታቸውን ያጋሩንን እናመሰግናለን፤ የእናንተን ተሞክሮም ልታካፍሉን ትችላላችሁ።

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW