1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አበዳሪን ከተበዳሪ ያገናኘው የቻይና አፍሪካ ዘጠነኛ የትብብር ፎረም

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ መሪዎች የሚሳተፉበት ዘጠነኛው የቻይና አፍሪካ ፎረም ዛሬ በቤጂንግ ተጀምሯል። ቻይና ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ዋና አበዳሪ ሆናለች። አንጎላ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ናይጄሪያ ከቻይና በቢሊዮኖች ዶላሮች በመበደር ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ በቤጂንግ ተገናኝተው ተወያይተዋልምስል Yin Bogu/Xinhua/IMAGO

አበዳሪን ከተበዳሪ ያገናኘው የቻይና አፍሪካ ዘጠነኛ የትብብር ፎረም

This browser does not support the audio element.

ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቤጂንግ ሲገናኙ የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት በአፍሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ወዳጃዊ ትብብር ጥሩ ምሳሌ አድርገው አቅርበውታል። ኢትዮጵያ ከጦርነት በኋላ የምታደርገውን መልሶ ግንባታ፣ ዕድገት እና መነቃቃት ለመደገፍ ቻይና ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ፕሬዝደንቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ተግባራዊ ትብብር ለማስፋት ሀገራቸው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረምን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን እንደተናገሩ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ባቡር እና ባሕርን የሚያስተሳስር የኢንተርሞዳል የትራንስፖርት አውታር በመዘርጋት የቀጠናው የትራንስፖርት ማዕከል ጥንካሬዋን በማጎልበት ተጠቃሚ እንድትሆን ቻይና እንደምታግዝም ቃል ገብተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ቻይና ኢትዮጵያን በተመለከተ የምትከተለውን ፖሊሲ አድንቀዋል። የቻይና ኢንተርፕራይዞች መዋዕለ-ንዋይ እና ትብብር ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ጠቃሚ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ መናገራቸውን የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ይጠቁማል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዘጠነኛው የቻይና አፍሪካ ፎረም ለመሳተፍ ቤጂንግ የገቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀሥላሴ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የተካተቱበትን ልዑካን ቡድን አስከትለው ነው።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉ ከኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እስከ ጅቡቲ አቻቸው ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ፤ ከዚምባብዌው ኤመርሰን ምንጋግዋ እስከ ደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎሳ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ቤጂንግ ሲደርሱ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የዘንድሮው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ዘጠነኛው ዙር ነው።

የዚምባብዌው ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምንጋግዋን ጨምሮ የአፍሪካ መሪዎች ቤጂንግ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ምስል Huang Jingwen/Xinhua/Imago Images

ከጉባኤው በፊት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ከቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ጋር ባደረጓቸው የተናጠል ውይይቶች የተለያየ ፍላጎት እንዳላቸው ታይቷል። ሁሉም ግን ከቻይና ጠቀም ያለ ብድር መውሰዳቸው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ነው።

የቻይና ባለሥልጣናት በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን በቀይ ምንጣፍ እና ሰንደቅ ዓላማዎቻቸውን በሚያውለበልቡ ሕጻናት ሲቀበሉ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎቻቸው ያከናወኗቸው ሥራዎች በኩራት የሚጠቅሷቸው ናቸው።

ከቻይና ብሔራዊ ልማት እና ማሻሻያ ኮሚሽን ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት ሹ ጄንፒንግ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ባለፉት አስራ አንድ ዓመታት የቻይና ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከ10,000 ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መንገድ፣ ከ100,000 ኪሎ ሜትር በላይ አውራ ጎዳና” ግንባታ እና እድሳት እንደተሳተፉ ተናግረዋል። 

በአፍሪካ የቻይና ኩባንያዎች ከተሳተፉባቸው ግንባታዎች ሹ ጄንፒንግ እንዳሉት “ከአንድ ሺሕ በላይ ድልድዮች፣ ከመቶ በላይ ወደቦች፣ 66,000 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያዎች እና 150,000 ኪሎ ሜትር የጀርባ አጥንት ሊባሉ የሚችሉ የኮምዩንኬሽን ኔትወርክ” ይገኙበታል።

ኃላፊው በኬንያ ከሞምባሳ እስከ ናይሮቢ፣ የኢትዮጵያ ጅቡቲ፣ በናይጄሪያ ከሌጎስ እስከ ኢባዳን በቻይና ኢንተርፕራይዞች የተገነቡ የባቡር ማጓጓዣዎች “አፍሪካ የባቡር ሐዲድ አውታር በብቃት እንድትፈጥር አግዘዋታል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ሹ ጄንፒንግ የጠቀሱት የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ነበር። ኢትዮጵያ ከቻይና የወጪ እና እና ገቢ ንግድ ባንክ በተበደረችው 4 ቢሊዮን ዶላር የተገነባው የባቡር ማጓጓዣ ሥራ የጀመረው በጥር 2010 ነው። ይሁንና የባቡር መጓጓዣው እስካሁን ስኬታማ ሆኖ ዕዳውን መክፈል የሚችልበት አቅም አላበጀም።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ካሉት 32 የጭነት ሎኮሞቲቮች የሚሠሩት 15 ብቻ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ታከለ ዑማ በቅርቡ አስታውቀዋል። ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ካሉት 32 የጭነት ሎኮሞቲቮች የሚሠሩት 15 ብቻ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ታከለ ዑማ በቅርቡ አስታውቀዋል። ኩባንያው በዓመት 6.3 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማጓጓዝ ዕቅድ ቢኖረውም የተሳካለት 2.4 ሚሊዮን ቶን ወይም ከውጥኑ 38 በመቶ ብቻ እንደሆነ አቶ ታከለ ገልጸው ነበር።

“...የባቡር መስመሩ መላ ካገኘ...”

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኢትዮጵያ በቻይና ብድር ከገነባቻቸው የተሰናከሉ ዕቅዶች አንዱ ነው። ከአያት አደባባይ እስከ ጦር ኃይሎች፤ ከዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ እስከ ቃሊቲ የተዘረጉ ሁለት መስመሮች ያሉት የባቡር አገልግሎት እንደ ታቀደው የዋና ከተማዋን የመጓጓዣ እጥረት መፍታት አልተሳካለትም። የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌክሳንደር ደምሴ በብድር ለተገነቡት ዕቅዶች መሰናከል “ቻይናን በቀጥታ መውቀስ አንችልም” የሚል አቋም አላቸው።

“በአዲስ አበባ ያለው ቀላል ባቡር ኢትዮጵያ እና ቻይና እንዴት ያለ መለዋወጫ ዕቃ ሊፈራረሙ ቻሉ? እንደምናውቀው ከሆነ የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት የድርድሩ አካል አልነበረም” የሚሉት አቶ አሌክሳንደር ችግሩ የፕሮጀክቶቹ ባለቤት እንደሆነ ይተቻሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚሉት የባቡር መጓጓዣው የንድፍ ችግር ጭምር ነበረበት። በ2008 ሥራ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በቻይና የባቡር ምኅንድስና ግሩፕ (China Railway Engineering Group) የተገነባ ነው። ለግንባታው 475 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሆነበት የባቡር አገልግሎት ህልውና ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

በተለይ ከአያት አደባባይ እስከ ጦር ኃይሎች የተዘረጋው የባቡር ማጓጓዣ ክፍል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሚያቀነቅኑት የኮሪደር ልማት ጋር ባለመጣጣሙ የሚነሳ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ሣምንታት በፊት በባቡር መስመሩ ምክንያት ከመገናኛ እስከ ሲኤምሲ ባለው አካባቢ የመንገድ ዳር ልማት ሲከናወን የፍሳሽ ቆሻሻ ማስተላለፊያ ለመገንባት ዕክል መፍጠሩን ተናግረዋል። 

“ከመገናኛ እስከ ሲኤምሲ ያለውን፤ መሀል ላይ ያስቸገረንን የባቡር መስመር ምን ማድረግ እንችላለን? የሚለውን እያየን ቆይተናል” ያሉት ዐቢይ “ውይይታችንን ከጨረስን በኋላ የባቡር መስመሩ መላ ካገኘ፤ ከመገናኛ ሲኤምሲ ያለው መንገድ በጣም ሰፊ፤ አራት አምስት መተላለፊያ ያለው ብዙ ትራንስፖርት ሊያሳልጥ ይችላል” ሲሉ ሊነሳ እንደሚችል በገደምዳሜ ጠቆም አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 475 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ነውምስል DW/E. Bekele

ኢትዮጵያ ከቻይና በተበደረችው ከፍተኛ ገንዘብ ተገንብተው ውጤታማ ሳይሆን የቀሩት ግን የባቡር ማጓጓዣዎቹ ብቻ አይደሉም። የታቀደላቸውን ዓላማ ማሳካት የተሳናቸው የስኳር ፋብሪካዎች የተገነቡት ኢትዮጵያ ከቻይና ተቋማት በወሰደችው ብድር ነው።

የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድን ጨምሮ ለግዙፍ አውራ ጎዳናዎች፣ ለድልድዮች፣ ፈጣን መንገዶች እና ለቦሌ አውሮፕላን ማረፈፊያ የእንግዶች መቀበያ ተርሚናል ማስፋፊያ ኢትዮጵያ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከወደ ቻይና ተበድራለች። ባለፉት ዓመታት ግን ኢትዮጵያ ከወደ ቻይና የምትበደረው ገንዘብ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል። “ለመቀዝቀዙ ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ ራሷ ነበረች” የሚሉት አቶ አሌክሳንደር ሀገሪቱ ብድሯን ለመክፈል መቸገሯ ዋንኛው ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ከዓለም ባንክ በተፈራረማቸው ሥምምነቶች የተበደረውን ሳይጨምር ሀገሪቱ 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ዕዳ ነበረባት። ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያክሉ ከቻይና የተበደረችው እንደሆነ ይታመናል።

በአሜሪካው ቦስተን ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የግሎባል ዴቬሎፕመንት ፖሊሲ ሴንተር መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከአንጎላ በመከተል ከፍተኛ የቻይና ተበዳሪ ሀገር ነች። በተቋሙ መረጃ መሠረት በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2000 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት አንጎላ 46 ቢሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ 14.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ግብጽ 9.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ናይጄሪያ 9.6 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና ተበድረዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአፍሪካ ሀገራት የምትሰጠው ብድር በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ መሔዱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች ታዝበዋል። የቦስተን ዩኒቨርሲቲ የሀገራት ብድር ጥናት ባለሙያዎች ቻይና ለአኅጉሪቱ የምትሰጠው ብድር የቀነሰው አበዳሪ ተቋሞቿን ከተበዳሪ ሀገራት ከሚመነጭ ሥጋት ለመከለል እንደሆነ ገልጸዋል። ቻይና ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገጠማት የኤኮኖሚ መቀዛቀዝም እንደ ከዚህ ቀደም ረብጣ ገንዘብ በብድር ከመስጠት እንድትቆጠብ እንዳስገደዳት ይታመናል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት እና የብረታ ብረት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከቻይና እንደሚተባበር በቤጂንግ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ተናግረዋል። ምስል Chen Zhonghao/Xinhua/Imago Images

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተባለውን የአራት ዓመታት መርሐ-ግብር ካጸደቀ በኋላ ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ የምታደርግበት ድርድር ይጠብቃታል። የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴን በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ብርቱ ዕዳ ቢጫነውም አሁንም ከፍተኛ መሠረተ-ልማቶች የመገንባት ዕቅድ አለው። ለዚህም ከፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ መንግሥት ጋር መተባበር እንደሚፈልግ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ተናግረዋል።

“ግብርናን ለማዘመን፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እና ተሰጥዖን ለማሳደግ መተባበር እንፈልጋለን። በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለግብርና ግብዓት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት፤ ኤኮኖሚያችንን እና መሠረተ-ልማት ለመገንባት የራሳችንን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ለማሳደግ እንፈልጋለን” ያሉት አምባሳደር ተፈራ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ጭምር ኢትዮጵያ ከቻይና መተባበር እንደምትፈልግ ጠቁመዋል።

የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ ኢትዮጵያ እንደከዚህ ቀደሙ ከቻይና ከፍተኛ ብድር የምትወስድበት አካሔድ እንደማይቀጥል ይስማማሉ። ካሁን በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመሩት ከግሉ ዘርፉ የተውጣጡ ኩባንያዎች እንደሚሆኑ አቶ አሌክሳንደር እምነት አላቸው።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ እንዳሉት ዘጠነኛው ፎረም ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ለወደፊቱ የቻይና አፍሪካ ትብብር የሀገራቸውን ዕቅድ የሚያስተዋውቁበት ነው። ፕሬዝደንቱ ከአፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር ለቻይና አፍሪካ ትብብር አዲስ ፍኖተ ካርታ እንዲሚቀርጹም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW