1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አብን ለመንግሥትና የፖለቲካ ኃይሎች ያቀረበው የሰላም ጥሪ

ዓለምነው መኮንን
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017

በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ባለድርሻ አካላት አገራዊ መግባባትንና ዘላቂ መፍትሔዎችን እንዲያመጡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠየቀ። በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ተባብሶ መቀጠሉንም ንቅናቄው አመልክቷል።

የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር
የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

አብን ለመንግሥትና የፖለቲካ ኃይሎች ያቀረበው የሰላም ጥሪ

This browser does not support the audio element.

 

የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ያደረገውን መደበኛ ስብሰባ ተከትሎ ክልላዊ፣ አገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ አብን በመግለጫው በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል ብሏል፣ በዜጎችና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ያለው አብን፣ አለመረጋጋቱንና ግጭቱን ተከትሎም የዝርፊያ ወንጀሎች በክልሉ ተስፋፍቷል ነው ያለው። አገራዊ ጉዳይን በተመለከተም «ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የበርካታ ፈተናዎች ማዕከል ሆናለች፣ የፀጥታ አለመረጋጋት፣ የኑሮ ውድነት እና የማኅበራዊ ትስስር መላላት የሀገሪቱን አንድነትና ሰላም አደጋ ላይ ጥለዋል።» ሲል በመግለጫው ጠቁሟል። 

እነኚህ ችግሮች እንዲፈቱና የአማራ ክልልም ሆነ መላ አገሪቱ ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ መወያየት እንደሚያስፈልግ የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ተናግረዋል። የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት ሰላም ለማናጋት የፕሮፓጋንዳ፣ የሴራና የጥፋት ስምሪት ይሰጣል ያለው የአብን መግለጫ፣ የኤርትራ መንግሥት ከድርጊቶቹ ባስቸኳይ እንዲታቀብ አብን አሳስቧል። 

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚፃረር ማንኛውንም ቀጠናዊ ተጽዕኖ ለመከላከል ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው አመልክተዋል። የባሕር በር ጥያቄን መላው ኢትዮጵያዊያን እና አደረጃጀቶች ሁሉ በፖለቲካና በርዕዮተ ዓለም ሳይለያዩ ሊታገሉለት የሚገባ ብሔራዊ ጥቅማቸው ነው ብሎ እንደሚያምንም አብን ገልጧል።

መገናኛ ብዙኀን በቃላት አጠቃቀም ረግድ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ርዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው አብሮነትንና ይቅርታ የሚጋብዙ ቃላትን መጠቅም ቅድሚያ እንዲሰጥ ተናግረዋል።

«... «ልክህን አሳይሀለሁ» እያልክ ለሰላም ዝግጁ ነኝ የለም፣ ለሰላም ዝግጁ ነኝ ስትል የሚደርስብኝን ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ ነኝ ነው ማለት የምትችለው፣ አገላለፆችና የብዙኀን መገናኛ ኮሚኒኬሽን ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፣ አብሮነትን የሚጋብዙ ቃላት ተግባር ላይ መዋል አለባቸው።» ብለዋል። 

የውጪ ጠላቶችን ለመመከት ብቸኛው መውጫ መንገድ ጠንካራ የሆነ አንድነት እና ሕብረት ነው፣ ያለው አብን ለመላ ኢትዮጵያውያን አንድነትን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አድርጓል።

በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ ወገኖችም የሰላም መንገድ ረጅም ቢሆንም የሕዝቦችን ዘላቂ ግብና ፍላጎት ለማሳካት የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጠይቋል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠናከር እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ መንግሥት በቁርጠኝነት እና በላቀ ተነሳሽነት እንዲሠራ አብን አሳስቧል።  

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW