አብኤል ግርማ ማናት?
ዓርብ፣ ጥር 2 2017አብኤል ግርማ ለዶቸ ቬለ በድምፅ ትወና አልፎ አልፎ ደግሞ በቴክኖሎጂ ላይ ያተኩሩ አጫጭር ቪዲዮዎችን በመስራት ተሳታፊ ናት። «ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በቲያትር የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ። ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው፤ ስራዬም ስለሆነ፤ ኪነ ጥበብ ላይ ነው የማተኩረው። የተለያዩ የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን እሰራለሁ። ብዙ አድማጮቻችን የእምነትን ገፀ ባህሪ ስለሚያውቁ እምነትን ሆኜ የምሰራውም እኔ ነኝ።»
ተዋናይ አብኤል የ 27 ዓመት ወጣት ስትሆን ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በቲያትር የተመረቀችው በ 2011 ዓ.ም. ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን ተጫውታለች። ለዶቸ ቬለ የምትጫወታት ገፀ ባህሪ እምነት የ2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ስትሆን ይህችም መምህርት በስልክ ሱስ ተጠምዳ በማስተማር ስራዋ ላይ ስለሚገጥማት ችግር እንዲሁም ከገጠማት ሱስ ለመላቀቅ በሀኪም እገዛ ስለምታደርገው ትግል ይተርካል።
«ፈታኝ የሆኑ ገፀ ባህሪያንትን መጫወት ያስደስተኛል »
ከዚህ በፊትም ብዙ የስራ ልምድ ያለኝ በድምፅ ትወና ነው የምትለው አብኤል የቃና ቴሌቪዥን ላይ ትሰራለች። «እዛም ብዙ ፈታኝ የሆኑ ገፀ ባህሪያት ይሰጡናል። ሳቅም ለቅሶም የሚያሳዩ፤ የዕለት ተዕለት ህይወታችን ላይ ያሉ ግን ፈታኝ ነገሮች ናቸው ። እንደነ ጀነት ያሉ ገፀ ባህሪያት እጫወታለሁ። የተለያዩ የህይወት ውጣ ውረዶችን የምታሳልፍ ገፀ ባህሪ ናት እና ስሜቷን እጋራለሁ። ስራው ስለሚፈትንም እወደዋለሁ።
የትወና ፍቅር
«ትወናን ከልጅነቴ ነው የጀመርኩት። ያደኩት ደብረዘይት የምትባለው ከተማ ነው። እዛም የተለያዩ እንደ ቤተሰብ መምሪያ እና የተለያዩ ክበባት ነበሩ። ከሰባት ዓመቴ አንስቶ እተውን ነበር። ከዛ ደግሞ በትምህርትም የታገዘ ሆነልኝ። እና ከልጅነቴ የነበረ ፍላጎት ነው»
ወጣቷ የድምፅ ትወና ላይ አተኩራ ትስራ እንጂ የቪዲዮ ትወና ላይም ተሳታፊ ናት። ከ 71 ሺ በላይ ተከታዮች ባላት የቲክቶብ ገጽ ላይም ቪዲዮዎን እየሰራች ታጋራለች።
«ቲክቶክ ተጨማሪ ነው። ከዛ በተጨማሪ በምስል ቲቪ ላይ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችንም እሰራለሁ። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ በቴሌቪዥን ድራማ እየመጣሁ ያለሁበት ሁኔታ አለ። » አብኤል ቴክኖሎጂ በቀላሉ የተሰኘው የዶቸ ቬለ አጫጭር ትምህርታዊ ቪዲዮችንም እየሰራች ትገኛለች።
«ያው ዶቸ ቬለ ብዙ አድማጭ እና ተመልካች ያለው ትልቅ ድርጅት ነው። እንደገና ደግሞ ማህበረሰቡን እንዴት እናንቃ በሚለው ጉዳይ ላይ ከከተማ እስከ ገጠር ዘልቆ የሰዎችን ችግር የሚያሳይ ትልቅ ድርጅት ነው። እዛም ላይ በመስራቴ በጣም እድለኛ ነኝ። የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ሁኔታ ሰዎች በሚገባቸው መንገድ አጭር በሆነ፤ ነገር ግን ብዙ ቁም ነገር አዘል ስራዎችን ለህዝብ የምናደርስበት ነው። ህዝቡ ብቻም ሳይሆን እኔም አንዳንድ አዳዲስ የማላቃቸውን ነገሮች ግንዛቤው እንዲኖረኝ አድርጓል።»
የበጎ ፍቃደኝነት ተሳትፎ
አብኤል በበጎ ፍቃደኝነት ስራዎች ትሳተፋለች። ለምሳሌ ሜቄዶንያ በማስተዋወቅ « ትልቅ ተቋም ነው። ወደ 42 ቅርንጫፎች አሉ፤ በተለያዩ ከተሞች እየተከፈቱ ያሉ። እና የተጀመረው ህንፃ አላለቀም። ለዛም የገቢ ማሠባሰቢያ አለ። እዛ ላይ በበጎ ፍቃደኝነት እሰራለሁ። ድርጅቱን ለማገዝ ሰዎች ጋር ተደራሽ እንዲሆን፤ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት እዛም ላይ የበጎ አድራጎት ስራ እሰራለሁ።»
ወደፊት በተሰማራችበት የኪነ ጥበብ ስራ በርትታ መስራት ትሻለች። «ትወና እና የመድረክ ዝግጅት ላይ ነው የማደላው። በትወናው በደንብ ጠንክሬ መስራት እፈልጋለሁ። ህልሜ የተለያዩ ፊልሞችን ፕሮዲውስ ማድረግ ነው። እንደገና ደግሞ ራሴንም በብቁ ሁኔታ ማውጣት እፈልጋለሁ። እሱ ላይ ነው አተኩሬ የምሰራው።»
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ