1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“አቴቴ አያና ሐዎታ” - በገዳ ስርዓት ለሴቶች የሚሰጥ ያልተገደበ መብት

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 9 2017

ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበት እና ከሁለት ዓመታት በላይ የምርምር ጊዜን የወሰደው “አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀ፡፡ ፊልሙ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው አቴቴ የኦሮሞ ህዝብ ባህሉን፣ ትውፊቱንና ወጉን በአፈታሪክ እና በጽሁፍ እንዲሁም በዜማ፣ በስነቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገሩ አንዱ ማሳያመም ተደርጎ ተወስዷል፡፡

“አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀ
“አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀምስል Seyoum Getu/DW

“አቴቴ አያና ሐዎታ” - በገዳ ስርዓት ለሴቶች የሚሰጥ ያልተገደበ መብት

This browser does not support the audio element.

“አቴቴ አያና ሐዎታ” - በገዳ ስርዓት ለሴቶች የሚሰጥ ያልተገደበ መብት

ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበት እና ከሁለት ዓመታት በላይ የምርምር ጊዜን የወሰደው “አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተመርቋል፡፡ በኑቢያ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበ ዘጋቢ ፊልሙ በወጣት ሮብሰን ዋቤ ፕሮዲዩሰርነትና ዳይሬክተርነት የቀረበ ነው።

ዘጋቢ ፊልሙ በገዳ ሥርዓት እና በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ልዩ ሚና ወጎች፣ ፍልስፍናዎች እና ታሪካዊ ፋይዳዎችን በጥልቀት በአቴቴ ስርዓትውስጥ የሚያሳይ ተብሎለታልም። ስለ የእናቶች የአቴቴ ስርዓት የሚያወሳው ዘጋቢ ፊሙም ታሪኩን ከማውሳት ባለፈ በገዳ ስርዓት ውስጥ ሴቶች እና እናቶች ያላቸውን ልዩ ሲፍራ አጉልቶ የሚያሳይም ነው ተብሏል።

ይህ ታሪካዊው የኦሮሞ ህዝብ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው አቴቴ የኦሮሞ ህዝብም ባህሉን፣ ትውፊቱንና ወጉን በአፈታሪክ እና በጽሁፍ እንዲሁም በዜማ፣ በስነቃል እና በሌሎች የጀግንነት መገለጫ ስርአቶች በሙሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገሩ አንዱ ማሳያመም ተደርጎ ተወስዷል፡፡

የዘጋቢ ፊልሙ ዓላማ

ይህን በጽሁፍና በአፈታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውን ባህልና እሴት  አግባብ ባለው መልኩ ለመጪው ትውልድ የማስተማርና ማስተላለፍ ስራ መስራት ያስፈልጋል የሚለው የዘጋቢ ፊልሙ አዘጋጅ ወጣት ሮብሰን ዋቤ ዘጋቢ ፊልሙን የመስራት ሃሳብ ሲያመጣ ዓላማው ምን እንደሆነም አስረድቷል፡፡ “ትልቁ ዓላማዬ የህዝባችንን ታሪክ፣ ትውፊት እና ወግ ባህሉን ከሚያውቁት ተላላቆቻችን በመቅዳት በዘመናዊ ሙዚየም ማኖር ነው፡፡ እንደ ምታወቀው እንደ አብዛኛው የአፍሪካ ማህበረሰብ ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ እኛ የምንኮራበትን የገዳ ስርዓቱን ጨምሮ ባህልና ትውፊቱን እዚህ የደረሰው በአፈታሪክና በሌሎችም መንገዶች በቀደምቶቻችን ጥንካሬ ነው፡፡ ይህን ዶክመንተሪ የሰራሁት ከዚሁ ዓላማ ጋር በማያያዝ ነው፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም የህዝባችን ባህልና ወግ ለማጥናት ፍላጎት ላላቸው መነሳሳትና ፍንጭ ይሰጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ገና ባህል ማንነታቸውን ላልተረዱ ታዳጊዎችም በራሳቸው በባህላቸው እንዲኮሩ ይረዳል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ከዚያም ባሻገር ዘጋቢ ፊልሙ የገዳ ስርዓት ለሰው ልጅ በሙሉ ያለውን የእኩልነት አመለካከት በጥንካሬው ለዓለም የማስተዋወቅ ውጥን በመያዝ ነበር ወደ ስራው የገባሁት፡፡ ሁለት ዓመታትን በሙሉ የፈጀው ይህ ዘጋቢ ፊልም ስሰራ አጠገቤ ሆነው ላበረታቱኝ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ከመነሻውም ከየት መጣህ ማነህ ሳትሉኝ ዓላማዬን ተረድታችሁ በቅንነት ከረዳችሁኝ ከናንተ በመወለዴም ፈጣሪን ከማመስገን ውጪ ምን እላለሁ” ብሏል፡፡

“አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀምስል Seyoum Getu/DW

ሃሊማ አብዱልሸኩር ስለአቴቴ የእናቶች በዓል ስለሚያትተው በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ በዋና ገጸባህሪ ተሳትፋ ተውናለች፡፡ ስለአቴቴ ባህልና የዘጋቢውን ፊልም ዓላማም ስታስረዳ፤ “አቴቴ በገዳ ስርዓት ስር እናቶች፤ ሴቶች ከለላና የመብት ጥበቃ የሚያገኙበት ህግ ነው” የምትለው ሃሊማ እሷ የወለደች እናትን ገጸባህሪ ተላብሳ በተወነችበት በዚህ ዘጋቢ ፊልም ይህቺን እናት ከየትኛውም ትቃት እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ለማሳየት መጣራቸውን አስረድተታለች፡፡ በዚህም ባህሉ “ብዙዎች እንደሚሉ የባዕድ አምልኮ ሳይሆን ሰብዓዊነትን ብቻ የያዘና የሰው ልጅና ተፈጥሮን የሚጠብቅ ባህል እንደሆነ ነው ለማስረዳት የፈለግነው” ትላለች፡፡ በዚህም ከጊዜ ወደጊዜ ወደ ኋላ የቀረውን ባህል በምን አይነት መልኩ ለትውልድ እናስተላልፍ የሚለው ሃሳብ ታሳቢ መደረጉንም አመልክታለች፡፡

የአቴቴ እና ሲንቄ ምንነት

መርየም ጳውሎስ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪ ናቸው፡፡ በአርሲ ኦሮሞ ዘንድ እስካሁን ባህሉ ህይወት ዘርቶ ባለበት የአቴቴ ባህል የሴት ልጅ መብት መጎናጸፊያ እሴት ይሉታል፡፡ “አቴቴ በሴት ልጅ ስተመሰል ሲንቄ ደግሞ ለሴት ልጅ ክብር፣ መብትና ግዴታ ናት” የሚሉት የባህል ተመራማሪዋ በአቴቴ ስርኣት አንዲት ወልዳ በመጫትነት ለች ሴት እስከ ስድስት ወሯ ምንም ብታጠፋ በባሏ ምንም አይነት አካላዊ ጥቃት እንዳይደርስባት ይከላከላል፡፡ ይህ የአቴቴ ባህል አሁንም ግን ለስድስት ወር መጫት መብት ብቻ የቆመ አይደለም፡፡ ከዚያም በኋላ ብሆን እንደ መጫት ሴት ልዩ ጥንቃቄ ባይደረግም ባል ምስትን ብጎዳ፣ ከመጠን በላይ አካላዊ ድብደባም ቢያደርስባት ሲንቄ መፋለሚያዋ ነው፤ መብቷን የምታስጠብቅበት ወግና እሴት፡፡ የስርኣቱ አተገባበርም፤ ተጎጂ እናት በባሏ ስትበደል “እልል እልል እልል” በማለት ሌሎች አቻዎቿን በእልልታ ትጣራለች የሚሉት ተመራማሪዋ፤ የድረሱልኝ ጥሪውን የሚሰሙ የጎረቤት እናቶች በሙሉ ይደርሱላታል፡፡ ከዚያም የደረሰባትን “ተጎድቻለሁ፤ በአራስነተ ተገቢው እንክብካቤ ልደረግልኝ ስገባ ተመትቻለሁ” ብላ ስታስረዳ ስሞታዋንም ስታቀርብ ጉዳቱ ጎልቶ የሚታይ ከሆነ ሌሎች ሴቶች ይረዱአትና በወግ በህጉ መሰረት ጥፋት ካጠፋው ባሏ የሚወደውን ከብት ተቀብለው አባገዳዎች ተጠርተው ተወቅሶ ከብቱ ታርዶ ይበላል እሷም ትካሳለች፡፡

“አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀምስል Seyoum Getu/DW

የአርሲ ሲኮ መንዶ ሃዳ ሲንቄ ሸምሲያ ጉተማም አስተያየታቸውን አከሉ፤ “ወንድየው ባሏ ሴት ወልዳ እስከ ስድስት ወር ውስጥ እንኳን ልመታት በክፉ ኤን አያያትም፡፡ ከስድስት  ወርም አልፎ አነስተኛ ግጭት ካልሆነ የበዛ አካል ላይ ጉዳት ካደረሰ ቅጣት ይጠብቀዋል” ብለዋል፡፡

ሌላው አቴቴና ሲንቄ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደለም፡፡ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪ መርየም ጳውሎስ ፤“አቴቴ በሰው ትመሰላለች፡፡ ሴት ልጅ አቴቴ ትባላለች፡፡ ሲንቄ ደግሞ የአቴቴ (የሴት ልጅ) ክብሯ ነው፡፡ ይህም ሲንቄ ስባል ቀችንና ረጅም እንጨት ሆኖ የሴት ልጅ ክብር ምልክት ናት” ተብሏልም፡፡

ታዲያ ይህንን ስንቄ ይዛ ለእርቅ የወጣች እናትን ወይም የእናቶችን ስብስብ ረግጦ ማለፍ የሚቻለው አካል አይኖርም፡፡ ካለም የሚደርስበት ውግዝትና ማግለል እስከወዲያኛው ከማህበረሰቡ የሚያገለው ስለሚሆን ጦርነትም ብሆን በሃዳ ሲንቄዎች ወይም በአቴቴ ይቆማል፡፡ “አቴቴ (ሃዳሲንቄ) ሲንቄዋን ዛ በሁለት ተፋላሚዎች መካከል ገብታ ጦሩ እንዲቆም እልልልልል ካለች ሁለቱም ወገን ጦራቸውን ወዲያው ማሳረፍ እና መታረቅ ኖርባቸዋል፡፡ አለዚ ያንን ሳይቀበል ቀርቶ የእርቁን ጥያቄ የረገጠና በዚህም ከፍተኛ ትፋት ያጠፋ በሸነቻ ስርዓት ተጠርቶ በአባገዳዎች ኮንቶማ በተባለ ስርዓት እንደየጥፋቱ ከምክር እስከ ግርፋትና እስር የሚደርስ አደገና ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል፡፡ እናም በዚህ የአቴቴ የእርቅና የሰላም ጥያቄ ላይ መራመድ የሚቻለው የለም” ተብሏልም፡፡

“አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀምስል Seyoum Getu/DW

ቀነኒ ደምሴ ደግሞ በምእራብ አርሲ ዞን ከሻላ ወረዳ ነው በአቴቴ ዘጋቢ ፊልም የምረቃ ስነስርኣት ላይ ለመታደም ትናንት ረቡዕ መስከረም 08 ቀን 2017 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የመጡት፡፡ አቴቴ የሰላም እናት ናት ስሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን፡፡ “አቴቴ ማለት የሰላም እርቅ የጦርነት እለት ደራሽ የሰላም ማምጫ እናት ማለት ነው፡፡ የጨከነ የመረረ የችግር ቀን እንኳ የሚራራላት ነው፡፡ ሰው  ስጣላ ሃዳ ሲንቄ ከአባገዳ ጋር ወጥታ ፈጣሪን ተማጽና በሲንቄዋ ሰላምን ስለምታወርድ አቴቴ ማለት የሰላም እናት ማለት ነው” ብለዋል፡፡

ከአርሲ ዞን ሙኔሳ ወረዳ የመጡት ሃዳ ሲንቄ ኑሬ ዋቆም ስለ አቴቴ ይህን ብለዋል፡፡ “አቴቴ በብዙ ይከፈላል፡፡ የጦርነት ጊዜ፣ የመልካ፣ የሙዳ አቴቴ ብለን ልናነሳቸው እንችላለን፡፡ አቴቴ ሁኔታና መልክ አላት፡፡ ሴት ሁሉ የሚሆነው የሚያደርገው አይደለም፡፡ ስለሲንቄ ክብር የምታውቅ ወግ ማዕረጉን የምታውቅ መሆን አለባት” ብለዋል፡፡

የአርሲ ሲኮ መንዶ ሃዳ ሲንቄ ሸምሲያ ጉተማም አስተያየታቸውን አከሉ፤ “አቴቴ ፊት የሚቆም ጦር የለም” የሚሉት ሃዳ ሲንቄዋ እናቶች ስንቄ ይዘው ከፊት ለፊት ቆሞ የሚንገራገር አይኖርምም ብለዋል፡፡

ከምእራብ አርሲ ዞን የመጡ አባገዳ ቃበቶ ቱፋም ስለ አቴቴ ክብርና በስርኣቱ ያለውን ወግ ሲያብራሩ፤  “የአቴቴ ባህል እርቅ ነው፡፡ እልልታውም የእርቅ ምልክት፡ ጦርነትን ጨምሮ የተለያዩ አደጋዎችን ቀንስልን ለማለት ትልቅ ወግ ያለው ባህል  ነው፡፡ አቴቴ የገዳ ስርዓቱ አካል እንደመሆኑ ገዳው ሰላም ካወጀ አቴቴም ወጥታ ህንኑን ሰላም ታስተጋባለች፡፡ የአቴቴን ትዕዛዝ ረግጦ ያለፈ ሰው በገዳ ስርዓቱ ተጠርቶ ህግ ይቆረጥና እስከ ማግለል የሚደርስ ቅጣት ልተላለፍበት ችላል” ብለዋል፡፡

አቴቴ ለተፈጥሮ ልማት

አቴቴ ከሰው እርቅ በተጨማሪ ፈጣሪንም ከሰው ልጅ ጋር ለማስታረቅ አደባባይ ትወጣለች፡፡ በተፈጥሮ አደጋ ድርቅ ወይም የዝናብ ብዛት ሰው ልጅን ስጎዳ አቴቴ ወጥታ ፈጣሪን ለእርቅ ትለምናለች፡፡ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪ መርየም ጳውሎስ “ዝናብ ካየለም ድርቅ ከበረታም ፈጣሪ ሆይ መጥንልን ብላ ትለምናለች፡፡ ድርቅም ሲሆን ከሲንቄዋ ጋር እንዲሁ ትለምናለች” ብለዋል፡፡

“አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተመረቀምስል Seyoum Getu/DW

አቴቴ የልጃገረዶች መብት ማስጠበቂያ

በአቴቴ ስርዓት ሴት ልጃገረዶች የሚጎናጸፉት ሌላው መብት አላቸው፡፡ አሴና ወይም አዳባና የተባለ ሴት ልጅ የትዳር አጋሯን የምትመርጥበት መብት፡፡ “ሴት ልጅ የወደደችውን እንድታገባ ይረዳል አቴቴ፡፡ ሲንቄ ይዛ የወደደችው ወንድ ቤተሰቦች ጋር ገብታ ስንቄ ብታስቀምጥ ወደደችው ተብሎ በለጠ የምትከበርበት ባህል ነው ያለው” ተብሏልም፡፡

ሰሞነኛው “አቴቴ አያና ሀዋኒ” በሚል የተሰራ በገዳ ስርዓት ውስጥ የእናቶች መብትና በባህሉ ውስጥ ያላቸው ስልጣን ላይ ያጠነጠነው ዘጋቢ ፊልምም ይህንኑን የኦሮሞ ህዝብ የትሁፊትና የታሪክ ወግ ባማረ መልኩ ለመግለጽና ለማስተማር የተዘጋጀ ስለመሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ ይህም ፍልስፍና የሰው ልጅ ከፈጣሪ በታች ያለውን ተፈጥሮ የማስተዳደር ጥብብ ተደርጎ ልወሰድ እንደምችል ተመልክቷል፡፡

ሥዩም ጌቱ / አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW