1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ወደ ሀገሪ እንዳልገባ ተከለከልኩ» አቶ ልደቱ አያሌው

ረቡዕ፣ የካቲት 5 2017

አቶ ልደቱ በአሜሪካን የኢትዮዽያ ኤምባሲን አነጋግረው "የተለየ ፈቃድ" ካልተሰጣቸው በስተቀር ወደ ኢትዮዽያ መጓዝ እንደማይችሉ በአትላንታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።"ከባድ"ያሉት ይህ ውሳኔ "የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ነው" ብለው እንደሚወስዱትና ሌሎች ባለሥልጣናት ይህንን ደፍረው ሊያደርጉ አይችሉምም ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien Addis Abeba | Lidetu Ayalew, äthiopischer Politiker
ምስል፦ privat

አቶ ልደቱ አያሌው ወደ ሀገሪ እንዳልገባ ተከለከልኩ አሉ

This browser does not support the audio element.

ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ያደረጉት ጥረት እና ያገኙት ምላሽ

ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው "የአገልግሎት ጊዜው ያላለፈ የኢትዮዽያ የይለፍ ሰነድ - ፓስፖርትና የተረጋገጠ የጉዞ ትኬት" ይዘው ዩናይትድ ስቴትስ አትላንታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቢገኙም የኢትዮዽያ አየር መንገድ እዚያ የሚገኘውን የኢትዮዽያ ኤምባሲን አነጋግረው "የተለየ ፈቃድ" ካልተሰጣቸው በስተቀር ወደ ኢትዮዽያ መጓዝ እንደማይችሉ በአትላንታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል። አቶ ልደቱ አያሌው እንደዚህ አይነቱ "ከባድ" ያሉት ውሳኔ [የኢትዮጵያ] "የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ነው" ብለው እንደሚወስዱት እና ሌሎች ባለሥልጣናት ይህንን ደፍረው ሊያደርጉ እንደማይችሉ ለዶቼ ቬለ አብራርተዋል።

ከኢትዮጵያም ሆነ ከውጪ መንግሥታት “ምንም የተሰጠኝ ዋስትና የለም” አቶ ልደቱ አያሌው

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ለማግኘት ስልክ መደወላቸውን ያስታወቁት አቶ ልደቱ በኤምባሲው ድረ- ገጽ ላይ የተቀመጡ ስልክ ቁጥሮች ሲደወልባቸው እንደማይነሱ ተናግረዋል። ሆኖም እስከ የበረራው ዕለት ድረስ የአየር መንገዱ መልዕክቶች በኢሜይል ይደርሷቸው እንደነበር ተናግረዋል።«የሚመጣዉን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ» ልደቱ አያሌዉ

ይህ እንደሚገጥማቸው አልገመቱም 

ሁልጊዜ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያስፈልጋል በሚለው አቋማቸው የሚታወቁት አቶ ልደቱ አያሌው አዲስ አበባ ኤርፖርት ስደርስ፣ በሽብርተኝነት እንደምጠረጠር መግለጫ ወጥቶ ስለነበር "ልታሠር እችላለሁ የሚል ሥጋት ነው የነበረኝ" እንጂ "በምንም ሁኔታ ወደ ሀገሬ እንዳልገባ ከአሜሪካ በረራ እንዳላደርግ እከለከላለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም" ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት አጋርተዋል።
እንደ ግለሰብ "ከልጅነቴ ጀምሮ ውጭ ሀገር ተሰዶ የመኖር ፍላጎት ያለኝ ሰው አይደለሁም" የሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው፣ እንደ ንቁ የፖለቲካ ተዋናይ ደግሞ "ትግልን መምራት ካለብን ውጭ ሀገር ሆነን መምራት አለብን ብየ አላምንም" ሲሉ ወደ ሀገር ቤት የመመለሱ ጉዳይ በእሳቸው ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ባይሆንም በሌሎች አየር መንገዶች ለመጓዝ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረውናል። 

እስካሁን ከመንግሥትም፣ ከአየር መንገዱም የተሰጠ ምላሽ የለም

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ማብራሪያ ጠይቀን ነበር። የአየር መንገዱ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ሐና አጥናፉ ስለ ጉዳዩ የአየር መንገዱን ኃላፊዎች ጠይቀው ምላሽ እንደሚሰጡን ከገለፁልን በኋላ ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም። ብሔራዊ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል ቡድን ውስጥ በሕቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል እንደሚፈልጋቸው ገልጾ ነበር።የአቶ ልደቱ አያሌው አዲሱ ሰነድና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW