1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ አንዳርጋቸው በመጪዎቹ ሁለት ቀናት ይፈታሉ ተባለ

ሰኞ፣ ግንቦት 20 2010

የግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ መሥራቹ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በመጪዎቹ ሁለት ቀናት እንደሚፈቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል። አድናቂዎቻቸው የኢትዮጵያ መንግሥት "በልዩ ሁኔታ" ይቅርታ ያደረገላቸው አቶ አንዳርጋቸው ተፈተዋል በሚል ደስታቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል።

Großbritannien - Protest gegen Haft von  Andargachew Tsige
ምስል Imago/ZUMA Press

Waiting for the release of Andargachew Tsige - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

አዲስ አበባ ላይ ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት ሳር ተጎዝጉዟል፤  ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሏል፤ጥሩምባ ይሰማል፤ ጭፈራም አለ። ቤቱን ያሞቀው ላለፉት አራት አመታት ገደማ በእስር ላይ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሳይፈቱ አልቀረም የሚለው ዜና ነው። ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ደጃፍ አቅንቶ የአቶ አንዳርጋቸውን የመፈታት ዜና ሲጠባበቅ ያረፈደው የፖለቲካ አራማጁ ስንታየሁ ቸኮል "ቤቱ ገና አልገባም። መፈታቱን በእርግጠኝነት ወጥቷል ተብሏል" ሲል ይናገራል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነው እንደሚሉት ግን የአቶ አንዳርጋቸው መፈቻ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤት አስተዳደር አልደረሰም። የአቶ አንዳርጋቸው መፈታት "ያለቀ የተወሰነ ጉዳይ ነው" ያሉት አቶ ተስፋዬ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት "ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይተላለፍ ይሆናል" ብለዋል።

የግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ መሥራቹ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሊፈቱ ነው የሚል ወሬ ከተሰማ ሰንበት ቢልም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ "በልዩ ሁኔታ" ይቅርታ እንደተደረገላቸው ያረጋገጠው ግን ቅዳሜ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር።

ከዚያን ዕለት ጀምሮ አባታቸው አቶ ፅጌ ኃይለማርያምን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው እና አድናቂዎቻቸው የመፈታታቸውን ዜና በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ታናሽ እህታቸው ወይዘሮ አይንዬ ፅጌ "ትናንትናም ሔደን ነበር፤ ዛሬ ጠዋትም እዚያ [ቃሊቲ ማረሚያ ቤት] ነበርን። ምንም ፍንጭ አላገኘንም። እንኳን አቶ አንዳርጋቸውን፤ ሁነኛ የተባለ ሰው እንኳ አነጋግረንው በቁርጠኝነት በዚህ ሰዓት በዚህ ቀን ነው የሚወጣው። አትቸገሩ፤ አትመላለሱ ብሎ የሚለን ሰውም የለም"ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ጋዜጠኞች እና መፈታታቸውን የጠበቁ አድናቂዎቻቸው በዛሬው ዕለት አቶ አንዳርጋቸው ይገኙበታል በተባለው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ደጃፍ አቅንተው ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ መታዘባቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች የዲፕሎማቲክ ሰሌዳ የለጠፉ ተሽከርካሪዎች ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ገብተው ለረዥም ሰዓታት መቆየታቸው ለመፈታታቸው ምልክት ሆኖላቸው ነበር። ሲገቡም ሆነ ሲወጡ በተሽከርካሪዎቹ ውስጥ ማን እንደተቀመጠ የአይን እማኞች በእርግጠኝነት መናገር አልቻሉም። ነገር ግን ዲፕሎማቶች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ በአካባቢው የነበሩ ይጠረጥራሉ። እንደ የአይን እማኞች አባባል ተሽከርካሪዎቹ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ በአካባቢው የመቆም አዝማሚያ ያላሳዩ ሲሆን መስኮቶቻቸው በጥቁር መስታዎት የተለበጡ ናቸው።  አቶ አንዳርጋቸው አዲስ አበባ ወደሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ ሳይወሰዱ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ ያደረባቸውም አልጠፉም።  ወይዘሮ አይንዬ ግን ከኤምባሲው ጋር "ግንኙነት አለን። እነሱም እንደኛው ምንም አይነት መረጃ የላቸውም" ብለዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ወደ ኤርትራ በመጓዝ ላይ ሳሉ በየመን የሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ውለው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው የተሰጡት ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ነበር። የቀድሞው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ ቢፈቱ እንኳ በዜግነት ብሪታንያዊ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ለመቆየት የመቻላቸው ነገር አጠያያቂ ነው። ባለቤታቸው ወይዘሮ የሚ ኃይለማርያም ዘ-ጋርዲያን ለተባለው ጋዜጣ አቶ አንዳርጋቸው "በዚያ ቢወለድም፤ ሕጉ የሌላ አገር ዜግነት ስትወስድ ኢትዮጵያዊ ዜግነትህን እንደምታጣ ይደነግጋል። አንዳርጋቸው የብሪታኒያ ዜጋ ነው። ስለዚህ በዚያ ለመቆየት ህጋዊ ፈቃድ የለውም" ሲሉ ተናግረው ነበር። ወይዘሮ አይንዬ ግን ወንድማቸው አቶ አንዳርጋቸው "መጀመሪያ ከቤተሰብ ጋር ተገናኝቶ በገዛ ፈቃዱ ወደ እንግሊዝ አገር ይመለስ ይሆናል ብዬ ነው የማስበው" ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW