አቶ አደም ፋራህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ
ሰኞ፣ ኅዳር 7 2019
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አዲስ የቦርድ ሰብሳቢ ሾመ
አቶ አደም ፋራህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ።
የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ኃላፊነቱን የተረከቡት ከሰኔ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙን ሲመሩ የቆዩትን እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ የሆኑትን ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን በመተካት ነው።
ሹመቱ የግዙፉ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከፍተኛ አመራርን ከከፍተኛ የጦር መኮንን ወደ ከፍተኛ የፓርቲ ኃላፊ መሪነት ያዞረ ነው።
ከሰኔ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመት ከአምስት ወራት በኢትዮጵያአየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ሲመራ የቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሥራ አመራር ቦርድ አዲስ ሰብሳቢ ተሾመለት። ይህንን ኃላፊነት የተረከቡት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አደም ፋራህ ናቸው።
አቶ አደም የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ ሆነው የሚሠሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው። ከዚህ በፊት ከሰኔ 2012 ዓ.ም እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ፣ ከዚያ አስቀድሞ ደግሞ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነበሩ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አመራር ቦርድ በኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ሲመራ የቆየው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ አላቸው የሚባሉት አቶ ግርማ ዋቄን በመተካት ነበር።
ዶቼ ቬለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንኑ ጉዳይ እንዲያረጋግጥለት ዛሬ ማለዳ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ጥያቄውንም በኢሜይል እንድናቀርብም ተነግሮን ምላሽ ስንጠብቅ ቆይተናል። ይሁንና ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ከቀኑ 11 ሰዓት ድረስ ምላሹ አልደረሰንም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በሀገር ውስጥ ለሚታተመው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ የቦርድ ሊቀመንበር ለውጥ መደረጉን ስለማረጋገጣቸው ገልፆ ጋዜጣው ዘግቧል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የበረራ ዘርፍ ባለሙያ የአመራር ለውጥስለመደረጉ ተጨባጭ መረጃ እንዳላቸው ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ይሁንና ጉዳዩ እስካሁን በግልጽ ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን በ2025/26 የግሪጎሪያን የበጀት ዓመት ወደ 9.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቱ በወቅቱ ተገልጿል።
ይህ ግዙፍ ተቋም የዓለም አቀፍ በረራ መዳረሻዎችን የማስፋት፣ አዳዲስ አውሮፕላኖችን የመግዛትና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ግንባታን የማፋጠን እንዲሁም ትርፋማነቱንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የማስቀጠል ቁልፍ ተግባራት ያሉበት ነው።
አዲሱ የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በቀጣይ ምን ላይ እንደሚያተኩሩ ግን እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር የለም።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ሰለሞን