1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ የሚቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሩ ተመረጡ።

ቅዳሜ፣ መጋቢት 9 2015

ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ትላንት ባወጣው መግለጫ "ቅቡልነት እና ሕጋዊነት ያጣ ግዚያዊ አስተዳደር ፍትህና ዴሞክራሲ ሊያረጋግጥ አይችልም" ብሎታል።

Äthiopien Getachew Reda in Addis Abeba
ምስል፦ DW/Y. Geberegeziabeher

አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ የሚቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሩ በህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ተመረጡ።

This browser does not support the audio element.

አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ የሚቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሩ በህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ተመረጡ። የአቶ ጌታቸው ሹመት የፌደራሉ መንግስቱ ይሁንታ ይጠብቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቃዋሚው ፓርቲ ዓረና ትግራይ ለሉአለዊነት እና ዴሞክራሲ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የማቋቋሙ ሂደት ላይ የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት ወቅሷል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በትግራይ ይቋቋማል የተባለው ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሩ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ተሰብስቦ አቶ ጌታቸው ረዳን መምረጡ ያረጋገጡልን ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን፣ ይኽ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ውሳኔ በቅርቡ ለፌዴራሉ መንግስት ቀርቦ ሊፀድቅ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል። ሌላው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ዛሬ በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት "አቶ ጌታቸው ረዳ ለትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መሪነት እጩ እንዲሆኑ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ መወሰኑ" ገልፀዋል። የአቶ ጌታቸው እና ሌሎች የግዚያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ሹመት ህወሓት ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ተወያይቶ ተቀባይነት ካገኘ ወደ ስራ ይገባሉ ሲሉ ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀውልናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ከአራት በላይ ወር በላይ ቢቆጠርም ይቋቋማል የተባለው ግዚያዊ አስተዳደር እስካሁን እውን ባለመሆኑ የተለያዩ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ። በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ትላንት ባወጣው መግለጫ "ቅቡልነት እና ሕጋዊነት ያጣ ግዚያዊ አስተዳደር ፍትህና ዴሞክራሲ ሊያረጋግጥ አይችልም" ብሎታል። ዓረና በመግለጫው በትግራይ ጦርነት እንዲቀሰቀስ፣ ሚልዮኖች እንዲፈናቀሉ፣ በርካቶች እንዲሞቱ እና እንዲጎዱ ምክንያት የሆኑ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ ሌሎችን በማግለል ብቻቸው በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ለማቋቋማ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ቅቡልነት የለውም ሲል አክሏል።

ምስል፦ DW/G.Tedla

ያነጋገርናቸው የዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ ሃፍታይ ገብረሩፋኤል "ሁለቱ የችግሩ ምንጮች የሆኑ ሀይሎች መፍትሔ ሊፈጥሩ አይችሉም" ሲሉ የገለፁ ሲሆን፣ እስካሁን የተያዘው አካሄድ ግን ካለፈው ትምህርት የተወሰደበት አይመስልም ሲሉ አክለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ሃፍታይ በትግራይ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታት ሁሉን ያካተተ የሽግግር ስርዓት መዘርጋት ይጠበቃል ብለዋል።

በግዚያዊ አስተዳደሩ ማቋቋም ሂደት ዙርያ ከህወሓት ወገን ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም። ከዓረና ውጭ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ባይቶናና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከግዚያዊ አስተዳደር የማቋቋም ሂደቱ ማግለላቸው ይታወሳል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW