አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ ላይ የሰጡት መግለጫ
ሐሙስ፣ መጋቢት 4 2017
"የትግራይ ሕዝብ መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል" ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። አቶ ጌታቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቆ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ለፌዴራል መንግሥት በምክር ቤት ወይም በካቢኔ ደረጃ ያቀረብነው ይፋዊ ጥያቄ የለም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"ክልሉን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚደረግ ጥረት" በየቀኑ እየሰፋ ስለመሆኑ በመግለጫቸው የተናገሩት አቶ ጌታቸው "የፌዴራል መንግሥት ይህንን የማስቆም ግዴታ ግን አለበት" ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ "የተወሰኑ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች - ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ" ያሏቸው የህወሓት ኃይላት "ከኤርትራ ጋር ግንኙነት አላቸው" ሲሉም ተናግረዋል።
ሰሎሞን ሙጬ ዝርዝሩን ያቀርብልናል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥቱ ያቋቋመው አደረጃጀት መሆኑን በመጥቀስ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ ጣልቃ እንዲገባ ያቀረብነው ጥያቄ የለም ብለዋል። ሆኖም የፌዴራሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ድጋፍ ማድረግ የለበትም ማለት አይደለም ብለዋል።
"ጣልቃ እንዲገባ [የፌዴራሉ መንግሥት] ያቀረብነው ፎርማል ጥያቄ የለም"
"የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍላጎት ሊመጣ የሚችልን ጦርነት ማስቀረት ነው" ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ ሸሽተው መጥተው እንደሆን ምላሽ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ የመጣሁት "ግጭት እንዳይከሰት በጉዳዩ ላይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመነጋገር ነው" ብለዋል።
"የወረዳ፣ የቀበሌ፣ አሁን ደግሞ የከተሞችን ማህተም የሚነጥቅ እና ቢሮ የሚሰብር "ጉባኤ ያደረገ የሕወሓት አንጃ" እና ትግራይን ለበለጠ የእርስ በርስ ግጭት የሚዳርግ ኃይል" በክልሉ መኖሩን ጠቅሰው፣ ይህንን የሚያደርጉት "ጥቂት ሰዎች ናቸው" ብለዋል።
"እኔ አሁን ተፈጥራ የነበረችው ሰላም መረበሽ ስለጀመረች፣ ይቺው እንድትጠበቅ፤ ወደ ሌላ ጦርነት እንዳንገባ እንረባረብ ፌዴራል መንግሥትም ያግዘን ነው እያልኩ ያለኹት"
ትግራይ ክልል ውስጥ "መከፋፈል እና ቀውስ" መኖሩን የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በጦርነቱ ወቅት "በመቶ ሺህ ሰዎች መቀሰፋቸውን፣ ሕዝቡም ላለፉት አራት ዓመታት ስቃይ ውስጥ መሆኑን" ገልፀዋል። የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት በአግባቡ እንዳይፈፀም የሚፈልግ ያሉት "የትግራይ የፖለቲካ ኃይል" ለዚህ ተጠያቂ ነው ብለዋል።
"ፕሪቶሪያ [የግጭት ማቆም ስምምነቱ] በተሟላ መልኩ ከተፈፀመ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አያስፈልግም። በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ነው ትግራይ የሚያስፈልጋት"
የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ ምን አሉ?
የኤርትራን ጉዳይ እና በክልሉ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ትግራይ ክልል ውስጥ የሚነሳን ግጭት ብዙ ኃይል ይገባበታል" ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ "በዚህ ውስጥ ኤርትራ አንዱ እንደሆነ "አውቃለሁ" ብለዋል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግጭት የጀመረው "የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈፀመ በኋላ ነው" የሚል መረጃም አክለዋል።
"እኔ በማውቀው ደረጃ እንደ መንግሥት ኃላፊ የተወሰኑ ወታደራዊ አመራሮች ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ፤ የተወሰኑ የፖለቲካ አመራሮች ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ አመራሮች ግንኙነት አላቸው፤ የለኝም የሚል ሰው ያስተባብል።" ብለዋል።
"ክልሉን [ትግራይን] የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚደረግ ጥረት" በየቀኑ እየሰፋ መሆኑን በመግለጫቸው የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ወጣት ጦርነት ውስጥ ሊሳተፍ የሚችለው "ትግራይ ላይ በሌላ አካል ጦርነት ከታወጀ ብቻ ነው" ብለዋል። ከዚህ ውጭ ግን ጦርነት ውስጥ የሚገባበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይገባም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር አሁንም ጥሪ አቅርበዋል። በክልሉ "ሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር" በስፋት ስለመኖሩም አመልክተዋል። ይህም በጥቂት "የሕወሓት አንጃ" ቡድኖች እንደሚፈፀም እና ያም የሚሆነው "ተጠያቂነት ይኖራል" ብለው ስለሚፈሩ ነው ብለዋል።
በዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራውየሕወሓት ቡድንያወጣው መግለጫ
በሌላ በኩል በዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ቡድን "ሰሠራዊታችንን በመበተን የትግራይ ሕዝብን ለከፋ አደጋ ማጋለጥ አይቻልም" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ሕወሓት "ድርጅታችን፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ 'የተወሰኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አመራሮች ከተልዕኳቸው ወጥተው የውጪ ኃይሎች መሣሪያ በመሆን የትግራይ ሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው እየሰጡ ነው፣ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን በማፍረስ ማቆሚያ የሌለው አደገኛ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው' የሚል ተጨባጭ ያለው ግምገማና ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ይታወቃል" ብሏል።
ይሄው መግለጫ አክሎም " የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችን ለማገድና ለማባረር" የተደረገው ውሳኔ ተፈፃሚነት የሌለው" መሆኑ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል ብሏል። "የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሙሉነትና በፍጥነት በመተግበር ወደ ዘላቂ ሰላምና መልሶ መቋቋም በሚወስድ መንገድ አወንታዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ" ሲሉም ለፌዴራል መንግሥት እና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥሪ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኤምባሲዎች ጥሪ
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ በኢትዮጵያን ጨምሮ የ 24 ሀገራት ኤምባሲዎች በሰሜን ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ለውጦችን እና እየተባባሰ ያለውን ውጥረት እየተከታተሉ መሆኑን ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠቅሰዋል።
ለፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ ድጋፋችንን እንደምንሰጥ ደግመን እናሳውቃለን ያሉት ኤምባሲዎቹ ወደ ግጭት መመለስ እንደማይገባ እና ሁሉም ወገኖች አስቸኳይ ውይይት በማድረግ ስምምነቱን እንዲጠብቁ አናሳስባለን ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ