1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪው የሾልዝና የፑቱን የስልክ ንግግር ፤ ተቃውሞውና እንደምታው

ማክሰኞ፣ ኅዳር 10 2017

ሾልዝ ከፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ ለዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አስቀድመው አሳውቀዋቸዋል። ሆኖም የስልክ ንግግሩን ፈጥነው ከተቹት መካከል ዜሌንስኪ ግንባር ቀደሙ ነበሩ። በስልኩ ጥሪ «ችግር የሚያስከትል ጉዳይ ቀሰቀሱ» ሲሉ ሾልዝን የተቹት ዜሌንስኪ የሩስያውን መሪ ለማግለል የሚካሄደውን ጥረትም በማዳከም ወቅሰዋቸዋል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና የሩስያ ፕሬዝዳንት ኦላፍ ሾልዝ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና የሩስያ ፕሬዝዳንት ኦላፍ ሾልዝምስል Kay Nietfeld/Sputnik/AP/dpa/picture alliance

አነጋጋሪው የሾልዝና የፑቱን የስልክ ንግግር ፤ ተቃውሞውና እንደምታው

This browser does not support the audio element.

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ባለፈው አርብ የሩስያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን 2 ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ማነጋገራቸው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። ሾልዝ ወቅቱን ላልጠበቀ ምርጫ በዝግጅት ላይ ባሉበትና ፣አውሮጳም ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፣የዩክሬኑን ጦርነት አስቆማለሁ ያሉበትን እቅዳቸውን ለመስማት በሚጠባበቅበት በዚህ ወቅት  ያቀረቡት የሰላም ጥሪ ማነጋገሩ ቀጥሏል። ሾልዝ በስልክ ንግግሩ ፑቲን ከዩክሬን ወታደሮቻቸውን እንዲያስወጡ እና ከክየቭ ጋርም  ለዘላቂ ሰላም መንገዱን የሚጠርግ ንግግር እንዲጀምሩም መጠየቃቸውን የጀርመን መንግሥት አስታውቋል።  ሩስያ ከዩክሬን ጋር ንግግር ለመጀመር ፈቃደኝኝነቷን እንድታሳይ የጠየቁት ሾልዝ  አስፈላጊነቱ እስከ መቼም ይሁን ዩክሬን የሩስያን ወረራ እንድትከላከል ጀርመን የማይቋረጥ ድጋፏን ትሰጣለች ሲሉም አረጋግጠዋል።

የጀርመኑ ቻንስለር ለዩክሬን ያላቸዉ ግልፅ አቋም

የሾልዝ የሰላም ጥሪ ከሀገር ውስጥ ደጋፊዎች እንዳሉት ቢታመንም ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ከሩስያ ጋር ጦርነት የምታካሂደው ክየቭ ግን ንግግሩ በመካሄዱና የሰላም ጥሪውም በመቅረቡ ደስተኛ አይደለችም።ሾልዝ ለዜሌንስኪ አሳውቀዋቸው ነበር ከፑቲን ጋር የተነጋገሩት ሆኖም የስልክ ንግግሩ ፈጥነው ከተቹት መካከል የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ይገኙበታል። በስልኩ ጥሪ «ችግር የሚያስከትል ጉዳይ ቀሰቀሱ» ሲሉ ሾልዝን የተቹት ዜሌንስኪ የሩስያውን መሪ ለማግለል የሚካሄደውን ጥረትም በማዳከም ወቅሰዋቸዋል።

ሾልዝ በቢሮአቸው ከፑቲን ጋር የስልክ ንግግር ሲያካሂዱምስል Steffen Kugler/Bundesregierung/dpa/picture alliance

በሪዮ ደጀኔሮ ብራዚል ለሁለት ቀናት ከተካሄደው ከቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ሾልዝ በሰጡት መግለጫ የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ተከላክለዋል። የስልኩን ጥሪ ማድረጋቸው ትክክል መሆኑን ይህንንም ለማድረግ መነሻ የሆናቸውን ምክንያት አስረድተው ነበር ።

« በኔ አመለካከት ከሩስያው ፕሬዝዳንት ጋር አሁን መነጋገሬ ትክልል ነበር ለማለት እፈልጋለሁ ፤አሁንም ትክክል ነው፤ ምክንያቱም ይህ ለርሳቸው ግልጽ መሆን አለበት። ሃላፊነት አለባቸው። ጦርነቱን ማቆም አለባቸው፤ወታደሮቻቸውን ከ(ዩክሬን) ማስወጣት አለባቸው። የዩክሬንን መንግሥትና መከላከያውን ከሚደግፉ ሀገራት ጋር መቆመር መቻል የለባቸውም።  ይህ ደግሞ ለርሳቸው ግልጽ መደረግ አለበት።ጀርመን ከአውሮጳ ለዩክሬን አብዛኛውን ፣ከዓለም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ድጋፍ የምትሰጥ ሀገር ናት ።ይህ ደግሞ አይለወጥም። ሆኖም ጦርነቱን ወደ ፍጻሜ ማምጣት አለብን። ለዚህም ነው አንድ ነገር መደረግ ያለበት። ለዚህም በአመራር ደረጃ የሚገኙትን ማነጋገር አለብን።ለዚህ ግልጽ ቃላት ያስፈልጋሉ። »ብለዋል ሾልዝ

ጦርነቱ ሁለቱን ተፋላሚ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እየነካ ነው ያሉት ሾልዝ፤ ጀርመናውያንም የአውሮጳ ሰላምና ጸጥታ ስጋት ላይ እንደጣላቸውም ማንሳታቸው አልቀረምየመንግሥት ቀውስ በጀርመን፤ መንስኤው መዘዞቹና መጪው ምርጫ

« ይህ ጦርነት ጀርመናውያንን ጨምሮ ሁላችንንም እየጎዳን ነው።  ሁሉም ይህ ምን ማለት ነው እያለ ማሰቡ አልቀረም። አብዛኛዎቹ የጀርመን ዜጎች በአውሮጳ የሰላም የፀጥታ ጉዳይ የተጨነቁ መሆኑን አረጋግጫለሁ።  ለዚህም ነው ሁላችንም ዩክሬንን መደገፋችን፣ ትክክለኛውን ነገር ማድረጋችን ፣ሩስያን በሚመለከትም በዚህ ዓይነቱ ጊዜ ትክክለኛዎቹን ቃላት መፈለጋችን ጠቃሚ የሚሆነው።ሆኖም በተመሳሳይ እንቅስቃሴያችን በብልሀት ሊሆን ይገባል። የእኔን አካሄድ በሚመለከት በዚሁ መንገድ ነው የምቀጥለው ።»

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እና የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶርየስ በጀርመን ፓርላማምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ሾልዝ የሰላም ጥሪው ያስፈለገበትን ምክንያት እንዲህ ቢያስረዱም ዜሌንስኪና ሌሎች የአውሮጳ ባለሥልጣናት የሾልዝን እርምጃ በመቃወም ማስጠንቀቃቸው አልቀረም።  ከሀገር ውስጥም ቀኝ ዘመሙን የጀርመን የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲን ጨምሮ ሌሎችም ፓርቲዎችም ተቃውሞአቸውን አስምተዋል። ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የዩክሬን ምክንያት ምን እንደነበረ አስረድተዋል።

ክሬምሊን በሾልዝ ጥያቄ ተካሄደ ባለው በዚሁ ንግግር ፑቲን ደግሞ የዩክሬኑን ጦርነት ማስቆምን የተመለከተ ማናቸውም ስምምነት የሩስያን የጸጥታ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባና አዲሱን የግዛት እውነታ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበትም ማለታቸውን ተናግሯል።

 የመራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሳህል አስቸጋሪ ተልዕኮ

በጎርጎሮሳዊው የካቲት 23 ቀን 2025 ዓ.ም.  ምርጫ የሚጠብቀው በሾልዝ የሚመራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ  «መንግሥት ጦርነቱን ለማስቆም በቂ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አላደረገም» ከሚሉት መፍቅሬ ሩስያ ፣ ህዝበኛ ከሚባሉት ፓርቲዎች በኩል  ግፊቱ በርትቶበታል። እናም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች ጥሪውን የሀገር ውስጥ ደጋፊዎችን ለማብዛት የተካሄደ ይሉታል። ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋም ሾልዝ በዚህ ወቅት ላይ የሰላሙን ጥሪ የማቅረባቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል ያሉትን ተመሳሳይ  አስተያየት ነው የሰጡት ።

ሾልዝ ለፑቲን የሰላም ጥሪውን ያቀረቡት ትራምፕ መጪው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡበት ሳምንት ውስጥ ነው። ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት በፍጥነት እንደሚያስቆሙ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ተናግረው ነበር ። እንዴት እንደሚያስቆሙት ዝርዝሩን ያልተናገሩት ትራምፕ ምዕራባውያን  ለክየቭ የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍና ወታደራዊ እርዳታም አጥብቀው በተደጋጋሚ ተችተዋል። ትራምፕ እስካሁን እቅዳቸውን አላሳወቁም። የዩክሬን ጦርነት ጉዳይ አሁንም ማከራከሩ ቀጥሏል። መጨረሻውን አብረን የምናየው ይሆናል።

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW