1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪነቱ የቀጠለው የወደብ ጉዳይ

ማክሰኞ፣ ጥር 7 2016

ኢትዮጵያ ራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ ከምትጠራው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ከምትላት ሶማሊላንድ ጋ ስለ ወደብ አጠቃቀም ፈረመችው የተባለው የመግባቢ ሰነድ አሁንም እያነጋገረ ነው ።ጉዳዩ ዲፕሎማሲያዊ እልባት እንዲያገኝ በሚልም በቃጣናው ተሰሚ የሆኑ ተቋማትም ስብሰባ በመጥራት ላይ ናቸው ።

የበርበራ ወደብ፤ ሶማሊላንድ
ኢትዮጵያ የመግባቢያ ሰነድ ከፈረመች በኋላ እጅግ አነጋጋሪ የሆነው የበርበራ ወደብ፤ ሶማሊላንድ። የዲፕሎማሲ ጫናው ኢትዮጵያን ከውጥኗ ይመልሳት ይሆን ?ምስል Yannick Tylle/picture alliance

በወደቡ ጉዳይ የስብሰባዎቹ መጠራት ምን ተጽእኖ ይኖረዋል?

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ ከምትጠራው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ከምትላት ሶማሊላንድ ጋ ስለ ወደብ አጠቃቀም ፈረመችው የተባለው የመግባቢ ሰነድ አሁንም እያነጋገረ ነው ። ጉዳዩ ዲፕሎማሲያዊ እልባት እንዲያገኝ በሚልም በቃጣናው ተሰሚ የሆኑ ተቋማትም ስብሰባ በመጥራት ላይ ናቸው ። ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪቃ ቀንድን በቅርበት የሚከታተሉ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ተንታኞች ስለ ስብሰባዎቹ አንደምታ እና ጫና ለዶይቸ ቬለ አብራርተዋል ።

ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ለንግድና ጦር ሰፈር አገልግሎት ይውላል የተባለውን ወደብ በምታገኝበት መንገድ ላይ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ የጉዳዩ አነጋጋሪነት እንደቀጠለ ነው፡፡ በተፈረመው የጋራ መግባቢያ ሰነድ ሉዓላዊነቴ ተነክቷል ከምትለው ሶማሊያ ባሻገር በሶማሌላንድም ውዝግብ መነሳቱ ነው የሚነገረው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ አረብ ሊግ እና የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት (IGAD) በጉዳዩ ላይ ለመምከር የጠሩት ስብሰባ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል ፡፡ 

የቀጠናዊ ዓለማቀፍ ድርጅቶቹ ጫና

የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ባለሞያው ዶ/ር ዳርስከዳር ታዬ ስለ ሁለቱ ዓለማቀፍ ድርጅቶች የስብሰባ ጥሪ እና ሊመጣ የሚችለው ተጽእኖ ተጠይቀው ይህን መልሰዋል፡፡

"መጀመሪያ የሁለቱ ድርጅቶች ልዩነት ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ አረብ ሊግ ኢትዮጵያ አባል ያልሆነችበት ድርጅት ነው፡፡ አባልም ለመሆን በሃይማኖትና ማንነት መመሳሰልን የሚጠይቅ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ፍላጎት በተቃራኒ የሚቆም መሆኑን ነው የምናውቀው፡፡ ሆኖም ማህበሩ ጠንካራ የሚባል አይነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአረብ አገራት ላይ የሚከሰቱትን ችግሮች እንኳ ሲቀርፍ አንመለከትም፡፡ ያም ሆኖ ግን ዲፕሎማሲ ላይ የሚያሳርፈው ጫና ይኖረዋል። ኢጋድን ግን በምናይበት ጊዜ ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት ብቻ ሳይሆን ለዓመታት የመራችው ድርጅት እና ተጽእኖዋም ከፍተኛ የሆነበት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ይህ ትርጉም ያለው ተቋም ነው፡፡ ግን ደግሞ ሁለቱ ተቋማት ወደቡን በተመለከተ ጠሩ የተባለው ስብሰባ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ የመግታት ምንም አይነት ስልጣንም ሆነ አቅም አይኖራቸውም" በሚል ሃሳባቸውን ዘርዝረዋል፡፡

የበርበራ ወደብ፦ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴና የአፍሪቃው ቀንድ

የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካን በቅርበት በመከታተል በመተንተን የሚታወቁት ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ ግን ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ለመፈራረም የበቃችውን ውሳኔ እንደ የዴፕሎማሲ አቅጣጫ ለውጥ ነው የተመለከቱት፡፡ የሁለቱን ተቋማት የስብሰባ ጥሪ ግን ያን ያህል የጎላ ተጽእኖ የማያመጣ ብለውታል፡፡ 

ነዋሪነታቸውን ለንደን ያደረጉት ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ ምስል Ato Abdurehman Seid

"ሶማሊያ ሁለቱም ተቋማት አባል ናት፡፡ ተቋማቱ እየሰሩ ያሉት የዲፕሎማሲ ዘመቻ መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተወሰደው እርምጃ የሶማሊያን ግዛት ያላከበረና ከግዛቷ ጋር የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ በዚህም ለተገንጣይዋ ግዛት እውቅና እሰጣለሁ ማለቷ አሉታዊ ፖለሲ ለመከተል የመጀመሯ ሂደት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሶማሊያ ይህ ነገር ወደ መወሳሰብና ጦርነት እንዳያመራ ትረት የሚያደርጉ ነው የሚመስለው፡፡ ያም ሆነ ግን ኢትዮጵያ አባል ያልሆነችበት አረብ ሊግ የበዛ ተጽእኖ የሚያመጣ አይመስልም፡፡ ኢጋድም የበዛ የኢትዮጵያ ጫና ስለሚስተዋልበት አዲስ ነገር አያመጣም፡፡ ምናልባት ጫና ሊያመጣ የሚችለው አፍሪቃ ኅብረት እና የተባበሩት መንግስታት የሚስተላልፉት ውሳኑ ነው፡፡"

የዲፕሎማሲ ጫናው ኢትዮጵያን ከውጥኗ ይመልሳት ይሆን ?

ሶማሊያ ግዛቴ ነው የምትለው ሶማሊላንድ ውስጥ የሚገኘው የበርበራ ወደብምስል Jonas Gerding/DW

ዓለማቀፍ ማኅበረሰቡ የሚያደርጉት ጫና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የወደብ ማግኘት ዓላማዋን ያጨናግፍባት ይሆን የተባሉት የዲፕሎማሲ ተንታኙ ዶ/ር ዳርስከዳር ግን በዚህ የሚስማሙ አይመስልም፡፡ "የወደቡን ፍላጎት እስካለን ድረስ የምናደርገው ይመስለኛል፡፡ ግን ደግሞ ነገሮች ከስጋት ነጻ ናቸው ማለት አይቻለም፡፡ ነገሩ ተቃውሞና ድጋፍ ብኖርበትም የተሸለ ድጋፍ ካለው አካል ጋር የመስራት ነውና እንደዚህ አይነት የአፍሪካን ቀንድ ፖለቲካ የሚቀይር ትልቅ ውሳኔ ለምን ሙሉ ድጋፍ አላገኘም ተብሎም አይጠበቅም" ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራሃማን ሰይድ ግን ኢትዮጵያ የተለያዩ አማራጮችን ብትመለከት ይበጃል ባይ ናቸው፡፡ "የኢትዮጵያ የወደብ አገልጋይነት ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቿም ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህ አገሪቱ ከሞምባሳ እስከ ፖርት ሱዳን ሉትን ወደ ስምንት ወደብ በአማራጭነት ዋጋም አስቀንሳ መጠቀም ትችላለች፡፡ ይህ ደግሞ በስምምነት ብቻ መሆን ይገበዋል" ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ የወደብ የመግባቢያ ሰነድ ከራስገዟ ሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟን ተከትሎ  የሶማሌላንድ መከላከያ ሚኒስትር ውሳኔውን ተቃውመው ከስልጣናቸው መልቀቃቸውም የተሰማው በዘሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ደግሞ ውሳኔውን ተቃውመው ለኣለማቀፍ ማህበረሰብ ጥሪ ካሰሙ በኋላ እንደ ኤርትራ እና ግብጽ ያሉ አገራን በመጎብኘት ስባትሉ ታይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በመግባቢያ ሰነድ ሂደቱ የጣስኩት ዓለማቀፍ ሕግ የለም ስትል ትሞግታለች፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW