1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

አነጋጋሪ የሆነው አዲሱ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት

ዓርብ፣ መስከረም 13 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ. ም. አዲስ የትምህርት ዘመን መጀመር ብቻ ሳይሆን፤ በመላው ሀገሪቱ አዲስ ሥርዓተ ትምህርትም ተግባራዊ ሆኗል። በወጣቶች ዓለም ክፍለ ጊዜ ያነጋገርናቸው በተለይም መምህራን እና ወላጆች አዲስ ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን ቢደግፉም አያይዘው የሚያነሷቸው በርካታ ትችቶችም አሉ።

Äthiopien Studenten im Klassenraum
ምስል Shewangizaw/DW

አነጋጋሪ የሆነው አዲሱ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት

This browser does not support the audio element.

የ2015 ዓመተ ምህረት የትምህርት ዘመንን ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መሆን የጀመረበት መሆኑ ነው። መምህር ሙከመል ደቡብ ክልል ስልጤ ዞን አካባቢ ከዚህ ቀደም ከ 5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ያስተምሩ ነበር። ዘንድሮ ግን በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል የጀነራል ሳይንስ መምህር ናቸው። የሚያስተምሩበትን መጽሐፍ ያገኙት ግን ትምህርት የጀመረ ዕለት ነው። « መስከረም 9 ነው ያገኘነው። ተማሪ እስከጭራሹ አላገኘም። መምህሩም አንድ ፍሬ ነው ያገኘው።» ይላሉ። ይህ ብቻ አይደለም ። ከዚህ ቀደም የባዮሎጂ መምህር የነበሩት ሙከመል ከባለፈው ሰኞ አንስቶ ሦስት ትምህርቶችን ጨምቀው እንደ አንድ የትምህርት አይነት ማስተማር ይኖርባቸዋል። « ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና ሶሻል ጀነራል ሳይንስ ተብሎ መጣ። ለዚህ ደግሞ የኮርስ ትውውቅ ወይም ስልጠና ሳይሰጠን ነው ወደ ትምህርቱ የገባነው።» ይህም በተማሪው እና መምህራን ዘንድ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ነግረውናል።
ኢብራሂም ክብረት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ልጅ አላቸው። በደሴ ዙሪያ ከላላ አካባቢ የሚኖሩት እኝህ ወላጅ  የመማሪያ መጽሐፉ እንኳን ተማሪዎች ጋር ይቅርና መምህራኑ ጋርም አልደረሰም ይላሉ ። በዚህም የተነሳም ደካማ ነበር ከሚሉት የቀድሞ የትምህርት ሥርዓት ጋር ለማነፃፀር በቂ መረጃ አላገኙም። « መጽሀፉ እንደ አዲስ አበባ ትላልቅ ከተሞች ካልሆነ በቀር ወደ ገጠር አልወረደም። »

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሚመለከታቸው  በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶችን ሲሆን የማኅበረሰብ እና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶችን እንደማያካትት ተገልጿል።  በትምህርት ሚኒስቴር ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ እንደሚነበበው  « አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል እውቀትን ፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ፣ እንዲሁም ተግባር ተኮር ትምህርትን ከስነ ምግባር ትምህርት ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ ነው»።  በወሎ ዩንቨርስቲ የግዕዝ መምህር የሆኑት ሙሉዓለም ምንም እንኳን ጥያቄ ውስጥ የሚከቷቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ለሀገሪቱ አስፈላጊ ነበር ይላሉ።  « ለምሳሌ ግብረገብ የሚባለው ነገር ባለመኖሩ ትውልዱ ተበላሽቷል ብዩ አስባለሁ ። ይህ ትምህርት ከመጀመሪያው አንስቶ ቢሰጥ ኖሮ እንደዚህ ሀገርን የማይወድ፤ አዛውንቶችን ወላጅን እና መምህራንን የማያከብር ትውልድ አይፈጠርም ነበር»


መምህር ሙሉዓለም ለማስተማሪያ ሞዴል ተብለው በኮምፕዩተር PDF በሚባለው መልኩ በኢንተርኔት አማካኝነት የተሰራጩትን መጽሐፎች የፈተሹት በራሳቸው ተነሳሽነት እና ያገባኛል በሚል መንፈስ  እንደሆነ ገልፀውልናል። በተወሰኑት እና አየኋቸው የሚሏቸው ማስተማሪያ መጽሐፎች ላይ ተመርኩዘው አዎንታዊ እና አሉታዊ የሚሉትን ይዘረዝራሉ። «  ለምሳሌ ግብረ ገብ፤ የሙያ ስራዎች መካተታቸው ጥሩ ነው። ነገር ግን ታሪክ ላይ ትንሽ ዝብርቅርቅ ማለቱ ደስ አይልም።  መምህር ሙሉዓለም ሌላም የታዘቡት ነገር አለ። ይህም አዲሱ የአራተኛ ክፍል የሂሳብ መፅሀፍ ላይ ተጽፎ ነበር የሚሉት ነው። « የተወሰነ አስተካክለንዋል ብለዋል። መጀመሪያ ላይ የግዕዝ ቁጥሮች ቀጥታ ከግሪክ የመጡ ናቸው ይል ነበር። ኋላ ላይ ግን ይህን አውጥተውታል።   በቃ የኢትዮጵያ ቁጥር የግዕዝ ቁጥር ነው ይላል። ስህተቱ ይህ ቀጥታ ከግሪክ ነው የመጣው የሚለው ነው። እንዲህ ነው የሚል የተፃፈ መፅሀፍ ምንጭም የለም።  በርግጥ ግዕዝ ከሌላ የወረሳቸው ነገር አለ። ነገር ግን እንደዚህ አድርጎ ወስዷል ማለቱ ስህተት ነው።» ይላሉ የግዕዝ መምህሩ።

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የታሪክ መፅሀፎች ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ በትክክሉ አልተፃፈም ሲሉ ይተቻሉምስል Solomon Muche/DW

ሌላው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ያላቸውን አስተያየት ያካፈሉን የዩንቨርስቲ መምህር መለሰ ይባላሉ። « ባለድርሻ አካላት አዲሱ ፖሊሲ ላይ ተሳትፈዋል? መምህራንስ ብቁ ናቸው ? ህፃናትን የሚቀርፁት አስተሳሰባቸው ምን አይነት ነው? ከዘር ነፃ ናቸው? » በደፈናው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መሆኑን የማይቃወሙት መምህር መለሰ ፤ ለመምህራን የሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም ለትምህርት ጥራቱ መሻሻል አንዱ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ይናገራሉ። 
አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ እቃወመዋለሁ የሚሉት እና ስማቸውን ያልገለፁልን ተከታዩ የግል ትምህርት ቤት መምህር  ስርዓቱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የፔዳጎጂ ስልጠና ሊሰጠን ይገባ ነበር ይላሉ። ይህ ባለመሆኑ ሥራቸውን አጥተዋል።  « መጀመሪያ ለመምህራኑ አስቀድመው መናገር ነበረባቸው። አብዛኛው የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ የፔዳጎጂ ስልጠና ስልጠና የላቸውም። እኔ ለምሳሌ ስራ አጥቼ እቤት ከተቀመጥኩ ሁለት ሳምንት ሆኖኛል።» ይላሉ ከትምህርት ሚኒስቴር መፍትሔ የሚሹት መምህር።
የመንግሥት ሠራተኛ እንደሆነ የነገረን እረቀቀ የ 27 ዓመት ወጣት ሲሆን ትምህርት ቤት በሚሄዱ ታናሽ ወንድም እና እህቱ የተነሳ ተግባራዊ መሆን የጀመረውን ሥርዓተ  ትምህርት ይዘት በመፈተሽ የደረሰበት ድምዳሜ ማኅበረሰቡን የሚስተምር ሳይሆን የሚያራርቅ እንደሆነ ነው። « የ4ኛ እና የ8ኛ ክፍል መፅሀፍት በቴሌግራም በሶፍት ኮፒ ደርሶኛል።  በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚባሉትን እያጣረዝኩ ለማየት ሞክሬያለሁ።  ስለሆነ ብሔር ጨቋኝ ተጨቌኝ በጣም በዝርዝሩ ማብራሪያ ይሰጣል። በጣም ከእውነት የራቁ የታሪክ መሰራረቅ አለ። የተፃፉት ምንም ምንጭ የላቸውም።  የሆነ ሰው ተነስቶ እሱ እንዳሻው የፃፈ ነው የሚመስለው። ይህ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብዬ አላምንም። ጉዳታቸውንም በቅርቡ የምናየው ይመስለኛል።»

ገላን የሚገኘው የትምህርት መፅሀፍት ማተሚያምስል Seyoum Getu/DW

አስተያየታቸውን ያካፈሉን በርካታ መምህራን የመማሪያ መጽሐፎቹን ያገኙት ታትመው ሳይሆን በኮምፕዩተር ሰነድ ማለትም ሶፍት ኮፒ መልክ እንደሆነ ገልፀውልናል። የሚያነሷቸው ቅሬታዎች በርግጥ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት ውስጥ ይገኛሉ? ወይስ በኢንተርኔት የተሰራጩ የሀሰት ወሬዎች ናቸው? መጽሐፎቹ በሰዓቱ ወደ መምህራን እና ተማሪዎች ሳይደርሱ ሥርዓቱ ተግባራዊ የሆነውስ ለምንድን ነው? እነዚህን እና ሌሎች ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችን ጉዳዩ ከሚመለከተው ትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለማግኘት እና በዚህ ዝግጅት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም። 

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW