1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንዳንድ የፋኖ አመራሮች ከመንግሥት ጋር ለመወያየት አወንታዊ ምላሽ ሰጡ መባሉ

ሐሙስ፣ መስከረም 16 2017

በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፋኖ አመራሮች ጋር መወያየቱን መንግስትንና የፋኖ ታጣቂዎችን ለድርድር አንዲቀራረቡ የአመቻችነት ሚና የተሰጠው የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት አስታወቀ፣ ምክር ቤቱ በውይይቱ አወንታዊ ምላሽ ማግኘቱን ገለፀ፡፡ የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ለማድረግ መጠየቁንም አስታዉቋል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የፋኖ ኃይሎች በላሊበላ ከተማ
ፎቶ ማህደር፤ የፋኖ ኃይሎች በላሊበላ ከተማ ምስል Mariel Müller/DW

አንዳንድ የፋኖ አመራሮች ከመንግሥት ጋር ለመወያየት አወንታዊ ምላሽ ሰጡ መባሉ

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፋኖ አመራሮች ጋር መወያየቱን መንግስትንና የፋኖ ታጣቂዎችን ለድርድር አንዲቀራረቡ የአመቻችነት ሚና የተሰጠው የአማራ ክልል  የሰላም ምክር ቤት አስታወቀ፣ ምክር ቤቱ በውይይቱ አወንታዊ ምላሽ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡ የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ለማድረግ መጠየቁንም አስታዉቋል፡፡ በአማራ ክልል የልዩ ኃይልን እንደገና ለማደረጀት በሚል ከተነሳው ውዝግብ ጋር ተከትሎ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት  ከአንድ ዓመት በላይ  አስቆጥሯል፡፡ጦርነቱ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፣ ብዙዎችንም ለአካል ጉዳት ዳርጓል፣ በክልሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይም ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡

ጦርነቱ እንዲቆም የሰላም ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት አልተገኘም፡፡ መንግስትና የፋኖ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ የአመቻችነት ሚና የተሰጠው የአማራ ክልል የሰላም ጉባኤ በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ የጉባኤው ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ሁለቱ አካላት ወደ ድርድር እንዲመጡ ለማድረግ ከአንዳንድ የፋኖ ታጣቂ አመራሮች ጋር በተናጠል ተወያይተዋል፣ በውይይቱም አወንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ነው ያብራሩት፡፡

በተደራጀ በአንድ ሆነው ባይመጡም በተናጠል የአገኟቸው የፋኖ አመራሮች ለመደራደር መልካም አመለካከት እንዳላቸው ተናግረዋል፣ “ በተናጠል ደረጃ ድርድሩን የሚደግፉ አሉ፣ ይህንን ደግሞ በተጠናከረ መንገድ እንቀጥልበታለን” ነው ያሉት፡፡ ፋኖ ወደ አንድነት ይመጣል፣ አንድ ሆኖ መግለጫ እንደሚሰጥ ሚያምኑ አመራሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ምክር ቤቱም ይህ እንዲሆን እንደሚሰራ አቶ ያየህይራድ ተናግረዋል፡፡ በቅንነት የድርድር ሀሳቡን የሚደግፉ ኃይሎችን እንደሚያመሰግኑም ሰብሳቢው አመልክተዋል፣ ጥሩ የሆነ አዝማሚያ እንደሚታይና፣ በቅርቡም መፍትሔ ሊሰት የሚችል አንድ ሆነው መግለጫ ለመስጠት እንደሚፈልጉ የገለፁላቸው አንዳንድ የፋኖ ወገኖች እንዳሉም አስረድተዋል፡፡

እስካሁን የአማራ ክልል መንግስት መልካም ምላሽ እንደሰጠ ሰብሳቢው አመልክተው፣ በፌደራል ደረጃም ከሰላም ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፣ ለምክር ቤቱም አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግለታል መባላቸውን አስረድተዋል፣ የሰላም ምክር ቤቱን ጥረትም የሰላም ሚኒስቴር እንደሚደግፈው እንደተገለፀላቸው አብራርተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር ለመወያየትም ቀጠሮ እንዲያዝላቸውና ምላሽ እየጠበቁ እንደፎነ ገልጠዋል፡፡ “ ከአርሳቸው(ከጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ) ጋር ቀጠሮ እንዲያዝልን ጠይቀናል፣ ምናልባት በአንድ ወቅት እናገኛቸዋለን ብለን እናስባለን” በሁለቱም አካላት በኩል ፈተናዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ያየህይራድ፣ ሆኖም ሁለቱም ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ “ትግላችን ይቀጥላል” ብለዋል፡፡ የሰላም ምክር ቤቱ ዋና ዓላማ ሁለቱ ኃይሎች በፈለጉት ጊዜና ቦታ፣ እንዲሁም በሚመርጧቸው አደራዳሪዎች የሚፈልጓቸውን ጥያቄዎች አንስተው እንዲወያዩና ችግሮች እልባት እንዲገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ስለጉዳዩ ከመንግስትም ሆነ ከፋኖ በኩል አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካልንም፡፡

 

ዓለምነው መኮንን

 

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW