1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አንድ ለአንድ- የሕወሓት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዝ እና ቀጣይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ፀሀይ ጫኔ
ዓርብ፣ ግንቦት 15 2017

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋና ተዋናይ ሆኖ የቆየው ሕወሓት፤ ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ አስታውቋል።ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልህ ስፍራ ይዞ የቆየው ህወሓት መሰረዙ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ፖለቲካ ምን ያዞ ይመጣ ይሆን?

ዳንኤል ብርሃነ፤የህግ ባለሙያ ፣ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች
ዳንኤል ብርሃነ፤የህግ ባለሙያ ፣ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችምስል፦ Daniel Birhane

አንድ ለአንድ- የሕወሓት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዝ እና ቀጣይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ

This browser does not support the audio element.

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋና ተዋናይ ሆኖ የቆየው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ አስታውቋል።ሕወሓት ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናው የተሰረዘው «የሚጠበቅበትን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ» የተሰጠው ጊዜ በመጠናቀቁ  መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ/ም ባወጣው አሳውቋል።
የአሁኑ  የህወሓት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዝ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ምርጫ ቦርድ በ2013 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርቲውን የሰረዘው የትግራይ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ ፓርቲው «በአመጻ ድርጊት» መሳተፉን በመግለጽ ነበር። በዚህ ወቅት ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጆም ነበር።

ነገር ግን የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነቱ እንዲያበቃ ያደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት በህወሓት እና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መፈረሙን ተከትሎ፤ በህወሓት ላይ የተጣለው የአሸባሪነት ፍረጃ የተነሳ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ መሰረት  ህወሓት «በልዩ ሁኔታ»እንዲመዘገብ አድርጓል።
ሆኖም ግን  ምዝገባውን ተከትሎ ሕወሃት እንዲፈጽም የሰጠውን ትዕዛዝ  እንዲከብር በተለያየ ጊዜ ማሳሰቢያ ቢሰጠውም፤ ፓርቲው "በሕግ የተጣለበትን ግዴታ አልፈጸመም" ሲል የምርጫ ቦርድ የፓርቲውን መሰረዝ አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ  አመልክቷል።
ሕወሓት «በልዩ ሁኔታ» ከመመዝገቡ በፊት ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፤ነገር ግን ምርጫ ቦርድ  የተሰረዘን ፓርቲ መልሶ ለመመዝገብ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን በመጥቀስ የፓርቲውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። 

ዾክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል፤ የህወሓት ሊቀመንበርምስል፦ Million Haileselassie/DW

በሌላ በኩል ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት ህወሓት ነሐሴ 3 ቀን 2016 ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን የምዝገባ የምስክር ወረቀት “ያልተቀበለው” መሆኑን በቅርቡ አስታውቆ ነበር። ፓርቲው “ነባሩ ሕጋዊ የዕውቅና ሰርተፍኬት” ሊመለስለት እንደሚገባ ገልጿል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን “የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ሠርተፊኬቱን እና ደብዳቤውን በሚገባ አይተው፣ አንብበው እና ተስማምተው በፈቃዳቸው ፈርመው ከወሰዱ በኋላ ‘በልዩ ሁኔታ’ ተመዝግቦ የተሰጠን የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ አንቀበለውም ማለት ተቀባይነት የለውም” ብሏል። 

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ፤ ላለፉት 50 ዓመታት በትግራይ ብሎም በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ዋና ተዋናይ የነበረ አንጋፋ ፓርቲ ነው።ምስል፦ Million Haileselassie/DW

በዚህ ሁኔታ ከ50 ዓመታት በላይ በትግራይ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ  ፖለቲካ ጉልህ ስፍራ ይዞ  የቆየው ህወሓት፤ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙ በትግራይ ብሎም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን አድምታ አለው ? ምንስ ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል ? መፍትሄውስ? የፓርቲው መሰረዝ ህጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ?  እነዚህን እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ የዛሬው የአንድ ለአንድ ዝግጅት የህግ ባለሙያ፣ ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዳንኤል ብርሃነን እንግዳ አድርጓል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።   

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW