1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አንድ - ለ - አንድ፤ ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር

ዓርብ፣ ሐምሌ 11 2017

አቶ በቀለ ገርባ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ በኋላ ተፈጥሮ የነበረዉን ረብሻ ተከትሎ በቁጥጥር ስር ዉለዉ ለ 18 ወራቶች እስር ላይ ቆይተዋል። ከእስር እንደወጡ፤ ከእስር እንዲፈቱ ሲጠይቅ በረዉን ማኅበረሰብ ለማመስገን ወደ ዉጭ ወጥተዉ አልተመለሱም። አሜሪካ ሲኖሩ ሦስት ዓመት ሆናቸዉ።«ኦቦ በቀለ የጠፉ? ኢትዮጵያ አልናፈቀቾትም?»ብለናቸዋል።

አቶ በቀለ ገርባ፤ የቀድሞዉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)ተቀዳሚ ምክትል
አቶ በቀለ ገርባ፤ ተጽኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ ምስል፦ Bekele Gerba/DW

አንድ - ለ - አንድ፤ ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር

This browser does not support the audio element.

አንድ - - አንድ ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር

እንግዳችን ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት የቀድሞዉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)ተቀዳሚ ምክትል አቶ በቀለ ገርባ የአንድ -ለ - አንድ ዝግጅት እንግዳችን ናቸዉ። አቶ በቀለ ገርባ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተፈጥሮ የነበረዉን ረብሻ ተከትሎ በቁጥጥር ስር ዉለዉ ለ 18 ወራቶች ታስረዋል። ከእስር እንደወጡ፤  እንዲፈቱ ሲጠይቅ የነበረዉን ማኅበረሰብ ለማመስገን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተጓዙ በኋላ እዝያዉ ጥገኝነት ጠይቀዉ ኑሮዋቸዉን በዩናይትድ ስቴትስ አድርገዋል። ዶቼ ቬለ ኦቦ በቀለ ገርባን እንደምን አሉ፤ ሲል በስልክ አግኝቶ ለአስርተ ዓመታት ሲታገሉበት ከነበረዉ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ለምን እንደጠፉ ሲል ጠይቋቸዋል።

ኦቦ በቀለ ገርባ የት ጠፉ?

«ከአገር ከወጣሁ እርግጥ ነዉ ሦስት ዓመት ሆኖኛል። አገር ዉስጥ ባለዉ ፖለቲካ የኔ ሚና አስፈላጊ የሚያደርገዉ ሁኔታ ባለመኖሩ፤ ከሁለት ዓመት በፊት የነበርኩበትን የፓርቲ አባልነት እና ሃላፊነት የለቀኩ መሆኔን በይፋ አሳዉቄ፤ ፓርቲዬም ጥያቄን ተቀብሎ አሰናብቶኛል። ግን በዝያ ወቅትም እንደገለፅኩት ጨርሶ ከፖለቲካዉ መድረክ ፈጽሞ የመገለል ሳይሆን፤ ልምዴ እና አስተዋጾዬ፤ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት በአገሬ ጉዳይ አስተያየቴን እንደምሰጥ አስታዉቄ ነበር። በዝያ ምክንያት በኢንተርኔትም ሆነ በአዳራሽ ዉስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ በተሳታፊነት እና በተናጋሪነት ተካፍያለሁ፤ እካፈላለሁም። በሚዲያ ላይ እጅግም ፖለቲካዊ ሳይሆኑ፤ ሰብዓዊ እና ሞራላዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በአገሪቱ እየተካሄዱ ባሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ላይም፤ አልፎ አልፎ ድምፄን አሰማለሁ። ስለዚህ ተሳትፎዬ እንደቀድሞ ባይሆንም፤ ስለአገሪ ሁኔታ መናገሪን አላቋረጥኩም። አላቋርጥምም» 

በፖለቲካዉ ዓለም በተለይ ያለፈዉን ሥርአት ለመጣል በግልም ሆነ በፓርቲ ብዙ ከታገሉት ኢትዮጵያዉያን ፖለቲከኞች መካከል እርሶ የሚጠቀሱ ኖት እና፤ ለአስርተ ዓመታት የታገሉበትን ጉዳይ እዳር ሳያደርሱ ገሸሽ ማለት ይቻላል? ለምን ብዙ ስለማይታዩ ነዉ።  

የአስርተ ዓመታት ትግልን እዳር ሳያደርሱ መተዉ ይቻላል?

«አዎ ትክክል ነዉ። ብዙም አልታይም። ተሳትፎዩ ላይ አንዳንድ ገደቦች አድርጌያለሁ። ገደብ ያደረኩባቸዉ ምክንያቶችም፤ አንደኛ፤ ቀድሞ የፓርቲ ሃላፊነቴ የሚጥልብኝ ግዴታ ነበረ። ስለዚህ በሃላፊነቴ ወጥቼ መናገር ይገባኝ ነበር። አሁን ግን ያ ሃላፊነት የለብኝም። ሁለተኛ፤ እኔ ማድረግ የምችለዉን ነገር ሌሎች አገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ያሉ ሰዎች አሉ። ስለዚህ አንዱ የሚናገረዉን መልሶ መናገር  አስፈላጊነቱ ብዙም ስለማይታየኝ፤ ሌላዉ ሰዉ ከሰራዉ የሚል አስተያየት ስላለኝ ነዉ። ሦስተኛዉ፤ እና ዋንኛዉ ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካዉ አካሄድ፤ ቀድሞ ከማዉቀዉ እና ከማስበዉ አካሄድ ዉጭ እየተጓዘ በመሆኑ ነዉ። የፖለቲካ ባህሉ እጅግ ተቀይሯል። ድሮ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት አነሰም በዛ፤ በክርክር በሃሳብ የበላይነት በዉይይት፤ ባይስማሙም ተቀራርቦ በመነጋገር ጥረት ይደረግ ነበረ። አሁን ግን ያ ሁኔታ አይታይም። ሚዲያን ያለአግባብ ኢ-ሞራላዊ በሆነ መንገድ፤ በገፍ በመጠቀም አድማጭን በማደናገር እና የመጡብህ ፖለቲካ ፍርሃትን በማሰራጨት ፖለቲካዉ በጣም ቆሽሿል።» አንድ - ለአንድ፦ ከአቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ጋር

የፖለቲካ ባህሉ ተቀይሯል

ኦቦ በቀለ፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ለ 18 ወራቶች ታስረዉ ከተለቀቁ በኋላ ነዉ አገር ለቀዉ የወጡት። ምናልባት ይህ በእስር የቆዩበት ጊዜ የጥሞና ጊዜ ሰጥቶት ይሆን ፖለቲካዉን እርግፍ አድርጎ ለመተዉ የወሰኑት እና አገር የለቀቁት?

« እኔ በሁሉም የእስራት ዙሮች በቂ የማሰብያ እና የተሞክሮ ጊዜ ነበረኝ። መጀመርያ ላይ ከነአንዱዓለም አራጌ፤ ከጀነራል አሳምነዉ ጽጌ፤ ከጀነራል ተፈራ ማሞ ፤ ከነተመስገን ደሳለኝ ጋር ነዉ የታሰርኩት። ሁለተኛዉ ዙር እስር ላይ፤ ከነቴድሮስ አስፋዉ፤ ከዮናታን ተስፋዬ ፤ ከነማስረሻ ሰጤ፤ ከነደጀኔ ጣፋ፤ ከነአበበ ኡርጌሳ እና ሃይሌ ማሞ ጋር ነዉ የታሰርኩት። እነዚህ ሰዎች ዛሬ የተለየ ዓለም ዉስጥ ያሉ ናቸዉ። ለሦስተኛ ጊዜ የታሰርኩት ከጃዋር መሐመድ፤ ከነሃምዛ ቦረና ጋር ነዉ። በታሰርኩባቸዉ ዙሮች ሁሉ በቂ የሆነ ትምህርት ያገኘሁበት ከብዙ ሰዎች፤ ጋር ለመገናኘት እድል ያጋጠመኝ ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ያየኋቸዉ ሁሉ ድምር ነዉ የፖለቲካ ባህሉ ተቀይሯል ያሰኘኝ።»

ጀዋር መሐመድ እና ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምልከታው

ኢትዮጵያ ትናፍቆታለች?

«እኔ በየአንዳንዱ ደቂቃ ስለአገሪ አስባለሁ። ተወልጄ ያደኩበት፤ የተማርኩበት፤ ስራ የሰራሁበት፤ ከብዙ ሰዎች ጋር የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን የሰራሁበት፤ አገር ምድሩ ይናፍቀኛል፤ አየሩ፤ ምኑ ሁሉ ይናፍቀኛል። እዚህ አገር በስደት የማሳልፈዉ ጊዜ እና  ዘመኔ አብቅቶ፤ አንድ ቀን ለአገሬ እበቃለሁ የሚል፤ ብርቱ እምነት ነዉ ያለኝ። ፈጣሪ ይረዳኛል የሚል እምነትም አለኝ።»

ጉምቱዉ ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ ስለሰጡን ቃለ-ምልልስ በ DW ስም በማመስገን ሙሉዉን ዉይይት የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW