አንድ - ለ - አንድ:- ከኡስታዝ ጀማል በሽር ጋር
ዓርብ፣ መስከረም 16 2018
አንድ - ለ - አንድ:- ከኡስታዝ ጀማል በሽር ጋር
ኡስታዝ ጀማል በሽር የአንድ ለ አንድ ዝግጅታችን እንግዳ ናቸዉ። ኡስታዝ ጀማል በሽር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደቱን በማጠልሸት ቅቡልነት ለማግኘት ግብጾች የተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑን አይቼ ቁጭት ይዞኝ እኔም የዛሬ ስድስት ዓመት ስለ ሕዳሴ ግድብ ስለ አባይ ዉኃ አጠቃቀም፤ የኢትዮጵያን አቋም ይዤ ለግብፅና የአረቡን ሚዲያ መሞገት ጀመርኩ ብለናል። ለአገሪ ልጆችም በተለያዩ ሚዲያዎች በአረብኛ ስለ ሕዳሴዉ ግድብ የሚወራዉን እየተረጎምኩ ማቅረብ እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ጀመርኩ ሲሉም አክለዋል። አጫዉተዉናል። የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ኡስታዝ ጀማል በሽር ስለ ህዳሴ ግድብ በሚዲያ ከሚሞገት ባሻገር በዉጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የእርዳታ ጥሪ አድርገዉ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሕዳሴዉ ግንባታ ገንዘብን አሰባስበዋል። ኡስታዝ ጀማል በሽርን እንኳን ደስ ያሎት የሕዳሴዉ ግድብ ለመመረቅ በቃ ስንል ሃሎ ብለናቸዋል። ኡስታዝን በስልክ ያገኘናቸዉ ለሕዳሴዉ ምርቃት በእንግድነት ኢትዮጵያ ተጋብዘዉ ሳለነዉ። ኡስታዝ ጀማል በሽር የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ እና መስራችም ናቸዉ።
የሕዳሴዉን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያዉያን በግንባታዉ፤ ገንዘብ በማዋጣት እና በግንባታዉ የተለያዩ ዘርፎች ተሳትፈዋል። ግድቡ ለምርቃት መብቃቱ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ ደስ ያሰኘ ነዉ። የግድቡን ግንባት በተመለከተ የኡስታዝ ጀማል በሽር ተሳትፎ ደግሞ ለየት ይላል። የአረቡ ዓለም ሚዲያ ስለ ሕዳሴዉ ግድብ የሚዘግቡትን በማነፍነፍ እና ለኢትዮጵያዉያን በመተርጎም፤ የአረቡ ዓለም ስለሕዳሴ ግድብ በሚጠራዉ ዉይይት ላይ በመቅረብ እና በአርብኛ በመሞገት ግንዛቤን በማስጨበጣቸዉ ይታወቃሉ። ኡስታዝ ጀማል የህዳሴዉን ግድብ በተመለከተ የያዙትን ዘመቻ የጀመሩት ከስድስት ዓመት በፊት እንደሆነና አሁንም እንደሚቀጥሉበት ነግረዉናል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከብዙ መከራ በኋላ ለምርቃት በመብቃቱ ልዩ ደስታ እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ኡስታዝ ጀማል፤ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደቱን በማጠልሸት ቅቡልነት ለማግኘት ግብጾች የተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ ሲያደርጉ እንደቆዩ እና አሁንም ይህንን በመግጠም የግንዛቤ ማስጨበጫ መረሃ-ግብራቸዉን እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል። እንደ ኡስታዝ ግብጾች ከሁለት መቶ በላይ የቴሌቭዥን እና የዲጂታል ሚዲያዎችን ተጠቅመው ስለ ኢትዮጵያና ሕዳሴው ግድብ ግንባታ የተሳሳቱ ዜናዎችን፣ መረጀዎችን ለአረብኛ ተናጋሪዉ ዓለም እንደሚያሰራጩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ይላሉ ኡስታዝ ጀማል በሽር፤ የዓረቡ ዓለም እውነታውን እንዲረዳ፣ የህዳሴው ግድብ የሚይዘው ውኃ የታችው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያስከትል ትክክለኛ መረጃ በመስጠት በርካታ የዓረብ ሀገራት ግለሰቦች ለህዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን መስጠታቸዉን አክለዉ ተናግረዋል። ኡስታዝ ጀማል በሽር ከ DW ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቃለ-ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ