1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

በርካታ ተማሪዎች የወደቁበት የ2015 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና

ማክሰኞ፣ መስከረም 29 2016

በ2015 ዓ,ም ኢትዮጵያ ውስጥ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከተፈተኑት ማለፊያ ውጤት ያገኙት ቁጥር ጥቂት መሆኑ ይፋ ሆኗል። በዚህም ከተፈተኑት ከ96 በመቶ በላይ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችል ነጥብ አላመጡም።

ፎቶ፤ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ
ትምህርት ሚኒስቴር በጽሑፍ ባወጣው መግለጫ ባለፈው ዓመት ከኩረጃ የጸዳ ፈተና መስጠት መቻሉን አመልክቶ በውጤቱ ከ50 በመቶ በላይ ያገኙ ተማሪዎች ቁጥር ማነስ አሁንም በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያለው ስብራት ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው ብሏል። ፎቶ፤ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ብርሃኑ ነጋምስል Hanna Demissie/DW

አስደንጋጩ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤት

This browser does not support the audio element.

በ2015 የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 845 ሺሕ 099 ተማሪዎች ውስጥ፤ 817 ሺሕ 838 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች የሆነ ውጤት ማምጣታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል። በሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በብሔራዊ ደረጃ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተቀመጡት ተማሪዎች ውስጥ 27 ሺሕ 267 ተማሪዎች ብቻ ናቸው 50 በመቶ እና ከዛ በላይ የሆነ ውጤት ያገኙት።   

በተጠቀሰው ዓመት ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አስተምሬ አብቅቻለሁ ብለው ተማሪዎቻቸውን  ለፈተና ካቀረቡት 3,106 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1,328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም። ይህ ለሁለት ተከታትታይ ዓመታት የተመዘገበ አሳዛኝ ኹነት ነው።  በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመገናኛ ብዙሃን እና የኮምንኬሽን/ተግባቦት/ መምህር የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው ጥላሁን ለዶቼ ቬለ /DW/ «ምንም አዲስ ነገር የለም የሚጠበቅ ነው ይልቁን ወገባችንን ጠበቅ አርገን ሌብነትን የሚጠላ መኮረጅን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት ከታች መጀመር ካልቻልን ከድጡ ወደማጡ ነው የምንገባው» በማለት የማማር ማስተማር ሄደቱ ያለበትን መሰረታዊ ችግር ይገልፃሉ።

በ2015 የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 845 ,099 ተማሪዎች፤ 817,838 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች የሆነ ውጤት ማምጣታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ፎቶ ከማኅደር፤ ተማሪዎች ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ውጤቱ  ስርነቀል ወደሆነ እና መሠረታዊ መፍትሄ ሊያመጣ ወደሚችል አቅጣጫ በአፋጣኝ እንድንገባ የሚያመላክት ነው ያሉት ዶክተር ጌታቸው አሁን ያለው የሀገራችን የትምህርት ፖሊሲ ችግር የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ግብር ከፋይ ሕዝብ አፋጣኝ ርብርብ የሚፈልግ ነው ይላሉ። ዶቼ ቬለ /DW/ ያነጋገራቸው ተማሪ እና ወላጅ «ምንም አዲስ ነገር የለም የትምህርት ሂደቱ የሚታወቅ ነው ያልዘሩት አይበቅልም» ነው ያሉት። በ2014 ትምህርት ዘመን ለፈተና ከተቀመጡ 896 ሺሕ 520 ተማሪዎች፣ ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ወይም ከ50 በመቶ በላይ ያስመዘገቡት 29 ሺሕ 909 እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፤ የዘንድሮ ውጤት በ0.01 በመቶ ከአምናው መቀነሱ ታይቷል።

የ2015 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ውጤታቸውን ከዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ በፈተናዎች ኤጀንሲ ድረገጽ ላይ እየገቡ ማየት እንደሚችሉ የገለጸው የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት፤በፈተና ውጤቱ ላይ ቅሬታ ያለቸው በሚቀጥሉት ስድስት ቀናት ማለትም እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉም አስታውቋል። የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት በእርማቱ ላይ ምንም ችግር የለብኝም ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።   

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW