1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኅብረተ ሰብሰሜን አሜሪካ

አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሶማሊያን በ72 ሰዓታት ውስጥ ለቅቀው እንዲወጡ ታዘዙ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20 2017

ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማልያ ዋና ከተማ ሞቅዲሾ ውስጥ የተመደቡ አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማትን ከትናንት ጀምሮ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሀገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች ።

የሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ
ጥበቃ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹምስል Hassan Ali ELMI/AFP

«የመጨረሻው ዲፕሎማሲያዊ ግምኙነትን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ነው

This browser does not support the audio element.

ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማልያ ዋና ከተማ ሞቅዲሾ ውስጥ የተመደቡ አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማትን ከትናንት ጀምሮ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሀገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች ።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፦ ኢትዮጵያዊዉ ዲፕሎማት ዕውቅናቸው እንዲሰረዝ የተደረገው «ከዲፕሎማሲያዊ ኃላፊነታቸው ጋር የማይገናኝ ተግባር» ሲፈጽሙ በመገኘታቸው ነው ።

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም አልተሳካም ።  አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ሃገራት መሰል ርምጃ የሚወስዱት «ቅር መሰኘታቸውን ለማሳየት ነው» ብለዋል ። «ከላኪ ሀገር ጋር መደማመጥ አለመቻላቸውን፣ የጋራ ፖለቲካዊ ጉዳያቸውም ችግር ውስጥ ችግር ላይ መውደቁን» ለመግለጽም ነው ሲሉ አክለዋል ።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው አጭር መግለጫ ሞቅዲሾ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ  ኤምባሲ አማካሪ ሆነው የሚሠሩት አሊ ሞሐመድ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ የሚል እርምጃ ስለመወሰዱ ይጠቅሳል።

ኢትዮጵያዊዉ ዲፕሎማት በግልጽ ፈጽመውታል የተባለው ድርጊት ምን እንደሆነ ባይገለጽም ከዲፕሎማሲያዊ ሚናቸው ጋር በማይገናኝ ተግባር ውስጥ መሳተፋቸው ተጠቅሶ ይህም የ1961 ዱን የቪየና ስምምነት በተለይም ዲፕሎማቶች የተቀባይ ሀገራትን ሕግ ማክበርን ብሎም በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ የሚለውን ድንጋጌ በሚጥስ እንቅስቃሴ ውስጥ መገኘታቸው በምክንያትነት ተገልጿል።

የዲፕሎማትን እውቅና መሰረዝ (persona non grata) ምን ማለት ነው?

ለመሆኑ ተቀባይ ሀገራት የላኪ ሀገራትን በየደረጃው ያሉ የተልዕኮ ሠራተኞችን እውቅና መንፈግ እርምጃ - persona non grata ምን ማለት ነው? ከሥራቸው ጠባይ መነሻ ስማቸውን ትተው ማብራሪያውን የሰጡን አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ ተከታዩን ብለዋል።

"አምባሳደርን መላክ አለ። የእሱ ተቃራኒው አምባሳደርን ማባረር ይባላል። በዲፕሎማትነት አገርህን ወክለህ/ ወክለሽ ተቀብለንሀል/ ተቀብለንሻል የሚለውን ዕውቅና የመሰረዝ ተግባር ነው"

ምንም እንኳን ርምጃው አሉታዊ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ፣ የሕግ ድጋፍ ያለው የዲፕሎማሲ መሣሪያ ነው የሚባለው የዲፕሎማቶችን እውቅና የመሰረዝ እርምጃ የላኪ እና የተቀባይ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚወሰድ ነው? የሚለውንም ተንታኙ "ግንኙነት ከፍተኛ መሻከር ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

የሶማሊያ፤ የቱርክ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎችምስል colourbox

የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚወሰድ ነው?

"በሦስት ደረጃ ከፍለን ብናየው የመጀመርያው ዲፕሎማሲያዊ ተልእኮዉን የተቀበለው መንግሥት፣ አገር - አንድን ጉዳይ በተመለከተ ተወካዮቹን ጠርቶ እንዲያስረዱ፣ ገለፃ እንዲያደርጉ የሚጠይቅበት አግባብ ነው። ከዚህ ደረጃ ከፍ ሲል ደግሞ ወደ persona non grata - እውቅናን ወደ መሰረዝ ይኬዳል። ሦስተኛውና የመጨረሻው ዲፕሎማሲያዊ ግምኙነትን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ነው"

የፖለቲካ ቅሬታን መግለጫ የሆነውን ይህን መሰሉን እርምጃ ሀገራት የሚወስዱባቸው ምነሻ ምክንያቶች ምንድን ናቸው የሚለውም የግንኙነት ሁኔታን ጠቋሚም አመልካችም ነው።

እንደ ተንታኙ መረዳት አስቸጋሪው ነገር ይህን መሰሉ እርምጃ የሚወሰድበት ሰው ተመልሶ ወደ ተቀባዩ ሀገር የሚሄድበት ዕድል አለመኖሩ ነው። "በፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን በማይገባ መንገድ አከናዉነዋል ተብሎ በሚታመንበት ጊዜ አገራት የሚወስዱት እርምጃ ነው"

እየሻከረ ያለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት

መልካም ይባል የነበረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት  ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የባህር በር የሚያስገኝላት የተባለውን የመግባቢያ ስምምነት ከፈረመች ማግስት ጀምሮ ክፉኛ ሻክሯል፣ ውዝግብም ውስጥም አስገብቷቸዋል።

የሶማሊያ ደኅንነት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Farah Abdi Warsameh/AP/dpa/picture alliance

ይህንን ተከትሎ በአለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ ከቀጣዩ ጥር ጀምሮ አትሚስ የተባለውን የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ጥምር ጦር በሚተካው ኃይል ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች አይካተቱም የሚለው የሶማሊያ አቋም ውዝግቡን አባብሶታል።

ሰሞኑን ከዶቼ ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት በአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ የሶማሊላንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር አብዱላሂ ሞሐመድ ኢትዮጵያን ከሶማሊያ የበረታ ቅራኔ ውስጥ ያስገባት የባሕር በር የሚያስገኝ የተባለው የመግባቢያ ስምምነቱ በሂደት ላይ መሆኑን እና ያንን በተመለከተ በቅርቡ የሚሰማ ነገር ይኖራል ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም አልተሳካም።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW