“አንድ የደጋ አጋዘን በ15 ሺህ ዶላር እየታደነ ነው” የኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር አራዊት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 9 2017
አንድ የደጋ አጋዘን በ15 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲታደን ህግ ወጥቶ ለጎብኚዎች መቅረብ ከጀመረ 16 ዓመታት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኦሮሚያ ደንና የዱር እንስሳት የደን ልማትና የዱር እንስሳት አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አሸናፊ መንግስቱ የዱር እንስሳቱ ለቱሪስቶች ስሸጡ ግን የራሱ የሆነ አሰራር እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ “የደጋ አጋዘን ሌላ ቦታ የለም፤ በብዛት ያለው ኦሮሚያ ውስጥ በባሌ፣ አርሲ እና ሀራርጌ ተራሮች ነው፡፡ እንደ ኦሮሚያ በያመቱ ለአደን ሽያጭ የሚቀርበው የደጋ አጋዘን እስከ 20 ግድም ነው፡፡ ለአደን ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ 21 ቀን ብቻ ስለሚሰጥ አንዳንዴ ደግሞ ተሽጠውም እንግዶች ስቿኮሉ ሳይገደል የሚታለፍበት ጊዜ አለ፡፡ ከሽያጩ ከሚገኝ ገንዘብ 15 በመቶ ለፌዴራል መንግስት ገቢ በመሆን እንደ አገር የዱር እና እንስሳት ጥበቃ ስራ ስሰራበት ከቀሪው ደግሞ 60 በመቶው ለአከባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊ አገልግሎት 40 በመቶው ለኦሮሚያ ደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃ ገቢ ሆኖ ለፓርኮች እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ይውላል” ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ 250 የዱር እንስሳትን ለአደን ለማቅረብ ታቅዶ ነበር
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ብቻ ለቱሪስቶች አደን የደጋ አጋዘንን ጨምሮ በአጠቃላይም 250 የዱር አራዊት ለመሸጥ ታቅዶ 176 ያህሉ መሸጣቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ 147 ያህሉ መገደላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህም በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ከዱር እንስሳቱ አደን በኦሮሚያ ክልል የ75 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱ ነው የተገለጸው፡፡ ይሁንና ከዱር እንስሳቱ አደን ከሚገኘው የቱሪስቶች ገቢ ባሻገር በዱር እንስሳቱ ጥበቃ ላይ ልደርስ የሚችለውን አሉታዊ ጉዳት እንዴት መቋቋም ይቻላል በሚል የተጠየቁት አቶ አሸናፊ፤ “የምንሰራው በሳይንሳዊ ስልት በመሆኑ ተጽእኖ የለውም፡፡ ለምሳሌ አጋዘን ስንለይ መጀመሪያ ምንያህል እንዳለን እንቆጥራለን፡፡
ከዚያን በዚህ ዓመት በብዛት ምን ያህሉን ለአደን ማቅረብ አለብን የሚለው በዱር እንስሳት ባለስልጣን ተወስኖ ነው ወደ ስራ የሚገባው፡፡ ሌላው የዱር እንስሳትጥበቃው ላይ ተጽእኖ የለውም ስንል በጣም ያረጁና ወደ ተፈጥሮአዊ ሞት እየሄዱ ያሉትን ብቻ ነው ለአደን የምናቀርበው፡፡ ለምሳሌ የቆላ አጋዘን ቀንዱ ከ42 ኢንች በላይ እና የደጋ አጋዘን ቀንዱ ከ29.5 ኢንች በላይ ከሆነ ብቻ ነው ለአደን የሚሸጡ፡፡ ከዚህ በታች ያለውን ቱሪስቶቹ በአደኑ ከገደሉ ከከፈሉት ገንዘብ በእጥፍ ነው የሚቀጡት” ብለዋል፡፡ የደጋ አጋዘን አሁን ላይ ለቱሪዝም አደን የሚሸጥበት 15 ሺህ ዶላር፤ ከ16 ዓመታት በፊት በ2001 መተመኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ አሁን ላይ በዚህ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የአገሪቱ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሀሳቡን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ስያጸድቅ ነውም ብለዋል፡፡
የባለሙያ አስተያየት.
አቶ ጨመረ ዘውዴ ለሶስት አስርት ዓመታት ግድም በዱስ እንስሳት ጥበቃ ዙሪያ የሰሩ ባለሙያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለስፖርታዊ አደን የዱር እንስሳትን ለዓመታት ስታቀርብ መቆየቷንና አሁንም እያቀረበች መሆኑን በማስረዳት፤ ለዓለም በብቸኝነት ደግሞ ሶስት የዱር እንስሳት አይነቶችን ለአደን ገቢያ የሚቀርቡ የደጋ አጋዘን፣ የጭላዳ ዝንጀሮ እና የሚኒሊክ ድኩላ ናቸው ብለዋል፡፡ “እነዚህ ሶስቱ ለኢትዮጵያ ስፖርታዊ አደን ቅመም ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው” ያሉን ባለሙያው አብዛኛው ለአደን ወደ ኢትጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች እነዚህን ሶስቱን ፍላጎት በማድረግ እንደ ሆነም ገልጸዋል፡፡ ብርቅዬ የዱስ እንስሳ የሆነው የደጋ አጋዘን ከፍተኛውን ገቢ በዚህ ረገድ ስያስገባ እንደቆየም የገለጹት የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያው አቶ ጨመረ ዘውዴ ኢትዮጵያ የዱር እንስሳቱን ለአደን ገቢያ የምታቀርበው በዓለማቀፍ ስምምነቶች እና በአገሪቱ የዱር እንስሳት ፖሊሲዋ መሰረትም እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ