1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መምህርና አስጠኚ በቦን

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11 2015

አቶ አብዱልቃድር በሂሳብ መምህርነትና በአስጠኚነት ተማሪዎችን ለጥሩ ውጤት በማብቃት የስራቸውን ፍሬ ለማየት በቅተዋል። እዚህ ቦን በሂሳብ ውጤቱ ማነስ ምክንያት ወደ ዘጠነኛ ክፍል ማለፍ ያቀተውን ተማሪ ለአንድ ወር አስጠንተው ማለፍ መቻሉን ከጊዜ በኋላም በሁሉም ትምህርቶች ጥሩ ውጤት እያመጣ በምህንድስና ተመርቆ ጥሩ ስራ ለመያዝ መብቃቱን ያነሳሉ።

Abdurkadir Tura
ምስል Privat

አንጋፋው መምህር በቦን

This browser does not support the audio element.

አቶ አብዱልቃድር ቱራ ይባላሉ። ትውልድና እደገታቸው ከአርሲ ነገሌ (ነገሌ አርሲ )17 ኪሜ ርቃ በምትገኝ ሌጲስ በምትባል መንደር ነው።እዚያ በሚገኝ የካቶሊክ ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ሻሻመኔ ተከታትለው ጥሩ ውጤት በማግኘታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገቡ። ከልጅነታቸው አንስቶ ከትምህርት ሁሉ አስበልጠው በሚወዱት በሂሳብ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ እንደተመረቁ ባሌ በመምህርነት ተመድቡ። አቶ አብዱልቃድር ፣ባሌ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም እንዲሁም በሙያ ማሰልጠኛ ወይም በቴክኒክ ትምሕርት ቤት በሂሳብና በፊዚክስ መምህርነት እና በርዕሰ መምህርነት  ለ13 ዓመታት ሰርተዋል። ሂሳብን ከልጅነት አንስቶ በፍቅር የተማሩት አብዱልቃድር የከፍተኛ ትምህርት ምርጫቸውም አደረጉት።ከዛሬ 18 ዓመት በፊት ከባሌ በቀጥታ በመጡባት በቦን ጀርመንም በሚወዱትና ብዙ ልምድ ባካበቱበት በዚህ ሞያ የመስራት እድል ያገኙት መምህር አብዱልቃድር እንደተናገሩት ይህ የተሳካላቸው ያለውጣ ውረድ አልነበረም። ቦን ከመጡ በኋላ ከፈተኗቸውጉዳዮች ውስጥ ሁለቱን ከባድ ብለዋቸዋል።  

የመምህር አብዱርቃድር የሂሳብ ባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ በጀርመን እውቅና ካገኘ በኋላ ለግል ትምህርት ቤቶች ማመልከት ጀመሩ ። ተሳክቶላቸውም በግል ትምሕርት ማስተማር ቀጠሉ ።እያስተማሩ እንደከዚህ ቀደሙ ተማሪዎችን ሂሳብ ፊዚክስ እና ስታትስክስ ማስጠናቱንም ጎን ለጎን ማካሄዱን ገፉበት። ከዚህ ቀደም ከሀገራቸው ወጥቶ የመስራትም ሆነ የመኖር ሀሳብ ያልነበራቸው አቶ አብዱልቃድር በተሰደዱባት በጀርመን ለ4 ዓመታት ተማሪዎችን በማስጠናት፤ ከዛሬ ለ12 ዓመት ወዲህ ደግሞ በግል ትምሕርት ቤት በማስተማር እና ተማሪዎችን በማስጠናት ላይ ይገኛሉ። መጀመሪያ ላይ ትምህርት ቤት ውስጥ ተግዳሮቶች ገጥመዋቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ ቋንቋ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት የትምህርት ስርዓቱንም በደንብ መረዳት በጀርመን በአስተማሪነት ለማገልገል ወሳኝ ነው ። ያም ሆኖ በሚያስተምሩበት የግል ትምሕርት ቤት የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪቃዊ መምህር የነበሩት አብዱልቃድር በተማሪዎቻቸው ሳይቀር ይፈተኑም እንደነበር ተናግረዋል።
ጀርመንንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ሀገራት ሂሳብ የሚከብዳቸው ውይም ትምህርቱን የማይወዱት ተማሪዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። መምህር አብዱልቃድር ተማሪዎች ሂሳብን እንዲወዱ ትምህርቱም እንዲቀላቸው የማስተማር ዘዴውን ሳቢ ማድረግ ጠቃሚ ነው ይላሉ። በዚህ ዘዴ በኢትዮጵያም ሆነ በጀርመን  በርካታ ተማሪዎች ለትምህርቱ ያላቸው አመለካከት እንዲቀየር ውጤታቸውም እንዲሻሻል ማድረግ ችያለሁ ብለዋል። በጀርመንና በኢትዮጵያ የሂሳብ ትምህርት አሰጣጥ መሠረታዊ ልዩነት አለውም ይላሉ ልዩነት እንዳለውም ያስረዳሉ።
አቶ አብዱልቃድር በውጭ ዓለምም በተሰማሩበት በሂሳብ መምህርነትና በአስጠኚነት ተማሪዎችን ለጥሩ ውጤት በማብቃት የስራቸውን ፍሬ ለማየት በቅተዋል። ከመካከላቸው በሂሳብ ውጤቱ ማነስ ምክንያት ወደ ዘጠነኛ ክፍል ማለፍ ያቀተውን ተማሪ ለአንድ ወር ካስጠኑ በኋላ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ማለፍ መቻሉን ፤ በዚህ ተበራትቶም  ከጊዜ ወደ ጊዜ በሁሉም ትምህርቶች ጥሩ ውጤት እያመጣ በምህንድስና ተመርቆ ጥሩ ስራ ለመያዝ መብቃቱን እንደ አንድ ምሳሌ አንስተዋል። አቶ አብዱልቃድር ኢትዮጵያ ቢቆዩ ኖሮ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው ትምህርት ቤት የመክፈት ሀሳብ ነበራቸው። ያ ምኞት አሁንም በልባቸው እንደተጻፈ ነው።ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት መምህር አብዱልቃድርወደፊት በሀገራቸው የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ከጀርመን የትምህርት ስርዓት ጋር አቀናጀቶ ለማሻሻል ይመኛሉ፤ የግል ትምህርት ቤት መክፈት ወይም ከሌሎች የግል ትምህርት ቤት ካላቸው ጋር የመስራትም ፍላጎት አላቸው።   

ምስል Privat

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW