1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አንጋፋው ሙዚቀኛ አሊ ብራ ሲታወስ

ሐሙስ፣ ኅዳር 1 2015

ክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ብራ ለ60 ዓመታት በዘለቀው የሙዚቃ ህይወቱ ስለነጻነት፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ ስለፍቅር፣ ስለተፈጥሮ እና ስለአገር በርካቶች በሚወዱት አንጸባራቂ ድምጹ አቀንቅንል፡፡ ባአሊ ብራ፤ አቀላጥፎ መናገር በሚችለው ስድስት ቋንቋዎች 267 ሙዚቃዎችን የተጫወተ ብሔራዊ ጀግና ነዉ፡፡

Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ምስል፦ Odaa Award

አሊ ቢራ ስለነጻነት፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ ስለፍቅር፣ ስለተፈጥሮ እና ስለአገር አቀንቅኗል።

This browser does not support the audio element.

የክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ብራ ለ60 ዓመታት በዘለቀው የሙዚቃ ህይወቱ ስለነጻነት፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ ስለፍቅር፣ ስለተፈጥሮ እና ስለአገር በርካቶች በሚወዱት አንጸባራቂ ድምጹ አቀንቅንል፡፡ ባለፈው እሁድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም አመሻሽ ህይወቱ አልፎ ከትናንት በስቲያ በትውልድ ስፍራው ዲሬዳዋ የተቀበረው አሊ ብራ፤ አቀላጥፎ መናገር በሚችለው ስድስት ቋንቋዎች 267 ሙዚቃዎችን የተጫወተ ብሔራዊ ጀግና ለመሰኘትም በቅቷል፡፡
የተለያዩ ማንነት- ባህልና እሴትን የምታቅፍ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ከምንም በላይ የሚዋደድና የሚከባበርባት ዲሬዳዋ መነሻው ናት፡፡ በ 1940 ዓ.ም በከተማዋ ገንደ ቆሬ ከአባቱ አቶ መሓመድ ሙሳ እና ከእናቱ ወ/ሮ ፋጡማ አሊ ተወልዶ 75 ዓመታትን በህይወት ሲቆይ 60 ዓመታቱ ከሙዚቃ ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ 
አሊ መሐመድ ሙሳ የልጅነት መጠራው ነው፡፡ የቅርብ ወዳጆቹ ደግሞ አዴሮ ይሉታል፡፡ ከቁራን እስከ መደበኛ ትምህርቱ በትውልድ ከተማው ዲሬዳዋ እና በኋላም በአዲስ አበባ የተከታተለው አሊ በውጪም በተለያዩ አገራት የሙዚቃ ትምህርትን እንደቀሰመ የግል ታሪክ ድርሳኑ ያወሳል፡፡
አባቱ ተምሮ መካኒክ እንዲሆንለት ያሻው የያኔው ታናሹ አሊ ገና በ14 ዓመቱ ነበር የህይወት ጥሪው ወደ ሆነው የሙዚቃ ሙያ ጎራ ያለው፡፡ የኦሮሞ ባህልና ኪነ-ጥበብን ለማበልጸግ በ1954 ዓ.ም. በዲሬዳዋ የተቋቋመው የአፍራን ቀሎ የኪነት ቡድን ደግሞ አሊን ወደ አባቱ ምኞት ሳይሆን ወደ የሙዚቃ ዓለም ለማስኮብለል ዋናው ምክኒያት ነበር፡፡ “የቢራ ወቅት መጣ የአበባው መዓዛ አወደ” የሚል ጥሬ ትርጉም ያለው “ቢራን በርሄ ኢሊሊን ኡርጎፍቴ” ሲል ያቀነቀነው ደግሞ የመጀመሪያው ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀው ስራው ነበርና አሊ ብራ የሚል የእውቅና ስሙም ከዚሁ ጀመረ፡፡ በኦሮሞ እና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ታላቅ ነገርን የሚሰራ ታዳጊ ለመሆንም በዚሁ ገና በ14 ዓመቱ ፍንጭ አስያዘ፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርቲስት መሃመድ ቆጴ አሊ ቢራን የጓደኘውና አብሮአደጉ ያህል በቅርበት ያውቀዋል፡፡ መሃመድ ቆጴ ስለ አሊ ሲናገር በእርግጥ “አሊ በእድሜ ብዜ የሚበልጠኝ ታላቄ ነው” ይላል፡፡ አሊ በዴሬዳዋው አፍራን ቀሎ ከታዳጊዎች እስከ አዋቂዎች ካገለገለና ብዙ ውጣውረዶችን ካሳለፈ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የክቡር ዘበኛ ባንድ አባልም ለመሆን መብቃቱን ያወሳልም፡፡ የአሊ ቢራ እና የአሊ ሸቦ የሙዚቃ አስተዋፅዖ
“አንደራሱ ቋንቋ አቀላጥፎ ከሚችላቸው ሰባት ቋንቋዎች በስድስቱ ሙዚቃን የተጫወተው አሊ በተለይም የአፋን ኦሮሞን ሙዚቃ ተወዳጅ በማድረግ የማይሻር ሚና ተወቷል” ሲልም በማያወላዳ ቃል አሞካሽቶታል፡፡
በተፈጥሮ ድምጽ የታደለው አንጋፋው አሊ የበርካታ ሙዚቃ መሳሪያዎች ተጫዋች እንደሆነም አሊን በቅርበት የሚያውቀው መሃመድ ቆጴ ያወሳል፡፡ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኦርጋን፣ አኮርዲዮ እና ኡድ ድግሞ አሊ እንዳሸው መጫወት ከሚችላቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የክቡር ዶ/ር ሙዚቀኛ አሊ ቢራ ስለ አንድነት ካቀነቀናጨው ሙዚቃዎቹ “Rabbimoo Namumaa” “ፈጣሪ ነው ወይ ሰው ህጉን ያጋደለው፤ እናታችን አንድ ሆና ምንድነው የለያየን?” ሲል የሚያጠይቀው ሙዚቃው ጉልበታምና በርካቶች ከወደዱለት ሙዚቃ ነው፡፡ 
አሊ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃን መሰረት የጣለ ይባልለታልም፡፡ በዲሬዳዋ የሙዚቃ ህይወቱ በተለያዩ አከባቢዎች ከጓደኞቹ ጋር ተዘዋውሮ የሰራው አሊ፤ ባንድ ወቅት ወደ ጂቡቲ ሄዶ ሙዚቃን ተጫውቶ ሲመለስ ግን ፈተና ይገጥመዋል፡፡ ከጓዶቹ ጋር ለእስራት በቅቶ በኋላም የአፍረን ቀሎ ባንድ መፍረሱ አሊን ወደ አዲስ አበባ ያመጣው ሲሆን፤ እንደ እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ እና አንጋፋ ሙዚቀኛ መሓሙድ አህመድ ጋር ወዳስተዋወቀው የክቡር ዘበኛ ባንድ ለመቀላቀልም ቻለ፡፡ 
የዘመናት ጓደኛው አንጋፋው ሙዚቀኛ መሓሙድ አህመድ አሊን ከሙዚቃ ችሎታው ባሻገር ስለስብዕናውም መግለጽ ከባድ ነው ይላል፡፡ 
ለአሊ አሁንም ነገሮች አልጋ በአልጋ የሆኑለት አይመስልም፡፡ በክብር ዘበኛ ባንድ ውስጥ ያጋጠሙት ለሱ ያልተስማሙት ነገሮች ባንድ ወቅት እራሱን ከሙዚቃ እስከማግለል ውሳኔ እንዲያሳልፍ ማብቃቱም በግለ ታሪኩ ተከትቧል፡፡ በዚሁ መሃልም ወደ አዋሽ በመሄድ የምድር ባቡድ የውሃ መካኒክ ሆኖ ማገልገል ይጀምራል፡፡ የህይወት ጥሪው ሙዚቃ ግን አሁንም ልትለቀው ከቶውንም አልተቻለውም፡፡ 
አሊ እስከ ህይወት ፍጻሜው በ60 ዓመታት ገደማ የሙዚቃ ህይወቱ 267 ሙዚቃዎችንም በ6 ቋንቋዎች ማለትም በአፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣ ሱዳንኛ፣ አረብኛ እና የስዊድን ቋንቋዎችን አሳምሮ ተጫውቷል፡፡ በዚህም ስለ እርቅ፣ መተሳሰብ፣ ትምህርት እና ሌሎችም በጎ ስለሆኑ ነገሮች ሰብኳል፡፡ 
ሙሉ ህይወቱን ለህዝብ የኖረ የሚባልለት አሊ ከአብራኩ ያገኘው ልጅ ባይኖረውም ህዝቤን በሙሉ እንደልጆቼ ነው የማየው ሲል በአንድ ቃለምልልስ ተናግሮ ነበርም፡፡ እስከ ህይወት ፍጻሜው አብራው የቆመች፡ በተግባር በታየው ፍቅርም በርካቶችን ያስደመመች ፊሊፒናዊ ባለቤቱ ሊሊ ማርቆስ (ወይም ኢሊሊ ቢራ) ደግሞ ሁለተኛ ባለቤቱና እስከመጨረሻው አብራው በፍቅር የፀናች ናት፡፡የዓሊ ቢራ ሽኝትና ቀብር
ጋዜጠኛና አርቲስት መሓመድ ቆጴ እንደሚለው አሊ የድንቅ ስብዕና እና ችሎታ ባለቤት ነው፡፡ ውጣ ውረድን ባሳለፈባት ዓለምም በተለያዩ አገራት ህይወትን ገፍቶ በመጦራ ዘመኑ ወደ አገር ተመልሶ ለትልቅ ክብርም በቅቷል፡፡ 
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ፕሬዝዳንት የክቡር ዶ/ር ዳዊት ይፍሩ አርቲስት አሊ ብራን ስራዎቹ እንዳይሞቱ አድርጎ የሰቀለ ድንቅ ሙዚቀኛ ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡ አሊ ቢራ ሙዚቃን ከሚዘፍንበት ቋንቋ አሻግሮ አቅም የሰጠው ስለመሆኑም ይመሰክራሉ፡፡ 
የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት ደግሞ አሊ ብራን ባለ ምጡቅ አዕምሮ የድንቅ ድምጽ ባለበት ሲል ነው የገለጸው፡፡ ባለሙያው አሊ ብራ ከሚዘፍንበት ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሻገር ማንንም በአድናቆት ያሰለፈ የሙዚቃን ምስጥር ከመሰረቱ የተረዳ ባለሙያ ነው ብሎታልም፡፡ አሊ በክህሎት ላይ እውቀትን ጨምሮ ሙዚቃን የሚጫወት፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችንም እንዳሸው የሚያነጋግር ምልዑ የሆነ ሙዚቀኛ ብሎታልም፡፡ 
ከአሊ ጋር ሙዚቃን ለመጫወትና በቅርበት የአብሮ መስራት እድል ካገኙ ድምጻውያን ደገሞ ድምጻዊት ሄለን በርሔ እና ድምጻሚ አቡሽ ዘለቀ ይገኛሉ፡፡ ሙዚቀኞቹም አሊን ታላቅ የሙዚቃ አባት ሲሉ ይገልጹታል፡፡ 
ለ6 አስርት ኣመታት ሙዚቃን በመጫወት ታላቅ እውቅናን ያተረፈው አሊ ብራ ለስራዎቹ ከ ጂማ እና ዲሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክቴሬት አግኝተዋል፡፡ 
አሊ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ግን በተለያዩ ህመሞች ሲሰቃይ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኛ እና አርቲስት መሓመድ ቆጴ የአሊን ሁኔታ በቅርበት ከሚከታተሉት ግለሰቦች ነው፡፡ “በስኳር ህመም መነሻ ያጋጠመው የካንሰር፣ የሁለቱም ኩላሊቶች ስራ ማቆም እና በመጨረሻም አንድ እግሩ እንዲቆረጥ ያደረገው ህክምና ውስብስብ እንደነበርም” አብራርቷል፡፡
የአሊ የቅርብ ጓደኛው ሙዚቀኛ መሓሙድ አህመድም ይህንነን ሲያስረዳ፤ “አንዱን እግሩን ሲያጣ እምባየን መቆጣጠር አቃተኝ፤ ለኔ ሁለት የልብ ጓደኞቼን በዚህ መንገድ ማጣት ህምም ነው” ብሏል፡፡
በ75 ዓመቱ እሁድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ህይወቱ ያለፈው አሊ ቢራ በብሔራዊ ደረጃ በተሰናዳ የአስከሬን ሽኝት እና የቀብር ስርዓት ተሰናብቷል፡፡ አዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ በተሰናዳው የሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም፡ አሊ ቢራ በሙያው ለአገሩ ታላቅ ነገርን ያደረገ ሲሉ አወደሱት፡፡ አቶ ሽመልስ “አርቲስቱን እራሱ ኢትዮጵያ ነው” ሲሉም ገልጸውታል፡፡ 
ከዲሬዳዋ በመነሳትም በርካታ ውጣውረዶችን በማለፍ ከስውዲን-ሳውድ አረቢያ፣ ከአሜሪካ እና ካናዳ እስከ ተለያዩ አገራትም ተዘዋውሮ ኑሮ በመግፋት በመጨረሻም በአገሩ ለበክብር ሽኝት የበቃው አሊ፤ ማክሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም መነሻው በመሆነችው ዲሬዳዋ፤ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የቀብር ስፍራ በሆነው ለገሃሬ ቀብሩ ተፈፀመ፡፡ 
የሙዚቃው ባለሙያ ሰርፀ ፍሬስብሃት የከበረ ስም ላኖረው አርቲስቱ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በስሙ ከመክፈት ጀምሮ ብዙ መታሰቢያዎች ማድረግን ይሻል ብሏል፡፡ 
የአሊ ወዳጆችና የሙያ አጋሮቹም በዘመን የማይገደብ ስራን ያኖረው አሊ በስራዎቹ መታወሱ ግድ ብልም፤ ለመማሪያና ክብርም ይሆን ዘንድ ስራዎቹ በሙዚየም ጭምር ቢቀመጡ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ምስል፦ Odaa Award
ምስል፦ Odaa Award
ምስል፦ Odaa Award
ምስል፦ Odaa Award


ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW