1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጋፋው ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ሲታወስ

ሰኞ፣ ሐምሌ 25 2014

የአንጋፋው የዶይቸ ቬለ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ባልደረባ የተክሌ የኋላ ዜና ዕረፍት ከተሰማ ወዲህ በርካታ አድማጮቻችን በማህበራዊ መገናኛ ገፃችን ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው። ተክሌ እንዴት ይታወሳል? የስራ ባልደረቦቹን እና ጓደኛው ተክሌን ሀገር ወዳድ፤ ትግስተኛ፣ ትሁት ነበር ሲሉ ይገልፁታል።

Äthiopien Tekle Yewhala
ምስል Shewaye Legesse/DW

This browser does not support the audio element.

የአንጋፋው የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ድምፅ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ከዶይቸ ቬለ የአማርኛው ስርጭት ርቆ ቆይቷል። ቅዳሜ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ተክሌ ከሰኔ 2007 ዓም አንስቶ በጡረታ ላይ ነበር። የዶይቸ ቬለ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ምክትል ኃላፊ እና ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ፣ ከተክሌ የኋላ ጋር ለብዙ ዓመታት አብረው ከሰሩ ባልደረቦች አንዱ ነው።ለ 25 ዓመታት ያህል  ያውቀዋል። « በዚህ የረዥም ጊዜ ካየኃቸው ጋዜጠኖች ተክሌን ለየት የሚያደርገው ወይም የሚሻልበት ነገር ረዥም ጊዜ ወስዶ ያደምጣል። ጥሩ አድማጭ እና ታጋሽ ነበር። በየጊዜው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ቢያነሳ አይጠግብም። ሀገር ወዳድ ነበር» ሲል ነጋሽ ይገልፀዋል።

የዶይቸ ቬለ የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ ኢትዮጵያ እያለ ተክሌን  በዝና ብቻ ነበር የሚያውቀው።  ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁበትን ዕለት ሳይቀር ያስታውሳል። « ኢትዮጵያ ውስጥ የድሮው ብስራተ መንጌል ይሰራበት በነበረበት ጊዜ የሚያዘጋጃቸውን ዝግጅቶች እከታተል ነበር። ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄጄ በዩንቨርስቲ በኩል ለስራ ልምምድ ወደ ዶይቸ ቬለ በላኩኝ ጊዜ ነው ከተክሌ ጋር የተገናኘነው።  እጎአ ሐምሌ 3 ቀን 1978 ዓ ም ነው» ይላል ድልነሳ።
ተክሌን ጨምሮ በርካታ ዛሬ በህይወት የሌሉ የአማርኛው ክፍል ባልደረቦች ጭምር  በጥሩ ሁኔታ እንደተቀበሉት እና ሊሰለጥን ከመጣበት የእንግሊዘኛ ክፍል ወደ የአማርኛው ክፍል እንዲዛወር እንዳደረጉ ድልነሳ ይናገራል። « ከዛ ጓደኝነታችን ጠነከረ። ከጓደኝነትም አልፎ እኔ ትዳር ስይዝ ሚዜዬ ነበር። እሱም ልጆች ሲወልድ እኔ እና ቤተሰቤ ነን ክርስትና ያነሳናቸው።» ይላል ድልነሳ።
አቶ ተስፋዬ አፅብኃ ተክሌ ለብዙ አመታት በኖረባት እና በሰራባት የምዕራብ ጀርመንዋ የኮሎኝ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከተክሌ ጋር የረዥም አመታት ትውውቅ አላቸው። የተክሌን ባህሪ እና ማህበራዊ ህይወቱን በተመለከተ ሲናገሩ« በጣም ትሁት ነው። ማንንም ሰው አያስቀይምም። ከሁሉም ሰው ጋር ተስማምቶ ይኖር የነበረ ሰው ነው።» ይላሉ። ተክሌ የጡረታ ጊዜውን በሚገባ ተጠቅሞበታል የሚሉት አቶ ተስፋዬ ተክሌ በዚህ አጭር አመታት « መፅሀፍ መደ መፃፍ ገባ፣ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይንቀሳቀስ ነበር። የጡረታ ጊዜውን ለስራ ተጠቅሞበታል» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
ከዚህም ሌላ ተክሌ ለአማርኛ ቋንቋ ጥራት እና አጻጻፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበር አብረው የሰሩ ባልደረቦቹ ይመሰክራሉ። 
ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ72 ዓመቱ ባለፈው ቅዳሜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበር።

ተክሌ የኋላ እጎአ 2005ምስል DW

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW