«አከራካሪ» የተባሉ አካባቢዎች ችግር በሰላም እንዲፈታ ስለመጠየቁ
ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2017
የአማራ ብሔራዊ ክልልና የፌደራል መንግሥት ከፈተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን በአማራና በትግራይ ክልሎች «አከራካሪ» ብሎ ከሚባሉ አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው በሁመራ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ያሉ ጥያቄዎች በሰላምና በውይይት ሊፈቱ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህን ለማድረግ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉን ማድረግ አለበትም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፣
“... በግጭት፣ በብረት የሚመጣ ሠላም የለም፣ ገጭትና ጦርነትም የሕዝቦችን ትስስርና ሰላም በዘላቂነት ያመጣል ብለን አንገምትም፣ የትግራይ ሕዝብም በድጋሚ ወደ ጦርነት መግባት የለበትም፣ ዘላቂ ሰላም የሚያስገኘው ሕጋዊና ሰላማዊ አማራጭ መሆኑን እንዲገነዘብ እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡
«በወልቃይት የማንነት ጥያቄዎች አሉ» አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድርና በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በአካባቢው የማንነት ጥያቄ መኖሩን አረጋግጠው ጉዳዩ ግን በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ነው ያስረዱት። የትግራይ ወጣትም የሚፈልገው ሰላም መሆኑን አመልክተዋል። የዛሬው ውይይትም «በር ከፋች» እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
«ለእውነተኛ ውይይት ዝግጁ ነን» አቶ አሽተ ደምለው፣ የወልቃይት ጠግዴ ሰቲት ሁመራ ዋና አስተዳዳሪ
በአሁኑ ወቅትየወልቃይት ጠገዴ ሠቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው በስልክ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ተጭማሪ አስተያይት «ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ ለሠላማዊ ውይይትና ንግግር በራችን ክፍት ነው» ነው ያሉት፡፡ ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በአካባቢው የማንነትና የወሰን ጥያቄ እንጂ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሌለ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል ሲሉ ነው የገለፁት፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አማኑኤል አሰፋ ሰሞኑን በመቐለ በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ እንዳሉት ሁሉንም ዓይነት ሰላማዊ መንገዶች እንደሚጠቀሙ፣ «ያ ካልተሳካ ግን የትግራይ ሉዓላዊነት ተደፍሮ ይቀራል ማለት አይደልም» ብለዋል፡፡
«የትግራይ ክብርና ሉዓላዊነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንሰራልን» አቶ አማኑኤል አስፋ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
« የትግራይን ብሔራዊ ጥቅሞች በሰላማዊ መንገድ ለማረጋገጥ ሁሉም ዓይነት ጥረት ይደረጋል ስንል በሰላማዊ መንገድ ካልተፈታ የትግራይ ክብርና ሉዓላዊነት ተደፍሮና ተወርሮ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል» ነው ያሉት፡፡
የወልቃይት ጠቀዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ በበኩላቸው“የጦርንት ፉከራ” ያሉትን እንደማይቀበሉ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
«ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ የመውረርና የጦርነት ፉከራ ይዞ በሰላማዊ ሠልፍ እየወጡ ጦርነት ለማወጅ፣ ወደ ወልቃይት ለመግባት ያለው ፉከራ ግን ተገቢም ትክክልም አይደለም ብለን እናምናለን» ብለዋል፡፡
«ለማንነትና የወሰን ጥያቄዎች እውቅና ይሰጠን» የሁመራ ከተማ ነዋሪ
አንድ በውይይቱ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪ በስልክ እንደነገሩን፣ «ለማንነትና የወሰን ጥያቄዎች እውቅና ይሰጠን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ይደረግ፣ ወንጀል የሰሩ በሕግ ይጠየቁ» የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት ተነስተዋል።፡ ተፈናቃዮች በሚመለሱበት ሁኔታም ውይይት የተደረገ እንደሆነና በዚህ ዙሪያ ቀጣይ ውይይቶች እንደሚደረጉም ስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
የወልቃይት ነባር ነዋሪዎች በመላው ዓለም በስደት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ እኚህም ወደ ቀደመ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉ ተወያዮቹ መጠየቃቸውን አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።
በቅርቡ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ፥ መንግሥት የትግራይ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንና በጉዳዩ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋርም ንግግር እየተደረገ ስለመሆኑ መናገራቸው ይታወሳል።
ዓለምነው መኮንን
ሽዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር