አካላዊ ጥቃት የሚደርስባቸዉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ
ሰኞ፣ ሰኔ 16 2017
አካላዊ ጥቃት የሚደርስባቸዉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ
ከገጠር ወደ ከተማ በቤት ሰራተኝነት ስራ ለመቀጠር የሚሄዱ ሴቶች ለአካላዊና ፆታዊ ጥቃት እየተዳረጉ ነዉ ተባለ በተለይም አስገድዶ መደፈርና በእሳት የአካል ጉዳት በቀጣሪዎቻቸዉ ይፈፀምባቸዋ በደሴ ከተማም ከ90 በላይ ጥቃቶች ተመዝግበዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ አካላዊና ፆታዊ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረየመጣበት ደሴ ከተማ በተለይም መነሻቸውን ገጠር አድርገው በከተማ የቤት ሰራተኛ ሆነው በሚቀጠሩ ሴቶች ጉዳቱ ከባድ ሆኗል፡፡ ሰይድ አሊ በደሴ ከተማ ከገጠር የሚጡ ሴቶች በቤት ሰራተኛ ስራ በማስቀጠር የድለላ ስራ የተሰማራ ወጣት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ ከገጠር አምጥቶ ሰው ቤት ሰራተኛ አድርጎ ያስቀጠራት ሴት በአሰሪዎቿ በተፈፀመባት አካላዊ ጥቃት የተነሳ ሀገሩ መግቢያ እንዳጣ ይናገራል፡፡
‹‹ሔጄ ስጠይቃት አሁን ልብስ ልታጥብ ወጥታለች አለች፡፡ እሷ ግን እያሰቃየቻት ነበር፡፡ በጣም ነው የሚያሳዝነው ነገር ግን እኔ ሀገሬ መሄጃ ቤተሰብ መጠየቂያ አጣሁኝ ሀገራቸው ላይ ይህ ከደረሰ ምን ህግ አለ ይባላል፡፡››
አስገድዶ መደፈር፣አካላዊ ጥቃትና ደመወዝ መቀማት
በአካላዊ ጥቃት መጎዳት አስገድዶ መደፈር እና የሰሩበትን ገንዘብ በአግባቡ አለመከፈል በሀገር ውስጥ ሰራተኞች ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው ይላሉ፡፡ በአሰሪና ሰራተኛን በማገናኘት ስራ ላይ የተሰማሩት አስተያየት ሰጭ ‹‹ጉዳት የሚደርስባቸው የመደፈር ደመወዝ የመቀማት የስራ ጫናም ይበዛባቸዋል፡፡ አሁን እንደ አዲስ ደግሞ በእሳት መቃጠል መጥቷል፡፡ ይህን የምናየው በውጭ ሀገራት ነበር ከዚህ ቀደም›› ፍትህ ለጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች
ጥቃቶቹ የሚፈፀሙበት መንገድ የረቀቀ መሆን
ከዚህ በፊት በሴቶች ላይ ይደርሱ ከበነሩ ጥቃቶች ይልቅ አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉት አካላዊና ፆታዊ ጥቃቶች ውስብስብ ሆነዋል፡፤ የሚሉት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማቆያ ማዕከል ሰራተኛ የሆኑት ወ/ሮ ሀብታም ታመነ ናቸው፡፡ ‹‹ከአሁን በፊት ከነበረው አሁን ላይ የሚፈሙት ትንሽ ውስብስብ ያሉ ናቸው፡፡ በአይነታቸውም ለየት እያሉ እየመጡ ነው፡፡ ከባድ ነው ህግ ባለበት ሀገር›› አሁን ላይ አካላዊም ይሁን ፆታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ወደ ህግ ከሚመጡ ሰዎች ይልቅ በመረጃ እጦትም ይሁን ባለማወቅ በቤት ውስጥ የቀሩ እንዳሉ በደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ግንዛቤ እና ንቅናቄ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታሁን ዓለም ይናገራሉ፡፡
‹‹አገልግሎቱ የሚሰጥተበትን ተቋም አውቀው መረጃ ደርሷቸው የመጡትን እንዳሉ ሌሎች ደግሞ ይህ መረጃ ሳይኖራቸው ከገጠር መጥተው የት መሄድ እንዳለባቸው ፣ የት አገልግሎት እንደሚሰጥ፤ ለማን መናገር እንዳለባቸው የማያውቁ ብዙ አካላዊ ጥቃትን፣ ወሲባዊ ጥቃትን ሌሎች ጥቃቶችም ደርሰውባቸው አፍነው ቁጭ ያሉ አሉ፡፡›› በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በተለይም በቤት ሰራተኝነት ላይ የተሰማሩት ተገደው የመደፈር፣ የመደብደብ እና ለሌሎች አካላዊ ጉዳት የሚዳርጉ ተግባራት ይፈፀምባቸዋል፡፡ የሚሉት የደሴ ከተማ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ ወ/ሮ ምሳየ ከድር ናቸው፡፡ በመቐለ ፆታዊ ጥቃቶችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ
‹‹ሠራተኛ አምጥቶ ሃላፊነት ወስዶ ሊያሰራ በአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት መሰረት የሚደፈሩ ሴቶች አሉ፤ በአሰሪዎቻቸው የሚደበደቡ፣ የሚቃጠሉ ህፃናት በአባቶቻቸው ይቃጠላሉ፣ በአካባቢያቸው ሰው የሚደፈሩም አሊ፡፡ ቤት ውስጥ ባለ አካል እና በጎረቤት ጥቃቱ ከቅርብ ጭምር ነው፡፡ ሁሉም እየተሰማው መምጣት አለበት፡፡ ››
የጥቃት መጨመር
አሁን ላይ ጥቃቶቹ ከተፈፀሙ በኋላ በፍርድ ቤት ቅጣት የማሰጠቱ ሂደት በተገቢው መንገድ እየሄደ ቢሆንም አስቀድሞ መከላከሉ ላይ ግን ስራዎች በተገቢው መንገድ ባለመሰራታቸው ከፍተኛ ችግር ማስከተላቸውን ወ/ሮ ምሳየ ከድር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጥቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ መከላከሉ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ነው መጉላት ያለበት፤ ጥቃቱ ከተፈመ በኋላ ግን ከሆስፒታልም ጋር ፣ ከፍትህ አካላትም ጋር በጋራ እየሰራን ነው፡፡ መከላከሉ ላይ ካልተሰራ ከባድ ነው እየሆነ ያለው፡፡›› ባለፉት ወራቶች 90 የሚደርሱ ጥቃቶች በደሴ ከተማ በሴቶች ላይ ተመዝግበዋል፡፡
ኢሳያስ ገላዉ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር