1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩስያ ቅጥር ተዋጊ ቡድን  በማሊ? 

ቅዳሜ፣ መስከረም 8 2014

ቅጥረኛ ተዋጊዎች የተባሉት ማሊ ስለመዝመት አለመዝመታቸው ዶቼቬለ የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ጠይቆ ነበር።ፔስኮቭ ይህን አስተባብለዋል፤ከማሊ ጋር ምንም ዓይነት ወታደራዊ ስምምነትን የተመለከተ ውይይት አልተካሄደም ሲሉ። አንዳንድ የሩስያ ድረ ገጾች ግን ከ1200 በላይ የሩስያ ቅጥር ተዋጊዎች ማሊ ይገኛሉ ሲሉ ዘግበዋል።

Magazin Global 3000 | 20.09.2021
ምስል WDR

የሩስያ ቅጥር ተዋጊ ቡድን  በማሊ? 

This browser does not support the audio element.

የሩስያ ቅጥር ተዋጊ እንደሆነ የሚነገርለት «ቫግነር» የሚባለው ቡድን፣ ሩስያ ፈጽማቸዋለች በተባሉ የጦር ወንጀሎች ይከሰሳል።ይህ ቡድን ማሊ ሊሰፍር ከባማኮ መንግስት ጋር ለመስማማት ተቃርቧል መባሉ ጀርመንና ፈረንሳይን አስቆጥቷል ።ወታደሮቻቸውን ማሊ ያዘመቱት ሁለቱ  መንግስታት ይህን ተቃውመው ወታደሮቻቸውን  ከማሊ ለማስወጣት እየዛቱ ነው። 
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መደበኛ ሠራዊት ያልሆኑ በአፍሪቃ ወታደሮችን የሚያሰለጥኑና ለከፍተኛ ባለሥልጣናት በአጃቢነት የሚሰሩ የሩስያ ተዋጊዎች የተሰባሰቡበት ቫግነር የተባለው ድርጅት አሰልጣኞችና  እና አማካሪዎች ተጽእኖ በክፍለ ዓለሙ እየጨመረ ነው። ፣የሩስያ   ቅጥር ተዋጊ እንደሆነ የሚነገርለት ሚስጥራዊው ቫግነር የተባለው ቡድን፣በዩክሬን በአፍሪቃ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ፣ሩስያ ከተሳተፈችባቸው ጦርነቶች ጋር ስሙ ይነሳል። ሰሞኑን ደግሞ ምዕራብ አፍሪቃዊቷ አገር ማሊ፣የቡድኑን ተዋጊዎች ለመቅጠር በውይይት ላይ መሆኗ ተሰምቷል። የዶቼቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ እንደዘገበችው ባማኮ ቡድኑን ማሊ ለማስገባት መዘጋጀቷን የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አሉ። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤ ኤፍ ፒ ሁለት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳለው ፣ማሊ ከግል ተዋጊዎች ከተውጣጣው ከዚህ የሩስያ ሚስጥራዊ ቡድን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርባለች።በማሊ ጽንፈኛ አማጽያንን ለመውጋት ወታደሮቻቸውን ማሊ ያዘመቱትት ጀርመንና ፈረንሳይ  የማሊ መንግሥት ከቫግነር ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርቧል መባሉን በመቃወም የማሊን መንግሥት አስጠንቅቀዋል።ፈረንሳይ ማሊ ያሰማራቻቸው ወታደሮቿ ቁጥር ከ5ሺህ በላይ ነው ። ከአንድ ሺህ በላይ የጀርመን ወታደሮችም ሚኑስማ በተባለው የተመድ የማሊ ተልዕኮ ስር  ዘምተዋል።የማሊ መንግሥት አንድ ሺህ የቫግነርን ተዋጊዎች ሊቀጥር ማቀዱ ነው የተሰማው። የማሊ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሀገሪቱን ደኅንነት አስተማማኝ ለማድረግ ግንኙነቱን ማስፋት እንደሚፈልግ አስታውቀው እስካሁን ግን ከቫግነር ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳልተፈረመ ገልጸዋል። 
ቅጥረኛ ተዋጊዎች የተባሉት ማሊ ስለ መዝመት አለመዝመታቸው ዶቼቬለ የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ጠይቆ ነበር ።ፔስኮቭ ይህን አስተባብለዋል፤ከማሊ ጋር ምንም ዓይነት ወታደራዊ ስምምነትን የተመለከተ ይፋዊ ውይይት አልተካሄደም ሲሉ። አንዳንድ የሩስያ ድረ ገጾች ግን ከ1200 በላይ የሩስያ ቅጥር ተዋጊዎች ማሊ ይገኛሉ ሲሉ ዘግበዋል።
ማሊ ቀደም ባሉት ዓመታት ከሩስያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበራት።በጎርጎሮሳዊው 1960  ከቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ተላቃ ሥልጣኑን የሀገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሞዲቦ ኬይታ ሲይዙ ፊታቸውን ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ነበር  ያዞሩት።ያኔ ለሩስያ ያቀረቡት ጥያቄ የማሊን ጦር እንድታሰለጥን ነበር።ይህ ወታደራዊ ስምምነትም እስከ ጎርጎሮሳዊው 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ዘልቋል።ሞሀማዱ ኮናቴ የተባሉ ተንታኝ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት አብዛኛዎቹ በሥልጣን ላይ የሚገኙ የማሊ ጦር ኃይል አባላት ሩስያ ነው የሰለጠኑት ፤ለክሬምሊንም ቅርብ ናቸው። ይሁንና በርሳቸው እምነት ቫግነር የተባለው የሩስያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ሚሊ እንዳይሰፍር መጠንቀቅ ይገባል።
«ባዶ እጃቸውን አይመጡም።ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይዘው ነው የሚመጡት።የማሊ ጦር ከዚህ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።ሆኖም በሌላ በኩል ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ተጽእኖዎቹንም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።እነዚህን ቅጥረኛ ተዋጊዎች ማዝመት የለብንም።መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሊፈጽሙ የመቻላቸው ስጋት አለ።»
ቫግነር ማሊ ሊገባ ነው የመባሉ ዜና ከተሰማ በኋላ ፈረንሳይ  ወታደሮቿን ከማሊየማስወጣት ምልክቶች አሳይታለች። የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦን ኢቬ ለድርዮን የቫግነር ማሊ መግባት ጥቅም አይኖረውም ሲሉ፤ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር አነግሬት ክራምፕ ካረንባወር በትዊተር ባስተላለፉት መልዕክት «በማሊና በሩስያ መካከል የሚደረግ ይህን መሰል ስምምነት ጀርመን ፈረንሳይ የአውሮጳ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት ላለፉት 8 ዓመታት በማሊ ሲያከናውኑ የቆዩትን የሚጻረር ነው።»ብለዋል። በተዘዋዋሪ መንገድ ጀርመንም ወታደሮቿን ከማሊ ማስወጣቷ እንደማይቀር አስጠንቅቀዋል።ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በጎርጎሮሳዊው 2018 ቫግነርን ለእርዳታ ስታስገባ ፣ፈረንሳይ በሃገሪቱ የነበራትን እንቅስቃሴ ወዲያውኑ ነበር ያቆመችው። ማሊ ከሩስያ ጋር ለመስማማት ተቃርባለች የተባለው የጥቅምቱ የፈረንሳይ አፍሪቃ ጉባኤ ከመካሄዱ አስቀድሞ ነው። ምናልባትም ማሊ በዚህ እርምጃ ከፈረንሳይ ውጭ ከሌሎች ሀገራትም ጋር ትብብሮችንም መፍጠር እንዲሚቻል ለፈረንሳይ በማሳየት ጫና ለማሳደር አስባ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል።ለጀርመኑ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ቅርበት ያለው ኮናርድ አደናወር የተባለው የጀርመን የጥናትና ምርምር ተቋም የሳህል ሀገራት አካባቢ ሃላፊ ቶማስ ሺለር ሩስያ በማሊ ጉዳይ ውስጥ መግባትዋ እንዳላስገረማቸው ተናግረዋል።ይህ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ሲናፈስ የቆየ መሆኑን በተለይ ለጦር ኃይሉ የፀጥታ አጠባበቅ ስልጠናዎችን እንደምትሰጥ ማሣሪያም ልታቀርብ እንደምትችል ይነገር እንደነበረ አስረድተዋል።ሆኖም እነዚህ ጉዳዮች መጣራት አለመቻላቸው አንዱ ችግር መሆኑን ገልጸዋል። ሺለር ማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ውስጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሃገራት በሙሉ ለውይይት እንዲቀመጡ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚሁ ጋር ማሊም ሆነች ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ሉዓላዊ ሀገሮች ስለሆኑ ምዕራባውያኑ ይህን አድርጉ ፣ያን አታድርጉ ማለት እንደማይገባቸውም አሳስበዋል።  
«እነዚህ ሉዓላዊ መንግሥታት ናቸው። ለአፍሪቃውያን የሚበጃቸው ምን እንደሆነ መንገር የኛ ስራ አይደለም። ይህን መለየት ፣የፖለቲካ ስርአታቸውንና ጦር ኃይላቸውን ማሻሻል ፤ የነርሱ ድርሻ ነው።»
የቫግነር ቡድን አንዳንዶች እንደሚገልጹት ሩስያዊ የግል ወታደራዊ ኩባንያ ነው።ቡድኑ የሚመለምላቸው ተዋጊዎች የሶሪያውን የርስ በርስ ግጭት ጨምሮ በተለያዩ ውጊያዎች ላይ እንደተሳተፉ ተዘግቧል። ቡድኑ ብቅ ያለው በጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓም በተጀመረው በዩክሬኑ ጦርነት ወቅት ነበር። ከ2014 እስከ 2015  ከዩክሬን ለመገንጠል ራሳቸውን የዶኔትስክና የሉሃንስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ ብለው ይጠሩ የነበሩት ኃይሎች በማገዝ በዶንባስ ዩክሬን በተካሄደው ጦርነት፣ የቫግነር ቡድን ተሳትፏል። ቡድኑ ከዩክሬን ቀጥሎ በሶሪያው ጦርነትም ተካፋይ ነበር። የበሽር አል አሳድ መንግሥትን ደግፎ ነበር የሚዋጋው። በወቅቱም ቡድኑ ሰዎችን ቁም ስቅል በማሳየትና የነድጅ ዘይት ማውጫ ስፍራዎችን በመጠበቅ  በሩስያ መገናኛ ብዙሀን ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል። ከዚያም የቫግነር ተዋጊዎች ተለዋዋጭ ፖለቲካ ወዳለባት እንደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክና ሊቢያን በመሳሰሉ የአፍሪቃ አገራት መሰማራት ጀመሩ ። ቡድኑ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወታደራዊ ስልጠና ይሰጣል፤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፋውስቲን አርቻንጄ ቱዋዴራ አጃቢዎች ሩሲያዊያኑ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ናቸው ፣በሊቢያ የጦር አበጋዙን የጀነራል ካሊፋ ሃፍታርን ኅይሎችና አስተዳደር በማጠናከር  ሥራ ላይም ነበሩ።በሌሎች ቦታዎች ደግሞ በግል ጠባቂነትም ይሰራሉ።
ኒውዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ በአንድ ዘገባው ፣ሚስጥራዊውን ቡድን ቫግነርን የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር አካል ሲል ገልጾታል።ጋዜጣው እንደጻፈው  የቡድኑ አባላት የሚሰለጥኑት በሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ተቋማት ውስጥ ነው።ባለቤቱም ይቭጌኒ ፕሪጎዚን የተባሉ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ከበርቴ መሆናቸውንም ዘግቧል።የ60 ዓመቱ ፕሪጎዚን ግን ከቫግነር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም ሲሉ ያስተባብላሉ።ሊብያን እንዳትረጋጋ በማድረግና በ2016ቱ የዩናይትድስቴትስ ምርጫም ጣልቃ በመግባት የተወነጀሉት ፕሪጎዚን፣ የአውሮጳ ኅብረትና ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ጥለውባቸው ነበር።እርሳቸው ግን እነዚህንም ውንጀላዎች አስተባብለዋል። በሶቭየት ኅብረት ዘመንም ፣በሙስናና በስርቆት ተወንጅለው 9 ዓመታት ታስረዋል።ሶቭየት ኅብረት ከተፈረካከሰች በኋላ ግን ከክሬምሊን ጋር ተቀራርበው ልዩ ልዩ ኮንትራቶችን ያገኙ ባለሀብት ናቸው። 
የፕሪጎዚን ነው የሚባለው ይህ ቡድን እንደማናቸውም የግል ቅጥር ተዋጊ ኩባንያዎች በሩስያ በሕግ የታገደ ቢሆንም ቡድኑ ተዋጊዎችን ከሩስያ ሕግ አስፈጻሚዎችና ከጦር ኃይሉ እንደሚመለምል ነው የሚገለጸው።በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም በዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ይጠበቁ የነበሩ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያዎችን ለመያዝ በተካሄደ ውጊያ የበርካታ የቫግነር ቅጥር ተዋጊዎች ሕይወት አልፏል።የቡድኑ ተቀጣሪዎች ደሞዝ የሩስያ መንግሥት በአማካይ ከሚከፍለው በአምስትና በስድስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው ይባላል።አንዳንድ የሩስያ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ለቡድኑ ይዋጋሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በውጊያ ሲሞቱ ቤተሰቦቻቸው ስለ አሟሟታቸው  ምንም እንዳይናገሩ በማስጠንቀቅ ጠቀም ያለ ገንዘብ ይሰጣቸዋል። የመብት ተሟጋቾች ቫግነርን በሶሪያ የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም ሲወነጅሉ፣ የተመድ ደግሞ ቡድኑን በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ይጠረጥረዋል። 
የቅጥረኛ ወታደሮችን ጉዳይ የሚከታተለው የተመድ ቡድን ሊቀመንበር የሌና አፓራክ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ብለዋል።የተመድም እያጣራ እንደሆነ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
«በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ ያለውን ወቅታዊ መረጃ እናጣራለን፤ጉዳዩ በጣም አሳስቦናል ።የተመድ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ወይም የግል የግል የየደኅንነት ኩባንያዎችን መቅጠርን ይቃወማል። የግል ውሎች ካሉም የስራው ሂደት ግልጽ መሆን አለበት።»
የአዝዋርድ ንቅናቄ ኅብረት በአጭሩ CMA ተብሎ የሚጠራው የቀድሞ የማሊ ተገንጣይ ቡድኖች ኅብረት መንግሥት ከሩስያ ቅጥር ተዋጊዎች ጋር ለመስማማት ማሰቡን ተቃውሟል።ማሊ ጦርነት ውስጥ የገባችው በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓም CMA ን ጨምሮ የቱዋሬግ ተገንጣዮች በጂሀዲስቶች ድጋፍ በሰሜን ማሊ ማመጽ ከጀመሩ በኋላ ነው።ግጭቱ ተባብሶ እስከዛሬም ቀጥሏል። የአክራሪ ሙስሊሞች አመጽ ከማዕከላዊ ማሊ ወደ ጎረቤት ቡርኪናፋሶና ኒዠርም ተዛምቷል።CMAና ሌሎች የቀድሞ አማጽያን በ2015 ዓም አልጀርስ ውስጥ ከተካሄደ ንግግር በኃላ ጦርነቱን ለማቆም ከማሊ መንግሥት ጋር የሰላም ውል ተፈራርመው ነበር።ውሉ አማጽያንን በማሊ ጦር ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርግ ነበር።እስካሁን ግን ተግባራዊ አልሆነም።ቫግነር ማሊ ይዘምታል መባሉ የጀርመን ወታደሮች የማሊ ዘመቻ እንደገና እንዲታይ እዚህ ጥያቄ አስነስቷል።የማሊ መንግሥት ከሩስያ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ጋር የሚሰራ ከሆነ ጀርመን ለማሊ ወታደሮች የምትሰጠው ስልጠና እንዲቆም የጀርመን የአረንጌዴዎች ፓርቲ እጩ መራሂተ መንግሥት አሳስበዋል።የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ እጩ መራሄ መንግሥት አርሚና ላሼትም የሩስያ ቅጥር ተዋጊዎች ማሊ ገብተው ከሆነ በቅርቡ አንድ ውሳኔ ላይ መደረስ አለበት ብለዋል።በአሁኑ ጊዜ ወደ 1200 የሚደርሱ የጀርመን ወታደሮች በተመድ የማሊ ተልዕኮ ስር የማሊ ወታደሮችን እያሰለጠኑ ነው።

ምስል Frederic Petry/Hans Lucas/picture alliance
ምስል picture alliance/dpa/Bundeswehr
ምስል picture alliance/dpa/Bundeswehr
ምስል WDR
ምስል Frederic Petry/Hans Lucas/picture alliance

ኂሩት መለሰ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW