1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝዋዜአፍሪቃ

አወዛጋቢው የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት

ሐሙስ፣ ጥር 16 2016

ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት ከሶማሊያ ላንድ ጋር ለወደብ አገልግሎትና የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር ሊሆን የሚችል የባህር በር እንድታገኝ የሚፈቅድ የመጀመሪያ ደረጃ ውል መፈራረሟ፤ የወቅቱ ትልቁ የመንጋገሪያ አጀንዳ ከመሆን አልፎ፤ በአካባቢው ሌላ የውዝግብና ግጭት ምክንያት እንዳይሆንም አስግቷል።

ክራይስስ ግሩፕ
ዓለም አቀፍ የቀውስ መንስኤዎችን የሚከታተለው ተቋም ክራይስስ ግሩፕ ምስል Gemeinfrei

አወዛጋቢው የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት በአውሮጳውያኑ አዲሱ አመት የመጀመሪያ ቀን ከሶማሊያ ላንድ ጋር ለወደብ አገልግሎትና የባሕር ኃይል ሰፈር ሊሆን የሚችል የባሕር በር እንድታገኝ የሚፈቅድ የመጀመሪያ ደረጃ ውል መፈራረሟ፤ የወቅቱ ትልቁ የመንጋገሪያ አጀንዳ ከመሆን አልፎ፤ በአካባቢው ሌላ የውዝግብና ግጭት ምክንያት እንዳይሆንም አስግቷል። ኢትዮጵያና ሶማሊያ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስነድ ሙሉ ይዘት እስካሁን በትክክል ባይታወቅም፤ ለባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ፤ በበርበራ ወደብ እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ የባሕር በር ለ50 ዓመት በሊዝ የሚያስገኝ እንደሆነ ተገልጿል።

የሶማሊያ ተቃውሞና የፈጠረው ስጋት

ሶማሊላንድእ.እ.እ. ከ1991 ም ጀምሮ ከሶማሊያ በመገንጠል ነጻነቷን ያወጀችና የራሷን መንግሥታዊ መቅር የመሠረተች ቢሆንም፤ እስካሁን ግን ባንድም አገር እውቅና ያልተሰጣትና ሶማሊያም የራሷ ለኡላዊ ግዛት አካል አድርጋ የምትቆጥራት ናት። በዚህም ምክንያት ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከግዛቲቱ ጋር ያደረገችው ስምምነት ሕገወጥና የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚደፍር ነው በማለት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ነች። ይህ አለመግባባትና ውዝግብ በአካባቢው ሌላ የፖለቲካ ችግርና ምናልባትም ወታደራዊ ግጭት እንዳይፈጥር ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂቶች አይደሉም። ዶቼ ቬለ ከናይሮቢ ያነጋገራቸው በዓለም አቀፍ ግጭቶች ላይ የሚሠራው ተቋም የምሥራቅ አፍርቃ ተመራማሪና ተንታኛ ሚስተር ኦማር ሞሃሙድ፤ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ላንድ ስምምነት ለብዙዎች እንግዳ ደራሽና ያልተጠበቀ ቢሆንም፤ የሶማሊያው ተቃውሞና ቁጣ ግን ብዙዎች ከገመቱት በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሶማሊያ ላንድ በወደብ ጉዳይ ከሌሎች አገሮች ጋርም ስምምነት ማደርጓ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ ለምን ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው ውል በዚህ ደረጃ ተቃውሞ እንዳስነሳ ሲያብራሩም፤ «በርክታ ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል፤ አንደኛው፤ የሶማሊያ መንግሥት ስለስምምነቱ ምንም ነገር እንዲያውቅ አለመደረጉ ይመስለኛል። የሶማሊያ መንግሥት በጅቡቲ ከሶማሊያ ላንድ ጋር  ሁለቱ ወገኖች ወደ ውይይት ሊመጡ በሚችሉበት ሁኒታ በተነጋገሩ ማግሥት ይህ ውል መፈረሙ የሶማሊያን መንግሥት ከጀርባ የመወጋት ስሜት ሳይፈጥርበት አልቀረም። ሁለተኛው  በሁለቱ አገሮች ከነበረው ታሪካዊ ግንኙነትና ውጣ ውረዶች  የሚያያዝ ሊሆን ይችላል። ሦስተኛውና ዋናው ግን የደህንነት ጉዳይም ይመስለኛል በማለት፤ ስምምነቱ የወደብ አጠቃቀም ብቻ ሳይሆን የባሕር ኃይል መመስረትንም ስለሚይዝ፤ ይህም ሌላው የስጋት ምንጭ ሆኖ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የዓለምን ትኩረት የሳበው የአፍሪቃው ቀንድ የባሕር ወደብ፤ ፎቶ ከማኅደር፤ የጅቡቲ የባሕር ወደብምስል ZUMA Wire/imago images

ሶማሊላንድ አገር ያልሆነች አገር

4.5 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሶማሊላንድከዋናዋ ሶማሊያ በተሻለ ሁኔታ ምርጫ በማካሄድ ጭምር የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት መመስረት የቻለች፤ የራሷን ገንዘብ ያተመችና፤ የራሷ የጸጥታ ኃይል ያላት፤ ባጠቃላይም የተሟላ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚከወንባት አገር መሆኗ ቢታወቅም፤ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ግን ሁለቱ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በውይይት ከመፍታታቸው በፊት ጣልቃ መግባት እንደማይፈልግና አሁንም ሁለቱ ሶማሊዎች ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ግፊት እንደሚያደርግ ያስታወሱት ሚስተር ኦማር፤ በሶማሊላንድ በኩል ግን ላለፉት 30 ዓመታት የተደረጉት ውይይቶች ውጤት አላስገኙም የሚል የተስፋ መቁረት ስሜት እንዳለ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ውዝግቡ መካረር መዘዝ

ይህ የወደብ ስምምነት የፈጠረው አለመግባባትና ውዝግብ ወዴት ሊያመራ እንደሚችልም ሚስተር ኦማር ሲገልጹ፤ « አለመግባባቱና ውዝግቡ ቀጥሎ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ፤ የጸጥታ ስጋት ሊፈጥር ይችላል። ይህ ማለት በሶማሊያና ኢትዮጵያ ወይም በሶማሊላንድና ሶማሊያ ጦርነት ይቀሰቀሳል ማለት ላይሆን ይችላል፤ ይህ ሁለተኛ ስጋት ነው የሚመስለኝ፤ ይልቁንስ ይበልጥ የሚያሰጋው፤ ውጥረቱ ከቀጠለና የሶማሊያን ኢትዮጵያ ግንንኙነት ከተበላሸ፤ ክፍተቱን አልሸባብ እንዳይጠቀምበት ነው» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ሚስተር ኦማር አልሸባብ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት፤ የሶማሊያን ብሔርተኝነት ለመቀስቀስ ሊጠቀምበትና የሚፈጠሩ ክፍተቶችንም ለወታደራዊ ጥቃት ሊይውላቸው እንደሚችል ያላቸውን ስጋትም ገልጸዋል ። በተጨማሪም ይህንን ውዝግብና አለመግባባት ለራሳችው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅም ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን አንስተው፤ ለመፍትሄው ግን ከሁሉም በላይ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት መቀራረብና መወያያት ያለባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW