1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አውሮፓ ኅብረት የመስፋፋት ፖሊሲ ታሪክ እና ሒደት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2016

ከ65 ዓመታት በፊት የአውሮፓ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ተብሎ በስድስት አገሮች የተመሰረተው የአውሮፓ ኅብረት የበለጠ የሚስፋፋበትን ውሳኔ የኅብረቱ መሪዎች ባለፈው ሣምንት አሳልፈዋል። ውሳኔው ዩክሬን እና ሞልዶቫ የኅብረቱ አባል ለመሆን የሚያስችላቸውን የመግቢያ ንግግር እንዲጀምሩ የፈቀደ ነው።

ኡርሱላ ፎን ደር ላየን፣ ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እና ቻርልስ ሚሼል
ከሩሲያ ጦርነት የገጠመችው ዩክሬን የአውሮፓ ኅብረትን በፍጥነት የመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት አላት።ምስል፦ Virginia Mayo/AP

አውሮፓ ኅብረት የመስፋፋት ፖሊሲ ታሪክ እና ሒደት

This browser does not support the audio element.

የአውሮፓ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ተብሎ በጎርጎሮሳዊው 1958 ዓ.ም በስድስት አገሮች የተመሰረተው የዛሬው የአውሮፓ ህብረት፤ ሰፍቶና አድጎ  የአባላቱ ቁጥር ከ27 ወደ ሰላሳና ከዚያም በላይ ሊዘልቅ የሚችልበትን ሁኔታ የህብረቱ አገሮች መሪዎች ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት ጉባያቸው አመቻችተዋል ውስነዋልም።

የስድስት አገሮች ስብስብ የነበረው የኤኮኖሚ ማህብረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰፋው እንደ አውሮፓውያኑ አቅጣጠር በ1973 ዓም ዴንማርክን፤ አየርላንድን እና በኋላ ህብረቱን የለቀቀችውን ብርታንያን  በመጨመር ነበር። በ1981 ግሪክ፤ በ1986 ደግሞ ስፔን እና ፖርቱጋል ህብረቱን ተቀይጠዋል። በ1995 ኦስትሪያ፤ ፊንላድ እና ስዊድን በመቀልቀል ህብረቱን የበለጠ ማስፋት ብቻ ሳይሆን አጎልብተውታል።

 የአውሮጳ ኅብረት ዩክሬንና ሞልዶቫ ለአባልነት ድርድር እንዲጀምሩ ፈቀደ

በ2007 ግን የበርሊንን ግንብ መፍረስ እና የቀዝቃዛው አለምን ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በሶቭየት ህብረት ጥላ ስር የነበሩ 10 የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ባንድ ግዜ ወደ ህብረቱ ገቡ። በ2013 ዓም ክሮሺያ ከተቀላቀለች በኋላ ግን፤ ላለፉት አስር ዓመታት የአውሮፓ ህብረት እንዲያውም ብርታኒያን ቀንሶ ባለበት ነበር የቆየው።

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በተለምዶ ማዕቀብ እና በጀትን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አንዳች ውሳኔ ለማሳለፍ ከፍተኛ ሙግት ይገጥማሉምስል፦ European Union

ቱርክን ጨምሮ የምዕራብ ባልካን ሀሮች የሆኑት ሰሜናዊ ሜቄዶኒያ፤ ሞንትኔግሮ፣ ሰርቢያ እና አልባኒያ እጩ አባሎች ቢሆኑም ፋይላቸው ግን ለብዙ አመታት ሳይንቀሳቀስ ቆይቷል። የቀለም አብዮት በሚባለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከሩሲያ የተለዩት ዩክሬን እና ሞልዶቫም የህብረቱ አባል ለመሆን ፍላጎት ቢያሳዩም በ2022 የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስ ግን አባል ለመሆን በይፋ አልጠይቁም። 

ዩክሬን እና ሞልዶቫን በአባልነት የሚቀበለው ውሳኔ

በሰኔ ወር 2022 የአውሮፓ ህብረት ዩክሬን እና ሞልዶቫን የእጩ አባልነት ደረጃ እንዲሰጣቸው እና ለአመታት ሲንከባለል የቆየው የምዕራብ ባልካን የአባልነት ድርድርም እንዲፋጠን ውሳኔ አሳለፈ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ በተለይ ዩክሬን እና ሞልዶቫ የህብረቱ አባል ለመሆን የሚያስችላቸውን የመግቢያ ንግግር እንዲጀምሩ ወስኗል። ውሳኔው በቀላሉ እንዳልተላለፈ እና እንደተለመደው የሁሉንም የህብረቱን አገሮች ይሁንታ ያገኘ እንዳልነበር ታውቋል። 

በአውሮጳ ደጃፍ በሞሮኮዋ ናዶር የሚገኙ ስደተኞች ይዞታ

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ከገባችበት ጦርነት እና ሞልዶቫም ካለባት ስጋት አንጻር ሁለቱን አገሮች አባል ማድረግ፤ እነዚህ አገሮች መደገፍ ብቻ ሳይሆን ለህብረቱ ለራሱም የደህንነት ዋስትና የሚያስገኝ ነው በማለት ብዙዎቹ አባል ሀገሮች የመግቢያ ንግግሩን እንዲጀምሩ ደግፈዋል። ከሁሉም በላይ ግን እነዚህን ሀገሮች በአባልነት አለመቀበል ለሩሲያና እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትልቅ ድል ሊሆን ይችላል በማለትም ይህ እንዳይሆን ጥያቄያቸውን መቀበልና ሀገሮቹን በህብረቱ ማቀፍ እንደሚያስፈልግ ብዙዎች አጥብቀው ተከራክረዋል።

የሐንጋሪ ተቃውሞ እና ሙግት

ሐንጋሪ እና ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉት መሪያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን መከራከሪያቸውን በተደነገጉት የመግቢያ መስፈርቶች ላይ በማድረግ ዩክሬን መመዘን ያለባት በተቀመጡት መስፈርቶች ብቻ መሆን እንዳለባትና እነዚህንም ስለማታሟላ የመግቢያ ንግግሩን እንድትጀምር ሊፈቀድላት እንዳማይገባ አጥብቀው ሲከራከሩ ተስምተዋል። 

የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ቅርበት እንዳላቸው ይነገራልምስል፦ Yves Herman/REUTERS

ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን “የአውሮፓ ህብረት መስፋፍት ንድፈ ሀሳብ አይደለም። የአፈጻጸም ብቃት እና የህግ ሂደት ያለው ነው።  ሰባት መስፈርቶች ተቀምጠዋል። ከነዚህ ውስጥ ውስጥ በራሱ በኮሚሽኑ እንደተገለጸው ቢያንስ ሶስቱ አልተሟሉም። ስለዚህ ድርድሩን ልትጀምር አትችልም” በማለት የመንግስታቸውን አቋም አስቀድመው አስታውቀው ነበር ወደ ስብሰባው የገቡት።

የአውሮፓ ኅብረት የ2023 የዓመቱ የመጨረሻ የመሪዎች ጉባኤ

ውሳኔው የሁሉንም አባል ሀገሮች ስምምነት የሚጠይቅ በመሆኑን እና ሰፊ ልዩነት የተስተዋለበት ስለሆነ፤ ምን ሊወሰን እንደሚችል ተሰብሳቢዎቹ ሳይቀር እስከመጨርሻው ሰአት ድረስ አያውቁም ነበር። በመጨርሻ ግን የጉባኤው ሰብሳቢ ሚስተር ሊዊ ሚሸል  ምሽት ላይ ጉባኤውና አቋርጠው ወደ ጋዜጠኞች  በመዝለቅ፤ መሪዎቹ የደረሱበትን ውሳኔ ስሜት በተቀላቀለበት ሁኒታ አስታውቀዋል።

“ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ነው። የህብረቱን ጥንካሬ እና ታማኒነት ያረጋገወጠ ውሳኔ” በማለት ዩክሬን እና ሞልዶቫ ያባልነት መግቢያ ንግግር እንዲጀምሩ፤ ጆርጂያ የእጩ አባልነት ደረጃ እንዲሰጣት እና ከቦስኒያ ሔርዞጎቪኒያም ጋር መሟላት የሚገባቸው እንደተሟሉ የመግቢያ ንግገር እንዲጀመር የተወስነ መሆኑን አበሰሩ። የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንዴር ሌየንም ውሳኔውን “ትልቅና ህብረቱም የገባውን ቃል የሚያከብር መሆንን ያረጋገጠበት” ሲሉ ገለጹት። በበርካታ ቀውስ ውስጥ ባለችው ዓለም ተጨማሪ አባል ሀገራትን ወደ ህብረቱ ማምጣት ኢንቨስትመንት እና የደህንነትም ዋስትና ነው በማለትም አንድምታውንም አውስተዋል።

ውሳኔው ሁሉንም ወገኖች ያስደንቀ እና ያልተጠበቀ እንደነበር ነው ተደጋግሞ የሚገለጸው። በጉባኤው ሰፊ ክርክር ከተደረገ በኋላ ምንም አይነት መስማማት እንማይደረስ ሲታወቅ ፤ የጀርመኑ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሹልስ ሚስተር ኦርባንን አዳራሹን ለቀው ቢወጡ እና እሳቸው በሌሉበት ውሳኔውን ለማሳለፍ ቢችሉ ጠይቀዋቸው አዳራሹን ለቀው ከወጡ በኋላ ባልተለመደ ሁኔታ ሀያ ስድስቱ አባል ሀገሮች ውሣኔውን ማስተላለፍ እንደቻሉ ተገልጿል።

ዩክሬን እና ሞልዶቫ የኅብረቱ አባል ለመሆን የሚያስችላቸውን የመግቢያ ንግግር እንዲጀምሩ የተላለፈውን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ቻርልስ ሚሼል ናቸውምስል፦ Virginia Mayo/AP Photo/picture alliance

የሁሉንም ተሰብሳቢዎች ስምምነት የሚጠይቁ ውሳኔዎች አንዱ አባል በሌለበት ሊወሰኑ ስለሚችሉ፤ ይህንኑ ዘዴ በመጠቀምና ሚስተር ኦርባንም በመስማማታቸው ውስኔው መተላለፉ ታውቋል። 

የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ከውሳኔው በኋላ፤ አገራቸው የዚህ ትክክል ያልሆነ ውሳኔ አካል መሆን ስለማትፈልግ ውሳኔውን እንዲያሳልፉ አዳራሹን ለቀውላቸው የወጡ መሆኑን አስታውቀል። ሌላውንና ቀጥሎ የተመከረበትን የዩክሬንን የ50 ቢሊዮን ኢሮ እርዳታ ግን ኦርባን ማገዳቸው ታውቋል።

ሩሲያ እና አሜሪካ በተለይ እነዚህ ሁለት ሀገሮች ዩክሬን እና ሞልዶቫን ወደ ህብረቱ እንዲገቡ ለማድረግ በተወሰነው ውሳኔ ላይ የሰጧቸው አስተያየቶች፤ ጉዳዩ ከሁለቱ አገሮች እና ከህብረቱ አባል ሀገሮች የበለጠ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

የአውሮጳ ኅብረት በጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ የተኩስ ፋታ ጠየቀ

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዴሚትርይ ፔስኮቨ “ወደ አውሮፓ ህብረት የሚያስገባውን መስፈርት እነዚህ ሁለት አገሮች እንዳላሟሉ ይታወቃል” በማለት ውሳኔው ፖለቲካዊ እንደሆነ እና የሀገሮቹ ወደ ህብረቱ መግባት ይልቁንም ለአካባቢው አለመረጋጋት ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ባንጻሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ውሳኔው የአውሮፓን እና የአሜሪካን ግንኙነት ጭምር የሚያጠናክር ታርካዊ ውሳኔ እንደሆነ ገልጿል።

የኮፐን ሄገን መስፈርቶችና የአባልነት ሂደት ደረጃዎች  

በመሰረቱ ማንኛውም ሀገር የህብረቱ አባል ለመሆን የኮፔን ሄገን መስፈርቶች የሚባሉትን መመዘኛዎች ማሟላት ይኖርበታል። በጎርጎሮሳዊው በ1993 በኮፔን ሄገን የመሪዎች ጉባኤ የጸደቁት መስፈርቶች፤ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት መኖር እና የሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ መረጋገጥን፤ የተረጋጋ እና ገበያ መር የሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት መኖሩን እና የህብረቱን ህጎችን ደንቦች ማክበርና መቀበል መቻልን የሚጠይቁ ናቸው።

ባለፈው ሣምንት በተካሔደው ስብሰባ ጆርጂያ የእጩ አባልነት ደረጃ እንዲሰጣት እና ከቦስኒያ ሔርዞጎቪኒያም ጋር መሟላት የሚገባቸው እንደተሟሉ የመግቢያ ንግገር እንዲጀመር ተወስኗል።

የአባልነት ሂደቱም በእጩ አባልነት፤ በመግቢያ ድርድር እና በመጨረሻም በመግቢያ ስምምነት ምራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በርካታ አመታትንም የሚወስድ ነው። ቱርክ የመግቢያ ንግግር ከጀመረች ሀያ አመት የሞላት ቢሆንም ድርድሩ አልቆ አባል የምትሆንበት ጊዜ ግን የማይታሰብ እንደሆነ ነው የሚነገረው።

የውሳኔው አንድምታና ተግዳሮት

ይህ በዚህ እንዳለ አሁን በተለይ ዩክሬን እና ሞልዶቫን ወደ ህብረቱ ለማስገባት የተወሰነው ውሳኔ፤ በሌሎች ለበርካታ አመታት እጩ ሆነው በቆዩ እንደ ቱርክ በመሰሉ ሀገሮች ቅሬታ መፍጠሩ እና ግንኙነትንም ሊያሻክር እንደሚችል ነው የሚገመተው። በተጨማሪም ህብረቱ አገሮቹን አባል ለማድረግ የሔደበት አሰራር ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን ሊደገም እንደማይችል እየተነገረ ሲሆን፤ ህብረቱ ግን ባጠቃላይ በአሰራሩና ውሳኔ አሰጣጡ ለውጥ ማድረግ እንዳለብት የሚያሳስቡ አስተያየቶች በሰፊው እየተሰሙ ነው።

በደብሊን ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚስተር ዶናቻ ባቼይን “ያለው ሁኔታ ህብረቱ አሰራሩን እንዲለውጥ የሚያስገድድ” መሆኑን ተናግረዋል። “ለውጥ ማድረግ ያስፈልገዋል። ከበርካታ አስርት አመታት በፊት ስድስት የነበሩት አባላት ዛሬ 27 ደርሰዋል፤ ሌሎችም ሊገቡ ነው፤ ስለሆነም ችግሮቹን በሁሉም አባል ሀገሮች ስምምነት በሚተላለፍ የጋራ ውሳኔ መፍታት እንደማይቻል በመረዳት ከጊዜው ጋር የሚሔድ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል” ሲሉ የሁኔታውን አስገዳጅነት ጭምር አስገንዝበዋል። 

የአውሮፓ ህብረት አሁን የያዘው የመስፋፋት እና አዳዲስ አባላትን የመቀበል ፖሊሲ ቀጣይነት ግን በሚቀጥለው አመት በህብረቱ ሀገሮች በሚካሄዱ ብሔራዊ እና የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ውጤት የሚወሰን እንደሚሆንም ከወዲሁ በሰፊው ይነገር ይዟል።

ገበያው ንጉሴ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW