1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አውሮፓ የራሱን ጦር ሠራዊት እንዲያቋቁም የዩክሬን ፕሬዝደንት ጥሪ አቀረቡ

ቅዳሜ፣ የካቲት 8 2017

አሜሪካ ከዩክሬን ጀርባ ከሩሲያ ጋር ሥምምነት እንዳትፈጽም ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ አስጠነቀቁ። አውሮፓ ከእንግዲህ አሜሪካ በምትሰጠው የደሕንነት ዋስትና ላይ መተማመን እንደማይችል በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ የተናገሩት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ አኅጉራዊ ጦር ሊቋቋም እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በሙኒክ ጸጥታ ጉባኤ
በርካታ መሪዎች አውሮፓ የራሱ ጦር ሠራዊት እንደሚያስፈልገው ከዚህ ቀደም መናገራቸውን ያስታወሱት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ “የአውሮፓ ጦር ሠራዊት የሚመሠረትበት ጊዜው ደርሷል ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።ምስል፦ Thomas Kienzle/AFP

አሜሪካ ከዩክሬን ጀርባ ከሩሲያ ጋር ሥምምነት እንዳትፈጽም ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ አስጠነቀቁ። ዜሌንስኪ ዛሬ በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር “ዩክሬን ያለ እኛ ተሳትፎ ከጀርባችን የሚፈጸም ሥምምነትን በፍጹም አትቀበልም” ሲሉ ተደምጠዋል።

የዜሌንስኪ ተማጽኖ የተደመጠው ለሦስት ዓመታት የተካሔደውን ጦርነት ለመቋጨት አሜሪካ በምታደርገው ግፊት ውስጥ ዩክሬን መሳተፏን ለማረጋገጥ በምትፍጨረጨርበት ወቅት ነው።

ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ “ዩክሬን በሌለችበት ስለ ዩክሬን ምንም አይነት ውሳኔ ሊወሰን አይገባም። ያለ አውሮፓ ተሳትፎ ስለ አውሮፓ ምንም አይነት ውሳኔ ሊወሰን አይገባም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንቱ በሙኒክ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የጸጥታ ጉባኤ ጎን ለጎን ጦርነቱን ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ላይ ለመምከር ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ጄድ ቫንስ ጋር ተነጋግረው ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት ለማብቃት በቅርቡ ከፕሬዝደንት ብላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ገልጸዋል።

ዩክሬን ግን አሜሪካ ሩሲያን ለመቋቋም “የጋራ ዕቅድ” ልታቀርብ ይገባል የሚል አቋም አላት። ዜሌንስኪ ትላንት ከጄድ ቫንስ ከተነጋገሩ በኋላ እስካሁን ሩሲያን በተመለከተ የጋራ አቋም አለመኖሩን ተናግረዋል።

ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ የትኛም አይነት የሰላም ሥምምነት ሩሲያ የኋላ ኋላ ጦርነቱን መልሳ እንዳትጀምር እንዳይፈቅድ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ “የደሕንነት ዋስትና” ለማግኘት ግፊት እያደረጉ ነው። በሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣል እና የዩክሬንን ጦር መገንባት ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚረዳ የተናገሩት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ሀገራቸው በሒደት የአውሮፓ ሰላም አስከባሪ ለመቀበል ፈቃደኛ ለመሆኗ ፍንጭ ሰጥተዋል።

አውሮፓ ከእንግዲህ አሜሪካ በምትሰጠው የደሕንነት ዋስትና ላይ መተማመን እንደማይችል የተናገሩት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ አኅጉራዊ ጦር ሊቋቋም እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በርካታ መሪዎች አውሮፓ የራሱ ጦር ሠራዊት እንደሚያስፈልገው ከዚህ ቀደም መናገራቸውን ያስታወሱት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ “የአውሮፓ ጦር ሠራዊት የሚመሠረትበት ጊዜው ደርሷል ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።

የአውሮፓ መሪዎች ዜሌንስኪ ለተግባራዊ እርምጃ እና አኅጉሩ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ላቀረቡት ጥሪ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በጉባኤው እንዳሉት “ሰላም የሚኖረው የዩክሬን ሉዓላዊነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።” 

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ አውሮፓ የአኅጉሩን ደሕንነት በተመለከተ “በአስቸኳይ የድርጊት መርሐ-ግብር ማዘጋጀት አለበት። አለበለዚያ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋንያን መጻኢ እጣ ፈንታችንን ይወስናሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “ዕቅዱ አሁኑኑ መዘጋጀት አለበት” ያሉት ቱስክ የሚባክን ጊዜ አለመኖሩን ጠቁመዋል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW